ነዳጅ ያስተሳሰራቸው ሩሲያ፣ ቻይና እና ሕንድ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱ ፕሬዚዳንት ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ እና የሕንዱ ፕሬዝዳንት ናሬንድራ ሞዲ ከሰሞኑ ተገናኝተው አንዳቸው ለአንዳንቸው ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።

ለፕሬዝዳንት ፑቲንም ይህ ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ ከሚገዟቸው መሪዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት ዕድልን የፈጠረ ነው።

ከዩክሬን ወረራ ጋር ተያይዞ ከምዕራባውያኑ አገራት ጋር ግንኙነቷ የሻከረው እና ማዕቀብ የተጣለባት ሩሲያ የነዳጇን ዋጋ ዝቅ አድርጋለች።

ይህ የነዳጅ ዋጋ መርከስም ቻይና እና ሕንድን በዋነኝነት የሳበ ሆኗል።

ከዩክሬን ጦርነት በኋላ የቻይና፣ የሕንድ እና የሩሲያ የንግድ ግንኙነት ጠብቋል።

አገራቱ ከአሜሪካ ተቃርነው ቆመዋል።

አሜሪካ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲሁም በንግድ አጋሮቿ ቻይና እና ሕንድ ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ጥላለች።

ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ ትገዛለች በሚል አሜሪካ ከፍተኛ ታሪፍ የጣለችባት ሲሆን፣ ይህም ሕንድን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳዘነ ሆኗል።

ቻይና አሜሪካ የጣለችባት ታሪፍ ላይ እንዲሁም የሩሲያን ድፍድፍ ነዳጅ በመግዛቷ ሊጣሉ ከሚችሉ ማዕቀቦች ለመውጣት እየተደራደረች ትገኛለች።

ሦስቱ መሪዎች ሰኞ፣ ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም የተገናኙት ቲያንጂን በተሰኘችው የቻይና ከተማ ውስጥ ነው።

የአገራቱ መሪዎች የተሰባሰቡት በቻይና ለተመሠረተው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዓለም አቀፍ የደኅንነት ጥምረት ለሆነው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት (ኤስሲኦ) ጉባኤ ላይ ነው።

የቀጣናው ጉባዔ ከምዕራቡ ዓለም የተለየ ዕይታን ለማስፈን እንዲሁም የበላይነትን ለመገደዳደር ያለመ ነው።

አንዳንድ ተንታኞች ደግሞ የአሜሪካን ተጽዕኖ ለመቋቋም ነው ይላሉ።

የዓለማችን ምጣኔ ሃብት ባልተረጋጋበት ሁኔታ መሪዎቹ ያደረጉት ጉባዔ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት ዕድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሩሲያ ትልቅ ዕድል

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህ ጉባዔ ሩሲያ ከታላላቅ አጋሮቿ ሕንድ እና ቻይና ጋር ያላትን የንግድ እንቅስቃሴዋን የበለጠ ለማጠናከር ዕድል እንደሰጣት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በርካታ ምዕራባውያን አገራት ከዩክሬን ወረራ ጋር ተያይዞ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት አቋርጠዋል።

ሆኖም ሁለቱ ታላላቅ አገራት ቻይና እና ሕንድ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን የንግድ ትስስር በማጠናከር ለምጣኔ ሃብቷ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ቻይና ባለፈው ዓመት ከ100 ሚሊዮን ቶን በላይ ድፍድፍ ነዳጅ ከሩሲያ ገዝታለች።

ይህም ግዢ ክብረ ወሰን የተባለ ሲሆን፣ ከሩሲያ ጠቅላላ የኢነርጂ ወጪ ንግድ 20 በመቶውን የሚሸፍን ነው።

በተመሳሳይም ሩሲያ ወደ ሕንድ የምትልከው ነዳጅ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ የተመነደገ ሲሆን፣ መጠኑም ወደ 140 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

ሩሲያ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የነዳጅ ምርቷን የምትልከው ለቻይና እና ለሕንድ ነው።

ሩሲያ ሩብ የሚሆነው የበጀት ገቢዋን የምታገኘው ከነዳጅ እና ጋዝ የወጪ ንግድ ነው።

ይህ ገቢዋ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነትም ይደግፍላታል።

ሩሲያ፤ ከሕንድ እና ከቻይና ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲመነደግ ተጨማሪ ቅናሾችን ብታደርግ የሚያስደንቅ እንደማይሆን የሕዝብ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ማንዳር ኦክ ለቢቢሲ ያስረዳሉ።

ይህ በተለይ ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ በመግዛቷ በያዘችው አቋም ከአሜሪካ ከሚደርስባት ጫና ወደ ኋላ እንዳታፈገፍግ ለማድረግ መሠረታዊ መሆኑን በአድላይድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማንዳር ያስረዳሉ።

