የሩሲያ ቅጥረኞች ሊቢያን ቀጣይዋ ሶሪያ እንዳያደርጓት ተሰግቷል

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአምባገነኑን የሙአመር ጋዳፊን ሞት ተከትሎ ወደ ዲሞክራሲ ትገባለች የተባለችው ሊቢያ ወደለየለት ቀውስ ካመራች ድፍን 10 ዓመት ልትደፍን ነው።
አንድ የቀጠናው ተንታኝ ሊቢያ ከዚህ በኋላ ወደ ፍጹም ሰላም ለመምጣት ሌላ 10 ዓመት ይወስድባታል ሲሉ ተነብየዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በዚያች አገር በርካታ የውጭ ኃይሎች እጃቸውን ማስገባታቸው ነው።
በቀዳሚነት ምሥራቅ ሊቢያን የሚቆጣጠረው የጦር ጄኔራሉ ኻሊፋ ሃፍጣርን የሚደግፉት ግብጽ የተባበሩት ኢምሬትስ እና ሩሲያ ሲሆኑ ውስጥ ውስጡን ፈረንሳዮችም ድጋፍ ያደርጉለታል።
በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያገኘውን የትሪፖሊ መንግሥት ደግሞ ኳታር በተለይ ደግሞ ቱርክ ታግዘዋለች።
የረመዳን ወር ከገባ ወዲህ ከጦርነት አፍታ ብንወስድ አይሻልም ወይ ሲል የሰላም ጥሪ ያቀረበው ጄኔራል ሃፍጣር ሲቆጣጠራቸው የነበሩ ገዢ መሬቶቹን ተነጥቆ ነበር።
እንዲያው አንዳንዶች ኻሊፋ ሃፍጣር አብቅቶለታል ለማለት ዳድቷቸው ታይተዋል።
ሆኖም ዛሬ አሜሪካ ይፋ ባደረገችው መረጃ ጄኔራሉን ለመደገፍ ሩሲያ ረቂቅ የጦር መሣሪያ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ በገፍ እያስገገባች ነው።
ይህ የአሜሪካ መረጃ እውነት ከሆነና ጦርነት ካገረሸ ሊቢያ ዳግማዊ ሶሪያ የመሆን እጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል ተብሏል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ወታደራዊ ጉዳዮች እዝ (አፍሪኮም) ይፋ ባደረገው መረጃ ሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ለማገዝ የሚሆኑ ተዋጊ ጄቶችን ወደ ሊቢያ እያጋዘች ነው።
በሊቢያ ቅጥረኛ ተዋጊ ሆኖ የሚሰራው የሩሲያ የጦር ኩባንያ ዋግነር ግሩፕ ሲሆን ንብረትነቱም በእጅ አዙር የፑቲንና አስተዳደራቸው እንደሆነ በስፋት ይታመናል።
ይህን ቅጥረኛ ጦር ወደዚያ መላኳ ሩሲያ በጦርነቱ እንደአገር እጇ እንደሌለበት ለማስተባበል ምቹ እንዲሆንላት የዘየደችው መላ መሆኑ ነው።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሰሞኑ ውጊያ ካልቀናው ጄኔራል ኻሊፋ ሃፍጣር ጋር የስልክ ቆይታ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
አሜሪካ እንደምትከሰው የሩሲያ ተዋጊ ጄቶች በሶሪያ ምድር የአፍታ እረፍት እያደረጉ ስሪታቸው የራሺያ እንዳይመስል ቀለም እየተቀቡ ወደ ሊቢያ እያቀኑ ያሉት።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና ያለው የሊቢያ መንግሥት ሰሞኑን እንደገለጸው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቱርክ ድጋፍ ከ1ሺ በላይ የሩሲያ ቅጥረኞች ከሊቢያ ተገፍተው ወጥተዋል። በአንቶኖቭ አውሮፕላን ተጭነውም ወደ ሩሲያ ሄደዋል።
ሩሲያም ሆነች ኻሊፋ ሃፍጣር ይህን ዘገባ አላስተባበሉም።
የቱርክ ሳባህ ጋዜጣ የትሪፖሊ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ትናንት ስምንት የሩሲያ ሚግ-29 ጄቶች እንዲሁም ሱ-24 የጦር አውሮፕላኖች ከሶሪያ ተነስተው ወደ ሊቢያ በረዋል።
ሊቢያ በነዳጅ ሀብቷ እጅግ የናጠጠች ሀብታም አገር መሆኗና የውጭ ኃያላን አገሪቱንም ሆነ አካባቢውን ለመቆጣጠር ካላቸው ላቅ ያለ ፍላጎት የተነሳ በዚያች አገር የውክልና ጦርነት ከማድረግ አልፈው ትሪፖሊን የፍልሚያ መድረክ አስመስለዋታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት፣ ቀጥሎም የጀመርኗ መራሂተ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በዚያች አገር እጃቸውን ያስገቡ ኃይሎችን ወደ ጠረጴዛ ውይይት ጋብዘው የሰላም ስምምነቶችን ያስፈረሙ ሲሆን ተግባራዊነቱ ግን ቧልት ሆኗል።












