ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት አሰፋ የሰበረችው የማራቶን ክብረ ወሰን ለምን መነጋገሪያ ሆነ?

ትዕግሥት አሰፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአራት ዓመታት በፊት በገጠማት ጉዳት ምክንያት በሐኪሞች ሩጫ እንድታቆም የተመከረችው ትዕግሥት፣ ባለፈው ሳምንት መስከረም 13/2016 ዓ.ም. ጀርመን ላይ ከባዱን የማራቶን ውድድር ክብረ ወሰን በሰፊ የሰዓት ልዩነት በማሻሻል ዓለምን አስደንቃለች።

ይህንን የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን በሁለት ደቂቃ ከ11 ሰከንዶች ለማሻሻል ዓመታትን እና ከፍተኛ ልፋትን እንደሚጠይቅ በስፖርት ተንታኞች እየተነገረ ነው።

ትዕግሥት ግን በርሊን ላይ ክብረ ወሰኑን ስታሻሻል በጥሩ ጉልበት ላይ እንደነበረች በመጥቀስ ከዚያም በላይ ሰዓቱ ሊሻሻል እንደሚችል ገልጻለች።

እሷም ሆነች አሠልጣኗ በዚህ ሃሳብ ከመስማማታቸው በሻገር፣ ቀጣይ ዕቅዷም የራሷን ክብረ ወሰን መልሳ ማሻሻል እንደሆነ በልበ ሙሉነት በመናገር፣ ሪከርዱ ከሁለት ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች ሊወርድ ይችላል ይላሉ።

ክብረ ወሰን ያሻሻሉ አትሌቶች አሠልጣኝ የሆነው ሬናቶ ካኖቫም፣ “በልምምድ እና በቴክኖሎጂ እድገት አማካይነት [ከአውሮፓውያኑ] 2030 በፊት ሴቶች ክብረ ወሰኑን የበለጠ ሊያሻሽሉት ይችላሉ” የሚል እምነት አለው።

ደራሲ እና ጋዜጠኛው አሌክስ ሃቺንሰን ደግሞ “የማይሆን ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን ትዕግሥት በአንድ ጊዜ ከሁለት ደቂቃ በላይ በሆነ ፍጥነት ሪከርዱን ማሻሻል በመቻሏ ከዚህ በኋላ ከዚያ በላይ ማሻሻል አይቻልም ብሎ መከራከር ከባድ እንዲሆን አድረጎታል” ይላል።

“ሴቶች ማራቶንን 2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች ሊሮጡ ይችላሉ” የሚለው አሌክስ ለዚህ ደግሞ በጫማ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሥልጠና እና በአመጋገብ ላይ የሚኖሩ ለውጦች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ያመለክታል።

ባለ ክብረ ወሰኗ ትዕግሥት አሰፋ ከአጭር ርቀት ውድድር ነው ወደ ማራቶን የገባችው። በተመሳሳይ በርካታ አትሌቶችም ከትራክ ውድድር ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች ፊታቸውን እያዞሩ ነው። ምክንያቱ ምን ይሆን?

ከአጭር ርቀት ወደ ማራቶን

ሬናቶ እንደሚለው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ኢሉድ ኪፕቾጌ የትራክ ላይ ተወዳዳሪ ሆነው ከ20 ዓመታት ቆይተዋል። በጊዜው ኮከብ አትሌቶች በበርካታ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ከማራቶን ይልቅ ከፍተኛ ገንዘብ ይገኝ የነበረው እዚያ ላይ በሚደረጉ ውድድሮች ነበረ።

“አሁን ግን ሁኔታው ተቀይሯል። በርካታ በተለያየ ደረጃ ከፍተኛ ሽልማትን የሚያስገኙ የማራቶን ውድድሮች አሉ። የትራክ ውድድሮች አሁንም ቢኖሩም የሚያስገኙት ሽልማት ግን ዝቅተኛ ነው” ይላል ሬናቶ ካኖቫ።

“ስለዚህም ማራቶን መሮጥ የሚፈልጉ አትሌቶች ውድድር የሚጀምሩት በትራክ ላይ ነው። ከዚያም በዓመት ውስጥ ወደ ግማሽ ማራቶን በመሸጋገር ወደ ሙሉ ማራቶን ይገባሉ።”

ዋነኛው ምክንያት ገንዘብ ነው የሚለው አሌክስ ሃቺንሰንም “ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት የጎዳና ላይ ውድድሮች ተወዳጅነት በፍጥነት አድጓል። በዚህም በቀዳሚ ደረጃዎች ላይ ለሚጨርሱ ሯጮች የሚሰጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከአዘጋጆች እና ከስፖንሰሮች ይቀርባል።”

ቀደም ሲል ኃይሌን እና ቴርጋትን የመሳሰሉ ሯጮች ወደ ማራቶን ለመግባት ወደ 30ዎቹ የዕድሜ ክልል አስኪገቡ ይጠብቁ ነበር። ማራቶን የረጅም ጊዜ ልምምድ እና ሥራን የሚጠይቅ ነው ተብሎም ይተመን ነበር ይላል አሌክስ።

