ቤተሰብ፡ የፈለጉትን ሰው ማግባት የማይፈቀድላቸው ናይጄርያውያን

የጋብቻ ቀለበት የምታወልቅ ሴት ጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ናይጄርያውኑ ጥንዶች እንዳይጋቡ ቤተሰቦቻቸው መወሰናቸውን ተከትሎ ራሳቸውን ያጠፉት በዚህ ወር መባቻ ነበር።

ቤተሰቡ ጋብቻውን አንቀበልም ያለው ከጥንዶቹ የአንደኛቸው ቤተሰብ የዘር ግንድ የሚመዘዘው በባርነት ከተሸጡ ሰዎች በመሆኑ ነበር።

ጥንዶቹ ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት “ጥንታዊ አመለካከት ተመርኩዘው እንዳንጋባ ከለከሉን” ብለው ጽፈው ነበር።

በ30ዎቹ መግቢያ ላይ የነበሩት ጥንዶች ቤተሰቦች የሚኖሩት ኦኪጃ በተባለች ግዛት ነው። በኦኪጃ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ990ዎቹ የባርያ ንግድ ተከልክሏል።

ነገር ግን የኢግቦ ማኅበረሰብ አባላት የሆኑ ከባርነት ነጻ የወጡ ግለሰብ፣ የልጅ ልጆች ከሌሎች የኢግቦ ተወላጆች ጋር ትዳር እንዲመሰርቱ አይፈቀድም።

ራሳቸውን ያጠፉት ጥንዶች “ሁሉም ሰው የተፈጠረው እኩል ነው፤ ታዲያ የሰው ልጆች አንዱን ከሌላው ለምን ያበላልጣሉ?” ብለው ነበር።

ብዙ የኢግቦ ጥንዶች ተመሳሳይ መድልኦ ይፈጸምባቸዋል።

የ35 ዓመቷ ፌቨር ከሦሰት ዓመት በፊት ትዳር ለመመሥረት እየተዘጋጀች ነበር። ለአምስት ዓመት አብራው የነበረችው ፍቅረኛዋ ቤተሰቦች፤ የፌቨር ቅድመ አያቶች በባርነት ተሸጠው እንደነበሩ ሲያውቁ ግን ጋብቻውን ተቃወሙ።

መጀመሪያ ላይ ፍቅረኛዋ ከሷ ጎን ነበር። የቤተሰቦቹ ጫና ሲበረታበት ግን ሐሳቡን ለውጦ ተለያት።

ፌቨር “በጣም ከፍቶኝ ነበር። እጅግ ተጎድቻለሁ” ትላለች።

2017 ላይ የ44 ዓመቷ ኦጌ ማዱግው ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ኋላ ቀር መድልኦ ለማስወገድ ማኅበር መሥርተዋል

የፎቶው ባለመብት, ADAOBI TRICIA NWAUBANI

“ደንቦቹን መሻር እንችላለን

የባርያ ቤተሰቦች የሚገለሉት ከትዳር ብቻ አይደለም። ከባህላዊ አስተዳደር፣ ማኅበረሰባቸውን ወክለው ለሕዝብ እንደራሴነት ከመወዳደርም ይታገዳሉ።

መማር እና መሥራት ቢችሉም ከሌላው ማኅበራዊ ግንኙነት መገለላቸው ከውጪ አገራት ከመጡ የክርስትና ሰባኪዎች ጋር እንዲቀራረቡ አድርጓቸዋል።

ቤተሰቦቻቸው ባርያ የነበሩ ሰዎች ምንም ያህል ስኬታማ ቢሆኑ ማኅበረሰቡ የበታች አድርጎ ይወስዳቸዋል።

2017 ላይ የ44 ዓመቷ ኦጌ ማዱግው ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ኋላ ቀር መድልኦ ለማስወገድ ማኅበር መሥርተዋል።

ላለፉት ሦስት ዓመታት በደቡብ ምዕራብ ናይጄርያ አምስት ግዛቶች እየተዘዋወሩ ስለ እኩልነት ሲያስተምሩ ነበር።

“አሜሪካ ውስጥ ጥቁሮች የሚደርስባቸው እንግልትና እዚህ በባርያ ቤተሰቦች ላይ የሚደርሰው ስቃይ አንድ አይነት ነው” ይላሉ።

ኦጌ የባርያ ቤተሰብ ባይሆኑም መድልኦውን እያዩ ስላደጉ ማስቆም ይፈልጋሉ።

በተለያዩ ግዛቶች ሲዘዋወሩ ይህን አግላይ ልማድ ለመግታት ከባህላዊ መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።

