የአውሮፕላን ጎማ ሥር ተደብቆ እንግሊዝ መግባት ያሰበው ግለሰብ ወድቆ መሞቱ ተሰማ

ኬኒያ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Public domain

ወደ እንግሊዝ ተደብቆ ለመግባት በማሰብ የአውሮፕላን ጎማ ውስጥ ተደብቆ የነበረው ሰው ወድቆ ሕይወቱ አለፈ።

ግለሰቡ ጎማው ከሚገባበት ማስቀመጫ ውስጥ የወደቀው፤ አውሮፕላኑ ወደ መዳረሻው መቃረቡን ተከትሎ ጎማውን በመዘርጋቱ ነው ተብሏል።

የግለሰብ አስክሬን የተገኘው ለንደን ከተማ በሚገኝ አንድ መናፈሻ ውስጥ ነው።

ባለስልጣናት ግለሰቡ ቀድሞውኑ አውሮፕላኑ ጎማ ላይ ተንጠልጥሎ ሳለ ህይወቱ ይለፍ ወይም ከጎማው ስር ወድቆ ያሉት ነገር የለም።

ፖሊስ ግለሰቡ ከናይሮቢ ኬንያ ወደ ለንደን ይበር በነበረ የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላን መውደቁን አረጋግጠዋል።

አንድ የዓይን እማኝ እንዳሉት፤ ከአውሮፕላኑ ላይ የወደቀው ግለሰብ ያረፈው ጎረቤታቸው ግቢ አጠገብ ነው። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈጉት እኚህ የዓይን እማኝ እንደሚሉት፤ ጎረቤታቸው በግቢ ውስጥ ሆነው ጸሃይ እየሞቁ ሳለ አንዳች ነገር እንደወደቀ መስማታቸውን ይናገራሉ።

''ከዛ በመስኮት ስመለከት አስክሬን እና በደም የተሸፈነ የአትክልት ስፋራ ተመለከትኩ'' ብለዋል።

''ከዚያ ወደ ውጪ ወጣሁ። ጎረቤቴም በጣም ተደናግጦ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።

ኦፍርቶን መንገድ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, አስክሬኑ የተገኘው ክላፍም በሚሰኝ አካባቢ ባለ መናፈሻ ስፍራ ነው

የለንደን ፖሊስ የአስክሬን ምረመራ እያደረገ መሆኑን እና ግለሰቡን "ሰው ነው የገደለው" የሚል እምነት እንደሌለ ጨምሮ አስታውቋል።

የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ሙሉ በሙሉ መመርመሩን እና በአውሮፕላኑ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

ቦርሳ፣ ውሃ እና ምግብ የአውሮፕላኑ ጎማ ታጥፎ የሚገባበት ቦታ ላይ መገኘቱ ተነግሯል።

የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ "6840 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው በረራ ስምንት ሰዓት ከ50 ደቂቃ ይፈጃል። በእኛ አውሮፕላን ተደብቆ ለመጓዝ ባደረገው ጥረት ህይወት ማለፉ ያሳዝናል። በክስተቱ ሃዘናችንን እንገልጻለን" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም የኬንያ አየር መንገድ ጉዳዩን ለመመርመር ከኬንያ እና እንግሊዝ ባለስልጣናት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።