ተዋናይት ሊዲያ ሞገስን 'ተደባዳቢ' ያደረጋት ምንድን ነው?

ሊዲያ ሞገስ

የፎቶው ባለመብት, Lidya Moges

ሊዲያ ሞገስን በርካቶች የሚያውቋት 'ላምባ' በተሰኘው ፊልም ላይ ከተወነች በኋላ ነው። የመጀመሪያ ፊልሟ በነበረው ላምባ በአተዋወኗ ብዙዎች አድንቀዋታል። ሽልማትም አግኝታበታለች። በትወናና በሌሎች የጥበብ ስራዎች ካላት ተሳትፎ ባሻገር ከተመረቀችበት የትምህርት ዘርፉ ጋር በሚቀራረበው ማርኬቲንግም ትሰራለች።

አመታትን ወደ ኋላ ስንመለስ ግን ሊዲያ 'በኃይለኝነቷ' ፣ 'በተደባዳቢነቷ' እና በተደጋጋሚ ከትምህርት ቤት በመታገድ ነው የምትታወቀው። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የደረሰባትን ተማሪ እንደ ኳስ ከመለጋት እና 'አንስታ ከማፍረጥ' ወደኋላ አትመለስም።

ሁለት ዓመታት ከቆየችበት ከዚህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፊት ደግሞ የነበራት ባህሪ ሌላ ነው። ቤተ ክርስቲያን በማዘውተር እና ማርሻል አርት በመማር መልካም ባህሪ አዳብራለች። ከመዋዕለ ህጻናት እስከ 8ኛ ክፍል በነበራት የትምህርት ዘመን ሊዲያ ከጓደኞቿ ጋር የምትግባባ፣ በሚኒ ሚዲያ የምትሳተፍ፣ በትምህርቷ የተጋች እና በጸባዩ የተመሰገነች እንደነበረች ትናገራለች።

ታዲያ የሊዲያን ባህሪ ምን ቀየረው? - ቡሊንግ!'

'ቡሊንግ' ምንድን ነው?

'ቡሊንግ' ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ ቀጥተኛ ትርጉም ባናገኝለትም ሰዎችን ማብሸቅ፣ ማሸማቀቅ፣ ማሳቀቅ፣ ማጥቃት እንዲሁም የጉልበተኝነት መንፈስ ማንጸባረቅ ነው በሚል ሊገለጽ ይችላል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት እና ስነባህሪ ኮሌጅ ዲን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሳይኮሎጂ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር የቆየዓለም ደሴ ለቡሊንግ አቻ የሆነ የአማርኛ ቃል ማግኘት ከባድ ነው ይላሉ። ሆኖም ጥቃት በሚል ሊገለጽ እንደሚችል ያስረዳሉ።

"ቡሊንግ ወይም ጥቃት የምንለው አንድን ሰው እንዲሸማቀቅ፣ እንዲፈራ፣ እንዲሰጋ፣ እንዲሳቀቅ የሚያደርጉ አካላዊም፣ ስነልቦናዊም፣ ስሜታዊም ጫናዎችን መፍጠር ነው" የሚሉት ዶ/ር የቆየዓለም ቡሊንግ የጸብ አጫሪነት [Aggression] አንዱ ዘርፍ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፈችው ሊዲያ ደግሞ ቡሊንግን "አንድ ሰው በመብቱ ወይም በተሰጠው ነገር እንዳይተማመን ወይም ደግሞ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር እንዳያደርግ በሰዎች ተጽዕኖ ሲደረግበት ነው" ስትል ትገልጸዋለች።

ሊድያ ሞገስ

የፎቶው ባለመብት, Lidya Moges

ሊዲያ በትምህርት ቤት ውስጥ በራሷ መንገድ ለመሄድ መሞከሯ እና "ሌሎች የሚሉትን ሁሉ መቀበል" አለመፈለጓ በሌሎች ነቀፋ እንዲቀርብባት፣ ዘለፋን እንድታስተናግድ መነሻ ሆኗል። በትምህርት ቤቱ ተጽዕኖ እንዳላት ከሚነገር ተማሪ ጋር በነበራት አለመግባባት ምክንያት አብዛኛው ተማሪ ከሷ ጋር ጓደኛ ለመሆን አይፈለግም ነበር።

