ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረትን ወይም የኔቶ አባላትን የማጥቃት ፍላጎት የላትም- ሰርጌ ላቭሮቭ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ አገራቸው የአውሮፓ ኅብረትን ወይም የኔቶ አባል አገራትን የማጥቃት ፍላጎት የላትም አሉ።
ሆኖም ወደ ሞስኮ የሚቃጣ ማንኛውም "ጥቃት"፤ "ወሳኝ የሆነ አጸፋ" እንደሚሰጠው ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
ሚኒስትሩ ቅዳሜ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ምዕራባውያን አገራት በሩሲያ ላይ የሚሰነዝሩት ማስፈራሪያ "እየጨመረ እና እየተለመደ" መጥቷል ብለዋል።
ላቭሮቭ በንግግራቸው እስራኤልን ጠቅሰው ሩሲያ ሐማስ መስከረም 26፣ 2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ብታወግዝም ዌስት ባንክን ለመጠቅለል እንዲሁም በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመው "የጭካኔ ግድያ"፤ "ምንም ማስተባበያ" የለውም ብለዋል።
እስራኤል ግን በጋዛ የምታካሄደው ዘመቻ ሐማስን ለማሸነፍ መሆኑን ትናግራለች።
የሐማስ ጤና ሚኒስትር እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 65,926 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።
ላቭሮቭ እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ ሌሎች አገራት ላይ የፈጸመቻቸውን ጥቃቶችም ተችተዋል።
እስራኤል በኳታር እና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ የፈጸመቻቸውን የአየር ድብደባዎች "ሐማስን የማጥፋት ዘመቻ አካል ነው" ስትል ትገልጻለች።
ላቭሮቭ ሩሲያ እና ቻይና አርብ ዕለት ኢራን ላይ ዳግም የተጣለው ማዕቀብ እንዲዘገይ ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ ወዲህ ምዕራባውያን የዲፕሎማሲ ጥረትን አስተጓጉለዋል ሲሉ ተችተዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እርምጃው "ሕገወጥ" ነው ብለዋል።
ኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከእሁድ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።
ላቭሮቭ በአውሮፓ ያለውን ውጥረት በተመለከተ ሲናገሩ "ሩሲያ ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚደረገው ማስፈራራት፣ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት እና የአውሮፓ ኅብረት ጥቃት ለመሰንዘር የሚያሰሙት እቅድ እና ዛቻ፣ በጣም እየተለመደ እና እየጨመረ መጥቷል። ፕሬዚዳንት ፑቲን በተደጋጋሚ እንደዚህ ዓይነት ጠብ አጫሪነቶችን ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል" ብለዋል።
"ሩሲያ እንደዚህ ዓይነት ፍላጎት አልነበራትም፤ አይኖራትምም፤ ነገር ግን በአገሬ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት ወሳኝ የሆነ የአፀፋ ምላሽ ይጠብቀዋል።"
ዴንማርክ የሩሲያ ድሮኖች የአየር ክልሌን ጥሰው ገብተዋል ስትል ያቀረበችውን ክስ ሞስኮ ውድቅ አድርጋለች።
ዴንማርክ የተፈጠረው ክስተት 'የባለሙያዎች ተግባር" ይመስላል ያለች ቢሆንም፣ የሩሲያ ተሳትፎ ግን ስለመኖሩ ምንም የሚያሳየው ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኔቶ የሩሲያ ድሮኖች የፖላንድን አየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ ቅኝት እያደረገ ባለበት ወቅት ኢስቶኒያም ሩሲያ የአየር ክልሏን መጣሷን ተናግራለች።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አባል አገራት የአየር ክልላቸውን ጥሰው የገቡ የሩሲያ አውሮፕላኖችን መትተው መጣል አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ኔቶ በበኩሉ የሚፈጸምበትን ወታደራዊ ጥሰት ለመመከት "ሁሉንም አስፈላጊ የሆኑ ወታደራዊ እና ወታደራዊ ያልሆኑ መንገዶችን" እንደሚጠቀም ገልጿል።
በዚህ ሳምንት ትራምፕ፣ ሩሲያ በዩክሬን የምታካሄደው ጦርነት ላይ ያላቸውን አቋም በመቀየር ኪየቭ "በሩሲያ የተወሰዱባትን ግዛቶች በሙሉ ታስመልሳለች" ብለዋል።
ላቭሮቭ የአሜሪካ እና የሩሲያን ግንኙነት በተመለከተ ሲናገሩም "አሁን ባለው የአሜሪካ አስተዳደር አቀራረቦች ውስጥ የዩክሬንን ቀውስ በተጨባጭ ለመፍታት አስተዋፅኦ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ርዕዮተ ዓለማዊ አቋም ሳይወስዱ ተግባራዊ ትብብርን የመፍጠር ፍላጎትን እንመለከታለን።"
ምዕራባውያንን ሲተቹም ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት አሁን ለፍልስጤም የሰጡትን የአገርነት እውቅና በመጥቀስ ይህንን ያህል ጊዜ የቆዩት "እውቅና የሚሰጠው ማንም እና ምንም አይኖርም ብለው ነው" ብለዋል።















