በሊቢያ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት በትንሹ 40 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።
ጥቃቱ የደረሰው በትሪፖሊ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኝ ታጆራ በሚባል ስፍራ ሲሆን 80 ሰዎች በፍንዳታው መቁሰላቸው ተገልጿል።
ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች ናቸው ተብሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሊቢያ ወደ አውሮጳ መሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች መነሻ ሆና እያገለገለች ነው።
ሊቢያ ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ሙአመር ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ2011 ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በግጭት እየታመሰች ሲሆን የተለያዩ የጦር አበጋዞች በሚቆጣጠሯቸው ስፍራዎችም ተከፋፍላ ትገኛለች።
የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆነው ኦሳማ አሊ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገረው ከሆነ የአየር ጥቃቱ የስደተኞች መቆያውን ሲመታ 120 ስደተኞች በውስጡ ነበሩ።
አክሎም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ያለ ሲሆን አሁን ያለውን መረጃ በቅድመ ዳሰሳ ያገኘነው ሲል ገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ፋዬዝ አል ሴራ ራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ብሎ የሚጠራውን አማጺ ኃይል ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል።
ጥቃቱ ማክሰኞ እለት የደረሰ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው "ቀድሞ የታሰበበት" እና ማቆያውን "ኢላማ ያደረገ" ነው በማለት ያወገዙ ሲሆን ድርጊቱ "ከባድ ወንጀል" ሲሉ ገልጸውታል።
አማፂ ቡድኑ በኻሊፋ ሐፍታር የሚመራ ሲሆን ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት በመዋጋት ይታወቃል።
ሰኞ እለት ጠንከር ያለ የአየር ጥቃት እንደሚያደርግ ገልጾ የነበረ ሲሆን በኢላማውም የተመረጡ ያላቸውን ስፍራዎች እንደሚያጠቃ አሳውቆ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት በስደተኞች ማቆያ ላይ የደረሰውን የአየር ጥቃት "እጅጉን አሳሳቢ" ሲል ገልጾታል።
ዶክተር ቢን አታኢ ጥቃቱ በደረሰበት የስደተኞች ማቆያ የተገኙ ሲሆን "እዚህም እዚያም ሰው ይታያል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው "መጠለያው ወድሟል፤ ሰዎች ያለቅሳሉ፤ የስነልቦና ቀውስ አለ፣ ሰቅጣች ነው" ሲሉ ሁኔታውን ገልፀውታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ በሊቢያ ተሻግረው አውሮጳ ለመድረስ የሚያስቡ ስደተኞች የሚቆዩት መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የስደተኛ ማቆያዎች ሲሆን አብዛኞቹ እነዚህ መጠለያዎች የሚገኙት ከአማፂያን ጋር ጦርነት በሚደረግባቸው ስፍራዎች ነው።
በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች አያያዝ ትችት ይቀርብበታል።
የአውሮጳ ህብረት ከሊቢያ ድንበር ጠባቂዎች ጋር በመተባበር የስደተኞች ጀልባን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ ይገኛል።
ነገር ግን ሰዎችን በድብቅ የሚያሻግሩ ቡድኖች የሀገሪቱን አለመረጋጋት እና ያለውን ቀውስ ተጠቅመው አውሮጳ ለመግባት የሚጓጉ ስተኞችን በነፍስ ወከፍ በርካታ ሺህ ዶላር ያስከፍሏቸዋል።












