ሩሲያና ዩክሬን ንግግር ቢያደርጉም ውጊያው ግን እንደቀጠለ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሩሲያና ዩክሬን የተኩስ አቁም ለማድረግ ድርድር ቢጀምሩም ጦርነቱ ግን አሁንም አምስተ ኛ ቀኑን እንደያዘ ይገኛል።
የዩክሬኗ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችው ካርኪቭ ውስጥ ሩሲያ በተኮሰችው ሚሳኤሎች በአስርታት የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በዋና ከተማዋ ኪዬቭ ደግሞ የአየር ጥቃት ሊኖር እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ ነበር።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ ካርኪቭ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ''የጦር ወንጀል ነው'' ብለውታል። በሌላኛዋ የዩክሬን ከተማ ቼርንሂቭም ቢሆን ከባድ የሆነ ጥቃት ሲፈጸም እንደነበር ተገልጿል።
ሩሲያ በአሁኑ ሰአት ዩክሬንን በበርከታ ግንባሮች ነው እያጠቃች የምትገኘው። ነገር ግን የዩክሬን መከላከያ ኃይል ባደረገው ከፍተኛ የመከላከል ስራ የሩሲያን ግስጋሴ በእጅጉ ማስተጓጎል ችሏል።
ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱም ከተሞችም ቢሆኑ እስካሁን በዩክሬን ቁጥጥር ስር ነው የሚገኙት።
ከጦርነት ቀጠናው በተጨማሪ ሩሲያ ላይ እየደረሰ ያለው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እንደቀጠሉ ነው። ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያውያን ከውጭ አገራት ገንዘብ ማንቀሳቀስ የከለከሉ ሲሆን ይህ ደግሞ የሩብል ዋጋ ማሽቆልቆልን ተከትሎ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ዋና ጸሀፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተኩስ አቁም ስምምነት በፍጥነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ሩሲያን ከቤላሩስ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ደግሞ የዩክሬን እና የሩሲያ ኃላፊዎች የመጀመሪያ ዙር ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
ምንም እንኳን በርካቶች ይህ ድርድር እምብዛም ለውጥ እንደማያመጣ ቢገልጹም የዩክሬን ኃላፊዎች ግን የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች ወደ አገራቸው ተመልሰው ውይይት እንደሚያደርጉና ስለሁለተኛው ዙር ውይይት ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል።
ሩሲያ በበኩሏ ሁለቱም ወገኖች ንግግሩን ለማስቀጠልና በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ንግግር ለመገናኘት መወሰናቸውን ገልጻለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ትናንት ማምሻውን ባሰተላለፉት መልእክት በካርኪቭ ከተማ ንጹሀን ዜጎች ሆን ተብሎ ኢላማ እየተደረገ ስለመሆኑ ከአይን እማኞች ጭምር መረጃ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
የምዕራቡ ዓለም አገራት ዩክሬን ምንም አይነት በረራ የማይካሄድባት እንድትሆን እንዲያስገድዱ ቢጠይቁም አሜሪካ ግን ይህ ውሳኔ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት ውስጥ ሊከት ስለሚችል በማለት ይህንን ሀሳብ ለጊዜው ይቆይ ብላለች።
በማህበራዊ ሚዲያዎች በተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ካርኪቭ ከተማ ላይ በርካታ ሮኬቶች ሲተኮሱ የሚያሳዩ ሲሆን አካባቢው ደግሞ በርካታ ሰዎች የሚኖሩበት እንደሆነ ተነግሯል።
ሩሲያ ግን ቀደም ብላ ንጹሀን ዜጎችን ኢላማ እንደማታደርግ ገልጻለች።
አዲስ የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት የሩሲያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሰሜናዊ ኪዬቭ በኩል እስከ 64 ኪሎሜትሮች ድረስ ይታያሉ። ነገር ግን በኪዬቭ ዙሪያ በድጋሚ ከፍተኛ ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ ነዋሪዎች ተመልሰው ወደ መጠለያቸው እንዲገቡ ተገድደዋል።












