ኬንያዊው የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ

ኬንያዊው አትሌት ከልቪን ኪፕቱም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪፕቱም ባለፈው ዓመት በቺካጎ በተካሄደው ውድድር በኢሊዩድ ኪፕቾጌ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ሰብሯል።

የዓለም የወንዶች ማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው የ24 ዓመቱ ኬንያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ።

እሑድ ዕለት በኬንያ ምዕራባዊ ክፍል በደረሰው አደጋ ሩዋንዳዊው አሰልጣኙ ጀራቬስ ሃኪዚማናም አብረውት አሸልበዋል።

ኪፕቱም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአገሩ ልጅ በእውቁ የማራቶን ሯጭ ኢሊዩድ ኪፕቾጌ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን መስበር ችሎ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት በቺካጎ በተካሄደው ውድድር ነበር ኪፕቱም አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን በሁለት ሰዓት ከ35 ሰከንድ በማጠናቀቅ በኪፕቾጌ ተይዞ የነበረውን ሰዓት ያሻሻለው።

ሁለቱም አትሌቶች በዚህ ዓመት መጨረሻ በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ በኬንያ የማራቶን ቡድን ውስጥ ተካተው ነበር።

የአትሌቱን ድንገተኛ ሕልፈት ተከትሎ ባለሥልጣናት፣ አድናቂዎቹ እና የሙያ አጋሮቹ ሃዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የኬንያ የስፖርት ሚኒስትር አባቡ ናምዋምባ በኤክስ ገጻቸው ሃዘናቸውን በገለጹበት ጽሑፍ “በጣም የሚያም ዜና! ኬንያ እንቁ የሆነውን አትሌቷን አጣች ። ቃል የለኝም” ብለዋል።

የኬንያው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ “ኬንያ እውነተኛ ጀግናዋን አጣች” ሲሉ በአትሌቲክስ ኮከቡ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ሴባስቲያን ኮ በበኩላቸው “ኪፕቱም በጣም አስደናቂ አትሌት ነበር። መልካም ሥራውን ትቶ ነው የሄደው። እጅጉን እንናፍቀዋለን” ብለዋል።

ታዋቂው ሯጭ እና አሰልጣኙ የሞቱበት አደጋ የደረሰባት መኪና

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ታዋቂው ሯጭ እና አሰልጣኙ የሞቱበት አደጋ የደረሰባት መኪና
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመኪና አደጋው የተከሰተው ትናንት እሑድ ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ መሆኑን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል።

አደጋውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠው ፖሊስ ኪፕቱም መኪናውን እያሽከረከረ የነበረ ሲሆን መኪናው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ መገልበጡንና ሁለቱም ወዲያውኑ ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል።

የፖሊስ ቃል አቀባዩ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት በመኪናው ውስጥ ሌላ አንዲት ግለሰብም የነበረች ሲሆን ጉዳት ደርሶባት ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አትሌቱ ዝናን የተቀዳጀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር።የመጀመሪያው የማራቶን ውድድር ላይ የተሳተፈው እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 ነበር።

የመጀመሪያውን ትልቅ የሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፈውም ከአራት ዓመታት ቀደም ብሎ ሲሆን ጫማ መግዛት ባለመቻሉ በውሰት ጫማ ነበር የተወዳደረው።

አትሌቱ ወደ ረዥም ርቀት ሩጫ ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ ከነበረው በመም [ትራክ] ላይ ከመሮጥ ልምድ በመውጣት የጎዳና ሩጫ በመጀመር ረገድም አዲስ እየመጡ ካሉ አትሌቶች አንዱ ነበር።

ኪፕቱም ባለፈው ዓመት ለቢቢሲ ሲናገር ያልተለመደው ምርጫው በሃብት እጦት ምክንያት የተወሰነ እንደነበር ተናግሯል።

“በመሮጫ መም ላይ ለመለማመድ ገንዘብ አልነበረኝም” ብሏል።

የ36 ዓመቱ አሰልጣኙ ሃኪዚማና በጡረታ ላይ የሚገኝ ሩዋንዳዊ አትሌት የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ኪፕቱም የዓለም ክብረ ወሰንን እንዲሰብር ለወራት ሲረዳው ቆይቷል።

እንደ አሰልጣኝ እና አትሌት የሁለቱ ግንኙነት የጀመረው በ2018 ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙትም ኪፕቱም በጣም ልጅ ሳለ ነበር።

“ ሕጻን እያለ በባዶ እግሩ ሆኖ ከብቶችን ሲጠብቅ አውቀዋለሁ” ሲሉ ሃኪዚማና ባለፈው ዓመት በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ ትውውቃቸውን አስታውሰዋል።

“ጊዜው እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 ነበር ።በአባቱ እርሻ አጠገብ አሰለጥን ነበር።መጥቶ ይመታኝ እና ተከትዬ አባርረው ነበር” ሲሉ ኪፕቱም ለደረሰበት ስኬት እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።