ቱርክ ወታደሮቿን ወደ ሊቢያ ልትልክ ነው

በኮማንደር ካሊፍ ሃፍታር የታዘዘው ብሔራዊ ወታደራዊ አባል ወደ ቤንጋዚ ሲያመራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቱርክ የሕዝብ እንደራሴዎች መንግሥት ወታደሮችን ወደ ሊቢያ እንዲልክ የሚፈቅደውን ሕግ አጸደቁ።

የቱርክ ወታደሮች በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ወዳለችው ሊቢያ እንዲሄዱ አዎንታቸውን የሰጡት አባላት 325 ሲሆኑ 184 የሕዝብ ተወካዮች ግን ውሳኔውን ተቃውመውታል።

የቱርክ መንግሥት ወታደሮቹን ወደ ሊቢያ የሚልከው በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ለተሰጠው መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ነው።

ይህ የተመድ እውቅና ያለው መንግሥት በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡድን ሲዋጋ ቆይቷል።

አሜሪካ የቱርክ መንግሥት ውሳኔ አላስደሰታትም።

ዋይት ሃውስ እንዳለው ትራምፕ የቱርኩን ፕሬዝደንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋንን በውጪ ሃገር ላይ ጣልቃ መግባታቸውን ኮንነዋል።

ለጀነራል ሃፍታር ድጋፍ የምትሰጠው ግብጽ የቱርክ መንግሥት ውሳኔን ኮንናለች።

ኤርዶጋን ወታደሮቻቸውን ወደ ሊቢያ ለመላክ ከውሳኔ የደረሱት እውቅና ያለው መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ነው።

ቱርክ የምትልካቸው ወታደሮች ከጀነራል ሃፍታር ሚሊሻዎች ጋር በቀጥታ የሚዋጉ አይደሉም። ይልቁንም እውቅና ላለው መንግሥት ወታደሮች ሥልጠና እና የምክር አገልግሎት ነው የሚሰጡት።

የቱርክ ውሳኔ ለጀነራል ሃፍታር ድጋፍ ከሚያደርጉ መንግሥታት ጋር ውጥረት ውስጥ ይከታታል የሚለው ስጋት እጅጉን አይሏል።

ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጆርዳን፣ የተባበሩት አርብ ኤምሬትስ እና ሩሲያ የጀነራሉ ደጋፊ ሃገራት ናቸው።

የቱርክ ምክትል ፕሬዝደንት ፉዓት ኦክታይ የቱርክ ወታደሮች ወደ ሊቢያ የሚያቀኑት ለአንድ ዓመት መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ምን ያህል ወታደሮች እንደሚጓዙ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የጀነራል ሃፍታር ወታደሮች የሊቢያን ዋና ከተማ ትሪፖሊን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲታገሉ ቆይተዋል።

የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ በህዝባዊ አብዮት እአአ 2011 ከተገደሉ በኋላ፤ ሊቢያ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

የትኛውም ኃይል ሊቢያን ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠረም።

Gen Haftar

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር

ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ናቸው?

ፊልድ ማርሻል ካሊፍ ቤልቃሲም ሃፍታር የአሜሪካ እና የሊቢያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የመሰረቱ እና የሚመሩ ተጽእኖ ፈጣሪ የጦር አለቃ ናቸው።

ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ መንግሥት ከሚቀናቀኑ ሁለት ቡድኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ጥምረት በመመስረት የትጥቅ ትግል ላይ ይገኛሉ። ጀነራሉ ከወራት በፊት ''አሸባሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች'' ባሏቸው አካላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

በጦር አዛዡ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው ጦር በወሰደው እርምጃ ቤንጋዚ ከተማን እና በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ደቡባዊ የሊቢያ ክፍሎችን ተቆጣጥሯል።

በሊቢያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዙ ንጹሃን ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። በተለይ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት እና በእስር ቤቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች የተገደሉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሊቢያ ከ8 ዓመታት በፊት በቀድሞ መሪዋ ሙአመር ጋዳፊ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ እና ከተገደሉ በኋላ ሰላም እና መረጋጋት ርቋት ቆይቷል።