ናይጄሪያ ትዊተር በድብቅ የሚጠቀሙ ሰዎችን አድና ልታስር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናይጄሪያ የመንግሥት ውሳኔ ተላልፈው ትዊተርን የሚጠቀሙ ሰዎችን በሕግ ልትጠይቅ መሆኑን አንድ የመንግሥት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ መንግሥት ባለፈው አርብ ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር አምባ እንዲታገድ መወሰኑ ይታወሳል።
የተንቀሳቃሽ ስልክ ኔትወርክ አቅራቢዎች ትዊተርን ለተጠቃሚዎቻቸው እንዳይቀርቡ የታገዱ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎችን ግን በድብቅ ድር አምባውን እየተጠቀሙ መሆኑ ተሰምቷል።
ድር አምባው፤ የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሓሙዱ ቡሃሪ የትዊትርን ሕግ የጣሰ መልዕክት ትዊት አድርገዋል በሚል ፅሑፉ እንዲሰረዝ ካደረገ በኋላ ነው መንግሥት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው።
መልዕክቱ ከመሰረዙ በፊት አንዳንድ ሰዎች ያዩት ሲሆኑ የፕሬዝደንቱ ፅሑፍ ከአርባ ዓመት በፊት የተካሄደው የናይጄሪያ እርስ በርስ ጦርነትን በሃገሪቱ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ ያለውን የመገንጠል ሐሳብ ያስቀረ ነው ይላል።
መንግሥት በፕሬዝደንቱ ትዊት መታገድ 'እንደተበሳጨ' ቢናገርም 'ጊዜያዊው' እገዳ ግን ከዚህ ጋር ተያያዥነት የለውም ብሏል።
"ከማሕበራዊ ድር አምባ ጋር በተያያዘ ናይጄሪያ ውስጥ ችግር እየተከሰተ ነው። አሳሳችና ሃሰተኛ መረጃዎች በድር አምባዎች በኩል እየተሰራጩ ብጥብጥ እያስከተሉ ነው" ብሏል የናይጄሪያ መንግሥት።
ትዊተር፤ አርብ ዕለት የናይጄሪያው መረጃ ሚኒስትር ላይ ሞሐመድ እገዳውን ካወጁ በኋላ ሁኔታው 'እጅግ አሳሳቢ ነው' ብሏል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎችም ተቋማት እገዳው ናይጄሪያ ውስጥ በነፃነት የመናገር መብትን ይጋፋል ሲሉ ተቃውመውታል።
መግለጫ የለቀቁት የናይጄሪያ ፍትህ ሚኒስትር አቡበከር ማላሚ "የመንግሥትን ውሳኔ ተላልፈው ትዊተር የተጠቀሙ ሰዎች በሕግ እንዲጠየቁ አዝዣለሁ" ብለዋል።
የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ኡማር ግዋንዱ መልዕክቱ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች የተላለፈ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የናይጄሪያ መንግሥት ትዊተር 'የናይጄሪያን ሕልውና' የሚፈታተን ነው ይላል።
ድር አምባው "ኃይማኖታዊ፣ ዘረኛና ሃሰተኛ መረጃዎች" መልዕክቶች እየተላለፉበት ነው፤ ይህ ደግሞ የአንዳንድ ሃገራትን ሕልውና የሚፈታተን ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ትዊተር ናይጄሪያ ውስጥ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን የፖሊስ ጭካኔን ጨምሮ የተለያዩ ማሕበረሰባዊ ጉዳዮች በስፋት እየተነሱ መንግሥት ላይ ጫና እንዲደርስ መልዕክት የሚላክበት አምባ ነው።