የምዕራባውያኑን ማዕቀብ ተከትሎ ሩሲያ የነዳጅ ፍሰቷን ወደ ሕንድ አድርጋለች።

ሕንድ ለሩሲያ የሕይወት መስመር ስትሆን፤ ሕንድ ደግሞ ርካሽ የኃይል ምንጭ እንድታገኝ ዕድል ተፈጥሮላታል።

አሜሪካ ብታወግዛትም ሕንድ አሁንም ቢሆን ተጨማሪ ነዳጅ ከሩሲያ ልትገዛ ትችላለች።

የሕንድ ፕሬዝዳንት ሞዲ ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጥብቃ እንደምትፈልገው አረጋግጠውላቸዋል።

አገራቱ "በጋራ እና በአንድነት ተራምደዋል" ብለዋል።

የሕንድ ባለሥልጣናትም በተጨማሪ አገራቸው "ጥሩ ስምምነት" ከምታገኝበት ስፍራ ነዳጅ እንደምትገዛም ጠቁመዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ሕንድ የሩሲያን ነዳጅ መግዛቷን ተከትሎ ተጨማሪ 25 በመቶ የታሪፍ ቅጣት በመጣላቸው የአገራቱ ግንኙነት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሻክሯል።

ሕንድ ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ረጅም የንግድ ታሪክ በመጥቀስም ውሳኔውን "ፍትሐዊ ያልሆነ" ስትል ገልጻዋለች።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱ ፕሬዚዳንት ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሞዲን ገጽታ ከፍ የሚያደርገው ውሳኔ

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ይህ እርምጃቸው በአገራቸው ያላቸውን ገጽታ ከፍ የሚያደርግላቸው ነው።

ሕንድ ከትራምፕ አስተዳደር ለሚደርስባት ጫና እንደማትበገር እንደ ማሳያ ስለሚወሰድ "ሞዲ አሜሪካን ችላ ማለታቸው ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ይሰጣቸዋል" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ሕንድ ድፍድፍ ነዳጅ የምታገኘው ከውጭ አቅራቢዎች በመሆኑ ከሩሲያ መግዛቷ በምጣኔ ሃብት ረገድም አዋጭ ይሆንላታል ይላሉ።

ሕንድ በነዳጅ ረገድ በአንድ ወቅት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ቁልፍ ደንበኛ ነበረች።

ነገር ግን የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ ሩሲያ ድፍድፍ ነዳጇ ላይ ባደረገችው ቅናሽ ፊቷን ወደ ሞስኮ አዙራለች።

የሕንድ ማጣሪያዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ ይልቅ በቅናሽ ከሩሲያ አቅርቦቶች ማግኘታቸው ወጪያቸውን ዝቅ አድርጎታል።

ከሩሲያ የምታስገባውን ነዳጅ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳደገችው ቻይናም በመሪዎቹ ጉባዔ ላይ ይህንን ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትፈልግ የንግድ ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ፒተር ድራፐር ያስረዳሉ።

በዚሁ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የሩሲያ እና የቻይና ጋዝ ኮርፖሬሽኖች ለእስያ አገራት የሚያደርጉትን አቅርቦት ለመጨመር ተስማምተዋል።

ነገር ግን ፑቲን ከሕንድ ጋር ተጨማሪ የነዳጅ ሽያጭ ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ ተመሳሳይ ቅናሽ ለቻይና ላያደርጉ እንደሚችሉ ፕሮፌሰር ድራፐር ይገልጻሉ።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱ ፕሬዚዳንት ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለቻይና መድረክ

ከንግድ ባሻገር ቻይና በዚህ የመሪዎች ጉባኤ ከትራምፕ የቅርብ ጊዜ የፖሊስ እርምጃዎች በኋላ ከአሜሪካ የተሻለ ጠንካራ አማራጭ መሆን እንደምትችል ማሳያ መሆኑን ፕሮፌሰር ድራፐር ያክላሉ።

በጉባዔው ላይ ቻይና ትራምፕ ታሪፍ ከጣሉባቸው እንደ ፓኪስታን፣ ምንያማር እና ሲሪላንካ ጎን መቆሟን አሳይታለች።

ቻይና የምዕራቡን ዓለም የበላይነት ስትቃወም ቆይታለች።

ቻይና፤ በርካታ ዋነኛ ተዋናዮች ኃይልን የሚከፋፈሉበት ጽንሰ ሃሳብ በማንሳትም "የባለብዙ ዋልታ (መልታይ ፖላር) የዓለም ሥርዓት ግንባታን" ስታስታውቅ መቆየቷንም ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ።

ይህ የመሪዎች ጉባኤ በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ምክንያት የምጣኔ ሃብታቸው ውስብስብ የሆነውን ሦስቱን አገራት አንድ ላይ ማምጣቱን ፕሮፌሰር ኦክ ያስረዳሉ።

በተለይም የአሜሪካ ታሪፍ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሃብት ስጋት ለመጋፈጥ አገራቱ "ጠንካራ አጋርነትን የመፍጠር የኢኮኖሚ ፍላጎት አላቸው" ብለዋል።