ሩሲያ እና ዩክሬን: ናይጄሪያ በዩክሬን ከጦርነት የሚሸሹ አፍሪካውያን የተያዙበትን መንገድ አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የናይጄሪያ መንግስት ዜጎቹ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጦርነት ከምታመሰው ዩክሬን እንዳይወጡ እየተደረገ ነው መባሉን ተከትሎ ድርጊቱን አውግዟል።
በሩሲያ ወረራ ምክንያት የተፈጠረውን ጦርነት ሸሽቶ ወደ ፖላንድ ለመዝለቅ ሲሞክር የነበረው ናይጄሪያዊው አይዛክ የድንበር ሰራተኞች አፍሪካውያንን ማለፍ እንደማይችሉ እንደተነገረው ገልጿል።
"እንድንመለስ አባረውናል። በፖሊስ ዱላ ተመትተናል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
በደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣን የሆኑት ክሌይሰን ሞንዬላ ተማሪዎች በድንበር አቅራቢያ በ"መጥፎ ሁኔታ" መያዛቸውን አስታውቋል።
የዩክሬን የደህንነት ባለስልጣናት ሀገሪቱን ጥለው ወደ ድንበር የሚሄዱ አፍሪካውያን አውቶቡሶች እና ባቡሮች ላይ እንዳይሳፈሩ መከልከላቸውን የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።
በዩክሬን የሚኖረው ናይጄሪያዊው ኦሴሜን ለቢቢሲ እንደገለፀው ወደ ፖላንድ ድንበር ለመጓዝ በሊቪቭ በባቡር ለመሳፈር ሞክሮ ዩክሬናውያን ብቻ እንዲገቡ እንደሚፈቀድላቸው ተነግሯቸዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ በዩክሬን ወደ 4 ሺህ የሚጠጉ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች እንዳሉ የገለጹ ሲሆን አብዛኞቹ ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ወደ ፖላንድ እንዳይገባ የተከለከለ ቡድን መኖሩን ገልጸው ወደ ዩክሬን ተመልሰው ወደ ሃንጋሪ ለማቅናት እየሞከሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ቡሃሪ "በትዊተር ገፃቸው ላይ የያዙት ፓስፖርት ወይም የቆዳ ቀለማቸው ምንም ይሁን ምን ከግጭት የሚሸሹ ሁሉ በተባበሩት መንግስታት ስምምነት መሰረት ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ የመሸሽ መብት አላቸው" ብለዋል።
የፖላንድ ድንበር ጥበቃ ሃይል ከዩክሬን ግጭት የሚሸሹ የየትኛውም ዜግነት ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ፖላንድ እየተቀበለች እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ የዩክሬንን የድንበር ሃይል ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ጂኦፍሪ ኦንያማ ከዩክሬን አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር መነጋገራቸውንና የዩክሬን ድንበር ጠባቂዎች ከዩክሬን የሚወጡ የውጭ ዜጎች ያለ ምንም ገደብ እንዲያልፉ ትእዛዝ እንደተሰጣቸው አረጋግጠውልኛል ብለዋል።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩክሬን የሚወጡ ዜጎቹ ወደ ፖላንድ ለመግባት ከመሞከር ይልቅ ወደ ሃንጋሪ ወይም ሮማኒያ እንዲያቀኑ መክሯል።
እስካሁን ወደ 200 የሚጠጉ ከዩክሬን ግጨት የሸሹ ናይጄሪያውያን ዋና ከተማዋ ቡካሬስት መድረሳቸውን በሮማኒያ የናይጄሪያ አምባሳደር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሩሲያና ዩክሬን ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ከ500 ሺህ በላይ ዩክሬናውያን የሩስያን ወረራ ለመሸሽ ሀገር ጥለው ወጥተዋል።












