የቻይናው ዢ እና የሩሲያው ፑቲን ባልተዘጋ ማይክራፎን ያወሩት 'ምሥጢር' ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከ20 በላይ የአገር ርዕሰ ብሔሮች በተገኙበት እና ቻይና ወታደራዊ ኃያልነቷን ለዓለም ባሳየችበት 80ኛ ዓመት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ዝክር ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የቻይናው ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲን ምናልባትም ሳይዘጋ በተረሳ ድምጽ ማጉያ እያወሩት የነበረው ጉዳይ ወደ መገናኛ ብዙኃን ደርሷል።
ሁለቱ መሪዎች እንዲሁም የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ከጎናቸው ኾነው እያወሩት የነበረው ጉዳይ የሰውነት አካል ንቅለ ተከላ በማድረግ ዕድሜን ከማራዘም ጋር የተያያዘ ነበር።
ሁለቱ መሪዎች ይህን ጉዳይ ሲነጋገሩ ስለራሳቸው ዕድሜ እያሰቡ ይሆን ወይም ጠቅላላ የሕክምና ሳይንሱ የደረሰበትን በማሰብ የታወቀ ነገር የለም።
በዚህ ባልተዘጋ ማይክራፎን በተቀለበ ድምጽ ፑቲን በሳይንስ ድጋፍ ሕይወትን ዘላለማዊ ስለማድረግ ሲያወሩ ይሰማል።
በባዮቴክኖሎጂ ድጋፍ ምናልባት ወደፊት ዘላለም መኖር የሚቻልበት ዕድል ይፈጠር ይሆናል ሲሉ ያልተዘጋ ማይክ ድምጻቸውን ቀልቦታል።
የሁለቱ መሪዎች ድምጽ ሊሰማ የቻለው የቻይና ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዝግጅቱን በቀጥታ በሚያስተላልፍበት ወቅት ነበር።
ይህንን በሚነጋገሩበት ወቅት የቻይናው ዢ መሀል ሆነው ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን በግራና በቀኝ አጅበዋቸው በታሪካዊው ቲይናሚን አደባባይን በእግር እያለፉ ነበር።
የቻይናው ዢ 13 ዓመት በሥልጣን ላይ የቆዩ ሲሆን፣ ፑቲን ሩብ ክፍለ ዘመን ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። ሁለቱም ከሥልጣናቸው የመልቀቅ ፍላጎት አሳይተው አያውቁም።
ትከሻ ለትከሻ ሆነው ታይናሚን አደባባይን እየተሻገሩ ሳለ ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ውይይት የሰውነት አካል ንቅለ ተከላ ሳይንስ ምን ያህል እያደገ እንደመጣ አውግተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከንግግሮቻቸው መሀል የሚከተለውን ያልተዘጋው መቅረጸ ድምጽ አስቀርቶታል፦
የቻይናው ዢ ጂንፒንግ ፡ ድሮ አንድ ሰው 70 ዓመት በሕይወት መኖሩ ብርቅ ነበር። አሁን 70 እኮ የልጅ ዕድሜ ነው።
ቪላድሚር ፑቲን፡ (ለአፍታ የማይሰማ ድምጽ ይከተላል) ...የሰውን የአካል ክፍል ደጋግሞ ማደስ ይቻላል። ይህም ማለት አንድ ሰው ደጋግሞ ወጣት መሆን ይችላል፤ ዕድሜው ምንም ይሁን ምን። ይህ ነገር ከቀጠለ ምናልባት ለዘላለሙ መኖርም ይቻል ይሆናል።
ዢ ጂንፒንግ፡ በዚህ ክፍለ ዘመን 150 ዓመት መኖር የሚቻልበት ተስፋ አለ።
ተንታኞች እንደሚሉት የሁለቱ መሪዎች ባልተዘጋ ድምጽ ማጉያ የተቀለበው ንግግራቸው ምናልባት ፍላጎታቸው የዓለምን አስተዳደር በአዲስ መልክ ማዋቀር ብቻ አለመሆኑን ነው። ምናልባትም ፍላጎታቸው ከኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ከፍ ያለ እንደሆነ አመላካች ነው ይላሉ።
ሁለቱ መሪዎች በወቅቱ ይነጋገሩ የነበረው በአስተርጓሚ ሲሆን፣ ንግግሩን ወደ እንግሊዝኛ የመለሰው ቢቢሲ ነው።
ፑቲን ወደ አገራቸው ከገቡ በኋላም ለሩሲያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ ምልልስ ከዢ ጂፒንግ ጋር የተለዋወጡትን ሐሳብ በተዘዋዋሪ ደግመውታል።
በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ዘመናዊ ሕክምና የሰውነት አካልን መቀየር እና ማደስ በመቻሉ የሰው ልጅ ዘለግ ያለ ዕድሜ መኖር እየቻለ ይመጣል ብለዋል።
"አማካይ ዕድሜ በየአገሩ የተለያየ ነው፤ ሆኖም የሰው ልጅ በሕይወት የሚቆይበት ዕድሜ ቀስ በቀስ እየጨመረ መሄዱ የማይቀር ነው'' ሲሉ አክለዋል።
ረቡዕ ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም. በተደረገው አስገራሚ የቻይና ወታደራዊ ትዕይንት የሰሜን ኮሪያውን መሪ ጨምሮ የዚምባብዌ፣ የፓኪስታን፣ የቬትናም፣ የኢራን እና የቤላሩስ መሪዎች ታድመዋል።
ብዙዎች የፖለቲካ ተንታኞች ይህን ስብስብ አሜሪካ እና ምዕራቡን ዓለም ለመገዳደር የተደረገ ትዕይንት እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ መሪዎችን በአሜሪካ ላይ እየዶለቱ ነው ሲሉ ከሰዋቸዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው እንዲህ የሚል መልዕክት ጽፈዋል፤ "ውድ ዢ ጂንፒንግ! በአሜሪካ ላይ እየዶለታችሁ ሳለ በዚያውም ለፑቲን እና ለኪም ጆንግ ኡን የከበረ ሰላምታዬን አቅርብልኝ።''