በዚህም ምክንያት "ምንም የተለየ ነገር ሳይኖረው" በአለባበሷ፣ በጸጉር አሰራሯ 'በማሾፍ' ሌሎች ተማሪዎች እንዲስቁ እሷ ደግሞ እንድትሸማቀቅ ይደርግ እንደነበር ታስታውሳለች።

"ስወጣ ስገባ ስም ይሰጠኛል፤ ክፍል ውስጥ አሳይመንት ወጥቼ ሳቀርብ ይሳቅብኛል፤ ወረቀት ይወረወርብኛል፤ የምሳ ዕቃ ይሰረቅብኛል፤ አንድ አንድ ጊዜ ምሳ ዕቃዬ ሙሉ ቦርሳዬ ውስጥ ተደፍቶ አገኘው ነበር። አስተማሪዎቼ ጋር ስሄድ ይሄ ቀልድና ልጅነት ነው ተብሎ ማንም አያዳምጠኝም። ከዛም እኔ ደግሞ ጉልበተኛ ሆንኩኝ" የምትለው ሊዲያ ሰሚ ያጣችው በቤተሰቦቿም ጭመር እንደነበር ትናገራለች።

"ትምህርት ቤቱን ስላልወደድሽው ነው። ሃይለኛ ስለሆንሽ ነው። ረባሽ ስለሆንሽ ነው" በሚል ለዚህ ችግር ቤተሰቧቿ ትኩረት አልሰጡትም።

ሊዲያ ማርሻል አርት ሰዎችን መጉዳት እንደማይመክር ብታውቅም እራሷን ለመከላከል የሚያሸማቅቋትን ተማሪዎች ትመታለች። ይህም በተደጋጋሚ ለ15 ቀን ወይም ለሳምንት ከትምህርት እንድትታገድ አድርጓታል።

እንደ ዶ/ር የቆየዓለም ገለጻ ሊዲያ ላይ የደረሰውን ጨምሮ በርካታ የቡሊንግ አይነት አለ ይላሉ። ቡሊንግ እንደ መደብደብ፣ መጎንተል፣ ቦርሳ መንጠቅ ወይም በሌላ መንገድ ባለ አካላዊ ጥቃት ሊገለጽ ይችላል።

በመሳደብ፣ በመዝለፍ፣ ቅጽል ስም በመስጠት፣ በመሳለቅ፣ በመጠቋቆም እና በመሰል መንገዶች ቃላት በመሰንዘር የሚገለጸው ቡሊንግ ነው። ስም ማጥፋት፣ በሃሜትና በተመሳሳይ አይነት ድርጊት የሚፈጸመው ማህበራዊ 'ቡሊንግ' ተብለው ይጠራሉ።

በእነዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ዘመኑ 'ሳይበር ቡሊንግ'ን ይዞ መጥቷል።

'ሳይበር ቡሊንግ' የተለያየ መልክ ያለው ቢሆንም በማህበራዊ የትስስር መድረኮች አማካኝነት ሰዎችን ማሸማቀቅ አንዱ መገለጫው መሆኑን ነው የስነልቦና መምህሩ የሚያስረዱት።

ስለዚህ "ቡሊንግ የሚባለው የሌለበት ቦታ የለም፣ የማይተገበርበት መንገድ የለም ትምህርት ቤት እና ስራ ቦታ ላይ የተለመደ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

ብዙ ጊዜ ሰዎችን የሚያሸማቅቁ ሰዎች ጥቃት ከሚያደርሱባቸው ሰዎች ጋር የበለጠ ጉልበት ይኖራቸዋል። "እኔ ከሌላው እበልጣለሁ" በሚል መነሻ የሚደረግ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ለዚህ ጥቃት የተጋለጠ ነው።

ሰዎች በሰብእና ችግር፣ ራሳቸው የቡሊንግ ሰለባ በመሆናቸው፣ የበላይነት ስሜትን ለማንጸባረቅ፣ እጅግ ጥብቅ በሆነ አስተዳደግ ማለፍ ሰዎችን ሌሎችን እንዲያሸማቅቁ በምክንያትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም ዶ/ር የቆየዓለም ይጠቅሳሉ።

ሊድያ ሞገስ

የፎቶው ባለመብት, Lidya Moges

'ቡሊንግ' የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው?

