ኔቶ ትራምፕ የሰጡት አስተያየት “የአባላቴን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምዕራባዊያን የደኅንነት ጥምረት የሆነው ኔቶ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰጡት አስተያየት “የቃል-ኪዳኑን አባላት ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብሏል።
ይህን ያሉት የሰሜን አትላንቲን ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት ሊቀ-መንበር ናቸው።
ጄንስ ስቶልትንበርግ አክለው የትራምፕ አስተያየት ዩኤስና አውሮፓን ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሩሲያ ክፍያቸውን በጊዜ ያልፈፀሙ የኔቶ አባላትን እንድታጠቃ “አበረታታለሁ” ብዬ ለኔቶ ተናግሬያለሁ ማለታቸው ቁጣ ቀስቀሷል።
የኔቶ አባላት ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢያቸው 2 በመቶውን ለኔቶ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው።
የቃል-ኪዳኑ አባላት አንድ አገር ከተነካ ሁላችንም ተነካን ማለት ነው ይላሉ።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የትራምፕን አስተያየት ከሰሙ በኋላ “አስገራሚ እና አደገኛ” ብለው የቀድሞው ፕሬዝደንት የሩሲያው አቻቸው “ጦርነት እንዲከፍቱ መንገድ እየሰጡ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሳውዝ ካሮላይና ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያሰሙት ትራምፕ፣ ስለኔቶ አስተያየት የሰጡት በጥምረቱ ስብሰባ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
እሳቸው እንደሚሉት የአንድ “ትልቅ አገር” መሪ ክፍያ መፈጸም ባይችል እና ከሩሲያ ጥቃት ቢፈጸምብን ምን ሊገጥመን ይችላል ብለው ጥያቄ አቅርበው ነበር።
አክለው እኒህ መሪ ይህ ቢሆን ዩናይትድ ስቴትስ ታግዘናለች ወይ ብለው መጠየቃቸውን አውስተዋል።
“እኔ እንዲህ አልኩ፡ 'መክፈል አትችልም?' 'አቅምህ አይችልም?'፤ እኔ ልጠብቅህ አልችልም፤ እንዲያውም የፈለጉትን እንዲያደርጉ ነው የምገፋፋቸው። መክፈል አለብህ።”
ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው በሚቀጥለው የአሜሪካ ምርጫ እንደሚወዳደሩ የሚጠበቁት ትራምፕ ንግግራቸው ስለየትኛው የኔቶ አባል አገር አሊያም መሪ እንደሆነ እንዲሁም መቼ እንደተናገሩት ግልጽ አላደረጉም።
ኔቶ በአውሮፓውያኑ 2023 ባወጣው ሪፖርት ከ30 አባል አገራት 19 የሚሆኑት ከ2 በመቶ በታች ገቢያቸውን ነው ለመከላከያ እያዋሉ ያሉት ይላል።
ከእነዚህ አገራት መካከል ጀርመን፣ ኖርዌይ እና ፈረንሳይ ይጠቀሳሉ።
ነገር ግን ዩክሬንና ሩሲያን የሚጋሩ አሊያም የሩሲያ አጋር የሆነችው ቤላሩስ ጎረቤት የሆኑ አገራት ከሚጠበቀው በላይ እያዋጡ ነው።
ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢዋ 3.9 በመቶው የምታዋጣው ፖላንድ ከአሜሪካ የበለጠ መዋጮ ታደርጋለች።
ሮማኒያ፣ ሀንጋሪ፣ ፊንላንድ እና የባልቲክ አገራቱ ላትቪያ፣ ኢስቶኒያ እና ሊቱዌኒያ ከ2.3 እስከ 2.7 በመቶ ያዋጣሉ።
እሑድ ዕለት መግለጫ ያወጡት የቃል-ኪዳኑ ሊቀ-መንበር ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ቢመጣብንም “ራሳችንን በጋራ ለመከላከል ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ጨምረው “አንዱ አባል አገር ሌላኛውን አልደግፍም ማለቱ አሜሪካና አውሮፓን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብለዋል።
የሪፐብሊካን ዕጩ ሆኖ በቀጣዩ ምርጫ ለመቅረብ ከትራምፕ ጋር እየተሟገቱ ያሉት ኒኪ ሄሊ ለፑቲን መወገን አደገኛ ነው ብለዋል።
ከቢቢሲ የአሜሪካው አጋር ሲቢኤስ ጋር ቆይታ የነበራቸው ሄሊ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን “ተቀናቃኞቹን የሚገድል አደገኛ ቦዘኔ” ብለዋቸዋል።












