ሊቢያ ሦስት የስደተኛ ማቆያ ማዕከላትን ልትዘጋ ነው

ስደተኞች በካምፕ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሊቢያ በአገሪቱ ያሉ ሦስት ትላልቅ የስደተኛ ማቆያ ማዕከላትን ልትዘጋ መሆኑን የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ፋቲ ባሻጋ አስታወቁ። ማዕከላቱ ሚስራታ፣ ታጆራ እና ኮምስ መሆናቸውም ተገልጿል።

ሚንስትሩ ይህን ያስታወቁት ባለፈው ስደተኞች ታጆራ ወደተባለው ማዕከል እንዲመለሱ መደረጋቸውን ተከትሎ ባጋጠማቸው ትችት ሲሆን ይህ ካምፕ በሐምሌ ወር በሚሳይል ተመትቶ ከ20 በላይ ስደተኞች ሕይወት አልፏል።

ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች ናቸው ተብሏል።

ማዕከሉ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት እና ራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ብሎ የሚጠራውን አማጺ ኃይል ለሚዋጉበት ቀጠና ቅርብ በመሆኑም እንደተዘጋ ተገልጿል።

በሊቢያ ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉ ድርጅቶች የእነዚህ ማዕከላት መዘጋት ሌሎች የስደተኛ ማዕከላት የተጨናነቁ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል። ከዚህ ባሻገርም በርካታ ስደተኞች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ እጅ ሊወድቁ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ለመጓዝ ሲሉ 150 ስደተኞች ባህር ላይ ሰጥመው ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

በዚህ ዓመት በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሰጥመው ከሞቱት ይህ አደጋ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ያለቁበት ነውም ተብሏል።

ሊቢያ ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ሙአመር ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ2011 ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ በግጭት እየታመሰች ሲሆን የተለያዩ የጦር አበጋዞች በሚቆጣጠሯቸው ሥፍራዎችም ተከፋፍላ ትገኛለች።