ሊዲያ ቡሊንግ ያስከተለባት ችግር አሁንም ድርስ አብሯት እንደዘለቀ ትናገራለች። በወቅቱ በተደጋጋሚ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማት ከማድረግ በተጫማሪ ለማሸማቀቅ የሚሰነዘሩባት ቃላት "እውነት ነው ወይ?" ብላ እራሷን እንድትጠራጠር ያደርጋት ነበር።

"እነሱ እንዳሉት ቀጫጫ ነኝ? ፣ መልኬ አያምርም?፣ ጸጉሬ አያምርም? እንድል፤ ያለኝ ነገር እንዳልወደው ስለራሴ ያለኝ ግምት እንዲቀየር፤ ራሴን እንዳልወደው፤ በራስ መተማመኔ እንዲቀንስ፤ ወጥቼ እስክገባ ድረስ በራስ መተማመን እንዳይኖረኝ አድርጎኛል" ትላለች።

አክላም "በዛ ዕድሜዬ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር፣ የመጨነቅ ስሜት ነበረኝ፣ ከትምህርት ስታገድ አንድ ሁለት ቀን እንቅልፍ አይወስደኝም - እንዲሁ ሌሊቱ ይነጋል ፤ በጣም እናደዳለሁ።"

በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበራት አስደሳች ጊዜ እና ውጤት እንዲያሽቆለቁል ብቻ ሳይሆን ወደ ቀጣይ ክፍል የሚያሸጋግራትን ነጥብ ያጣችበትም ጊዜ ነበር።

በርግጥ ይህ ሁሉ ሊዲያን የሚፈትን ሁኔታ እና የሚያስከትልባት የስነልቦና ተጽዕኖ በሙሉ አሁን አብሯት የለም። እንዲያውም በጥበቡም ይሁን በሌሎች ስራዎቹ በውጤታማት እየተጓዘች ነው። ሆኖም አሁንም የቡሊንግ ተጽዕኖ ይንጸባረቃል።

"ተጠራጣሪ" እንድትሆን "ትንሽ የሚባሉ ነገሮችን ከበድ አድርጋ" እንድታይ እና አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ በሳቅ እና ጨዋታ መሃል የሚደረጉ ቀልዶችን በቀጥታ ለእርሷ የተሰነዘሩ ይመስሏታል።

"ሰው ሁሉ ለኔ ክብር የሌለው የሚመስለኝ ጊዜ አለ" ስትል ትጠቅሳለች።

በአብዛኛው በትምህርት ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚስተዋለው ቡሊንግን በሰፈር እና በቤተሰብ ውስጥም ሊከሰት እንደሚችል የሚያነሱት ዶ/ር የቆየዓለም በቡሊንግ ውስጥ አጥቂ/ አጥቂዎች፣ ተጠቂ/ ተጠቂዎች ሁኔታውን የሚመለከቱ ሰዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ጠቅሰዋል። ታዲያ ይህ ሁኔታ ሶስቱም አካላት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይናገራሉ።

ቡሊንግ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለጽ የስነልቦና እና አእምራዊ ጉዳቶች ቢኖሩትም በተለይ ተጠቂው ራስን እስከ ማጥፋት የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም ገልጸዋል።

ቡሊንግ የሰዎች በራስ መተማመን ዝቅ እንዲል፣ በመሳቀቅ የተሞላ ህይወት እንዲገፉ፣ ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲስተጓጎል፣ በስራና ትምህርት ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርና ከዚያም አልፎ ለበርካቶች ትምህርት ማቋረጥ ምክንያት እንደሚሆንም አክለዋል።

ሰዎችን ማሸማቀቅ የትም ያለ እና በተለይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ እጅግ የሚስተዋል እና ከፍ ያለ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የሚያሳዩ ጥናቶች መኖራቸውን የስነልቦና መምህሩ ጠቅሰዋል።

