በጎዳና ላይ ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ ክብረ ወሰን የሰበረችው ድርቤ ወልተጂ

ድርቤ ወልተጂ

የፎቶው ባለመብት, WORLD ATHLETICS

ባለፈው እሁድ በላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ በተካሄደው አንድ ማይል የዓለም የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ድርቤ ወልተጂ የርቀቱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ታሪክ ሠርታለች።

የርቀቱ ክብረ ወሰን በአሁኑ ጊዜ በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍ እና ክብረወሰኖችን በማሻሻል የወቅቱ ኮከብ አትሌት በሆነችው ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕየጎን ተይዞ ነበር የቆየው።

አሁን ድርቤ በ4 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በሆነ ጊዜ የርቀቱን የጎዳና ላይ የዓለም ክብረ ወሰንን ያሻሻለችው ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የአንድ ማይል ውድድር ላይ መሆኑ አድናቆትን አስገኝቶላታል።

በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ለቢቢሲ የተናገረችው ድርቤ፣ “የጎዳና ላይ ሩጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሮጥኩት። ክብረ ወሰን ማሻሻል ያሰብኩት እና የጠበቅኩት ነገር አይደለም” በማለት ውጤቷ ከጠበቀችው በላይ መሆኑን ገልጻለች።

ድርቤ ከሁሉ በላይ ድሏን ልዩ የሚያደርገው በዓለም ላይ ዝናዋ እየናኘ ካለችው ልምድ ካላት ኮከብ አትሌት ፌዝ ኪፕየጎን ጋር ተፎካክራ በበላይነት ማሸነፍ መቻሏ መሆኑን ተናግራለች።

“ወደ ውድድሩ ስገባ ‘ባሸንፍ ደስ ይለኛል’ በሚል ስሜት እንጂ፣ ርቀቱ የመጀመሪያዬ እንደመሆኑ ክብረ ወሰን እሰብራለሁ ብዬ አልጠበኩም ነበር” በማለት ውጤቱ ለእሷም የተለየ እደሆነ ገልጻለች።

የአንድ ማይል ርቀቱ ብዙም ሳያደክማት ወደ መጠናቀቂያው ላይ መድረሱን የምትናገረው ድርቤ፣ “ወደ መጨረሻው ላይ ስንደርስ እኔ ብዙ የሚቀረን መስሎኝ ነበር። የውድድሩን ማጠናቀቂያ ቦታ ሳይ ደንግጬ ፍጥነቴን ጨመርኩት። እንደዚያ ቶሎ እንደሚያልቅ አላሰብኩም።” ብላለች።

በውድድሩ አሸናፊ ትሆናለች ተብላ የተጠበቀችው እና የአንድ ማይል ክብረ ወሰን ባለቤት የነበረችው ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕየጎን፣ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ኃይሉን ተከትላ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ፌዝ ባለፉት ወራት ሦስት የተለያዩ የአትሌቲክስ ክብረ ወሰኖችን የሰበረች ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በሃንጋሪ፣ ቡዳፔስት ላይ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ውድድር አንደኛ ስትወጣ፣ ድርቤ ሁለተኛ፣ ሲፈን ሐሰን ደግሞ ሦስተኛ ወጥተው ነበር።

ከፌዝ ጋር ሦስት ጊዜ አብራ የተፎካከረችው ድርቤ በጠንካራ አትሌትነቷ ታደንቃታለች። “እሷ ጠንካራ አትሌት ስለሆነች እና ተሞክሮ ስላላት በተለይ እንዴት ተፎካካሪዎቿን ቆርጣ እንደምትሄድ አይቼ ተምሬያለሁ። በዚህ ውድድርም አሸንፌያት ተምሬባታለሁ” ብላለች።

ድርቤ በላቲቪያ፣ ሪጋ ላይ ያሸነፈችበት የጎዳና ላይ የአንድ ማይል ሩጫ በአትሌቲክስ ውድድር ዘርፍነት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ዕውቅና ያገኘው።

የውድድሩን ክብረ ወሰን የሰበረችው የ21 ዓመቷ ድርቤ ወልተጂ፣ ያሳየችው ብቃት በአትሌቲክስ ጋዜጠኞች እና ተንታኞች ዘንድ አድናቆትን አስገኝቶላታል።

ድርቤ ከዚህ ቀደም በዓለም አትሌቲክስ 1500 ሜትር ውድድር የብር ሜዳልያ ያገኘች ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2018 የ800 ሜትር የሩጫ ውድድር ክብረ ወሰን ሰብራም ነበር።

ስለወደፊት ዕቅዷ በቢቢሲ የተጠየቀችው ድርቤ “በ1500 እና በ5000 ሜትር በመወዳደር ለራሴ እና ለአገሬ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማምጣት እፈልጋለሁ” ስትል መልሳለች።