“ነገር ግን ሳሚ ዋንጂሩን የመሳሰሉ ወጣት አትሌቶች ስኬት ያንን አስተሳሰብ ቀይሮታል። አሁን ደግሞ ትዕግሥትን የመሳሰሉ አትሌቶች በአትሌቲክስ ሕይወታቸው መጀመሪያ ላይ በማራቶን ለመወዳደር ፍርሃታቸውን አስወግደዋል።”

ትዕግሥት አሰፋ አሰፋ እና ሼይላ ኪፕቺሩይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትዕግሥት ክብረ ወሰን በሰበረችበት ውድድር ተከትላት ሁለተኛ ከወጣችው ኬንያዊት አትሌት ሼይላ ኪፕቺሩይ ጋር አዲሱን ጫማ ይዘው

አነጋጋሪው የትዕግሥት ጫማ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከትዕግሥት አሰፋ ድል ጋር ተያይዞ በውድድሩ ላይ ተጫምታው የነበረው ጫማ መነጋገሪያ ሆኗል። አዲሱ የውድድር ጫማ ቀላል እና ምቾትን የሚሰጥ በመሆኑ በማራቶን ሯጮች ፍጥነት ላይ የራሱ በጎ ውጤት እንዳለው አሌክስ ይናገራል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማውን አድርጋ የተወዳደረችው ትዕግሥትም ጫማው ከዚህ ቀደም ከምታደርጋቸው የቀለለ እና በጣም ምቹ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ጫማውን የሚያደርጉትን በርካታ አትሌቶች በልምምድ እና በውድድር ወቅት በጥቂት ደቂቃዎች ፈጣን እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል” የሚለው አሌክስ በልምምድ ወቅትም የራሱ የሆነ ተዘዋዋሪ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይናገራል።

ትዕሥስት ተጫምታው የተወዳደረችበት አዲሱ የውድድር ጫማ አዲዳስ አዲዮስ ፕሮ ኢቮ 1 የተባለ ሲሆን፣ እጅግ በጣም ቀላል እና ዋጋው 500 ዶላር የሚያስከፍል መሆኑም መነጋገሪያ አድርጎታል።

ትዕግሥት ካስመዘገበችው ከፍተኛ የማራቶን ክብረ ወሰን ጋርም ተያይዞ ስሙ በስፋት በመነሳቱ በዓለም ዙሪያ ትኩረትን ለማግኘት ችሏል። ይህም የአዲዳስ የሽያጭ ገቢ ላይ ከፍተኛ እመርታን ሊያስገኝ እንደሚችል ይታመናል።

ነገር ግን አሌክስ ሃቺንሰን “ከዚህ በፊት ተመርተው አገልግሎት ላይ ከዋሉት ጫማዎች በተለየ አዲሱ ጫማ በትዕግሥት ድል ላይ አስተዋጽኦ ይኑረው አይኖረው ወይም እንዲሁ የኩባንያው አዲስ የገበያ መሳቢያ ግፊት ይሁን የሚታወቅ ነገር የለም” ይላል።

የትዕግሥት አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ ምቾት የሚሰጥ ልብስ ሲለበስ የሚፈጥረውን ጥሩ ስሜት ያህል ጫማውም የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው ቢችልም “ዋናው ነገር ግን የእሷ ብቃት ነው” ይላል።

“ለአራት ወራት ከባድ ልምምድ ሰርተናል። ክብረ ወሰኑን ለመስበር ተዘጋጅተናል። ግምታችን የነበረውም ክብረ ወሰኑን ወደ 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ማውረድ ነበር፤ ግን ትዕግሥት ወደ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ በማሻሻል ትልቅ ውጤትን አምጥታለች” ብሏል አሠልጣኟ።

ሬናቶ ካኖቫም በበኩሉ “ጫማዎች ለዘመኑ አትሌቶች የተወሰነ ጥቅምን ሊሰጡ ይችላል። ቢሆንም ግን በግሌ እንደማስበው ጠቀሜታው ካምፓኒዎቹ ከሚሉት በእጅጉ ዝቅ ያለ ነው” በማለት ጫማዎቹ ለአንድ ውድድር ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በመሆናቸው ከዋጋ አንጻር መደበኛ ሯጮች ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው እንዳልሆኑ ይጠቅሳል።

ጨምሮም ጫማዎቹ የራሳቸው አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም “አሸናፊው አትሌቱ እንጂ ጫማው አይሆንም። አንድ ሯጭ በሰፊ የሰዓት ልዩነት ማሸነፍ ብትችል ምንም አይነት ተጨማሪ ማብራሪያ ሳያስፈልግ የአሸናፊነቷ ውጤት የራሷ፣ የአሰልጣኗ እና የማናጀሯ ነው የሚሆነው” ሲል የአትሌቲክስ ባለሙያው ሬናቶ ይደመድማል።