ሆኖም እያስከተለ ካለው ስነልቦናዊ ጉዳት አንጻር ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው አንስተዋል። "በማህበረሰቡ፣ በትምህርት ቤቶች እና የሰዎችን መብት በሚያስከብሩ ተቋማት እውቅና አልተሰጠውም። ጉዳቱ የአንድ ጊዜ፣ የአጭር ጊዜ ሳይሆን ዘላቂ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።

በዚህ ሃሳብ ሊዲያም ትሰማማለች። "ለምሳሌ አንድ ሰው ትምህርት አልወድም ካለ ምናልባት ቡሊንግ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ብዙ ትምህርት የማይወዱ ልጆች ይፈጠራሉ ማለት ነው። ተምሮም ተመርቆም በራሱ የሚተማመን ሰው አይኖርም" ማለት ነው። "ብዙ ሰዎች ቀላል አድርገው ነው የሚያዩት በዚህ ምክንያት ግን ብዙ ሰው እናጣለን" ሰዎች ስለጉዳዩና ይዞት ስለሚመጣው መዘዝ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ደግሞ መፍትሄው እንደሆነ ታምናለች።

ሊዲያ በበጎ ፈቃደኝነት ልጆችን የምታስተምር ሲሆን ቡሊንግ በእርሷ ላይ ያደረሰው ጫና ቢያንስ በእነርሱ ላይ እንዳይደርስ ክትትል እንደምታደርግ ትናገራለች።

መፍትሄውስ?

ተዋናይቷ ሊዲያ ቡሊንግ ያስከተለባትን ጫና ለመቋቋም እየሞከረች ላምባ ፊልም ላይ የነበራትን ትወና ጨምሮ በርከት ያሉ ስራዎችን ሰርታለች።

ሆኖም ቡሊንግ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም በስራዎቿ ላይ አልፎ አልፎም ቢሆን አጋጥሟታል።

የትምህርት ተቋማት፣ ተማሪዎችና ወላጆችን ጉዳዩን በሚገባ እንዲረዱት በማድረግ ችግሩን ማቅለል ይችላል ስትል ትጠቅሳለች። ወላጆች የልጆቻቸውን ሰሜት ተከትለው አቅሙ እና ዕድሉ ካለ ትምህርት ቤት እስከመቀየር የሚደርስ እርምጃ ሊወስዱ ይገባልም ብላለች።

በሌላ በኩል በትምህርት ቤቶች ውስጥ አካዳሚን መሰረት ካደረገ ትምህርት በተጨማሪ ግብረገብነን መሰረት ያደረገ ትምህርት ቢሰጥ ችግሩን ሊቀንሰው ይችላል የሚል እምነት አላት።

ቡሊንግ "በሄድንበት ሁሉ የሚከተለን ጠበሳ ያስከትላል" የሚሉት ዶ/ር የቆየዓለም በተለይ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የተሻለ የቁጥጥር ስርዓትንና የምክር አገልግሎትን በማጠናከር ችግሩን ማቃለል ይችላል ይላሉ።

"ከስረ መሰረቱ ለመቀነስ ግን ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ መብት እና ግዴታ እንዲያውቁ ማድረግ" ተገቢ መሆኑን የሚያስረዱት የስነ ልቦና መምህሩ መደበኛ መገናኛ ብዙኀንም ይሁኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች ጸብ አጫሪነት የሚያስተምሩ ይዘቶችን እንዳያሰራጩ መጠንቀቅ ይገባቸዋል ሲሉ ጠቅሰዋል።

ቡሊንግ የሚጋጥማቸው ሰዎች ደግሞ ጉዳዩን ለቤተሰብ፣ ለትምህርት ቤት ከፍም ሲል ለህግ አካል ማሳወቅ ይገባቸዋል ብለዋል። ይህንን የልጆቹን አቤቱታ ችላ ማለት እና "የልጆች ጨዋታ ነው" ብሎ ማለፍ ትንሹን ችግር አባብሶ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ የማይሽር ጠሳን ይጋብዛል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።