“ሰዎች ተሰባስበው እነዚህን ደንቦች እንዳወጡት ሁሉ እኛም ተሰባስበን መሻር እንችላለን” ሲሉ ጉዟቸውን ይገልጻሉ።

ኢግቦ ውስጥ የባርያ ቤተሰቦች በሁለት ይከፈላሉ። ኦሁ እና ኦሱ ይባላሉ።

ቅድመ አያቶቻቸው በሰዎች የተገዙት ኦሁ፤ ቅድመ አያቶቻቸው በአማልክት የተመሩት ደግሞ ኦሱ ተብለው ይጠራሉ።

በካሊፎርንያ የአፍሪካ ጥናት መምህሩ ኦጎ ንዌክጂ “ኦሱ ከባርነትም የከፋ ነው” ይላሉ።

ኦጎ እንደሚያስረዱት፤ ባርያዎች ከባርነት ቀንበር መላቀቅ ቢችሉም ኦሱ በሚል ለሚመደቡ ሰዎች ግን ይህ አይሠራም። ለልጅ ልጆቻቸውም ይሸጋገራል። ኦሱዎች ላይ የሚደርሰው መገለል ከኦሁ የባሰ ነው።

ኦሁዎች የሚገለሉት በማኅበራዊ የተዛባ አመለካከት ነው። በሌላ በኩል ኦሱዎችን አለማግለል በአማልክት ያስቀጣል ተብሎ ይታመናል።

ፌቨር ልታገባው የነበረው ግለሰብ ቤተሰቦች “ኦሱ ካገባህ ትሞታለህ” ብለው አስፈራርተውት ነበር። እሱም “እንድሞት ትፈልጊያለሽ?” ብሏት እንደነበር ታስታውሳለች።

ሕጉን ማስፈጸም አልተቻለም

የማኅበረሰቡ ፍርሀት መድልኦን የሚቀርፍ ሕግ እንዳይተገበር ምክንያት ሆኗል። 1956 ላይ ኦሁዎች አና ኦሱዎች እንዳይገለሉ በኢግቦ ሕግ አውጪዎች ቢደነገግም ማስፈጸሙ ከባድ ነው።

የካቶሊክ ቄስ አንቶኒ ኦቢና “አንዳንድ ጥንታዊ ልማዶችን ለማስቀረት ሕገ መንግሥት በቂ አይደለም። ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል” ይላሉ።

ኦጎ ሲያስተምሩ ኦሱዎችን በተመለከተ ያሉ ልማዶች ስለሚቀረፉበት መንገድ ይጠቁማሉ። በመቶዎች በሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞች የሚከናወነው ሥራቸው ቀላል አይደለም።

ቢሆንም በየማኅበረሰቡ ያሉ ባህላዊ መሪዎች እኩልነትን እንዲያሰፍኑ የማሳመን ጥረታቸውን እንደቀጠሉ ነው። ትግላቸውን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ “ባህላችንን አንቀይርም” ብለው የሚቃወሟቸውም እንዳሉ ኦጎ ያስረዳሉ።

በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ምን ያህል የባርያ ቤተሰቦች እንዳሉ መረጃ የለም። ባለው መድልኦ ሳቢያ ግጭቶች የሚቀሰቀሱባቸው ቦታዎች አሉ።

አንዳንድ የባርያ ቤተሰቦች የራሳቸው ማኅበርና አስተዳደር ፈጥረዋል። ለምሳሌ ከ13 ዓመት በፊት በሊሞ ግዛት ኦሱዎች ‘ኒንጂ’ ወይም ከአንድ ማህጸን የተባለ ቡድን ተቋቁሟል። የቡድኑ አባላት መካከል ትዳር ይመሠረታል።

ከሀብታም ኦሱዎች የተወለደችው ኦግዲማ “ሰዎች ካንቺ ጥቅም ሲፈልጉ ይመጡና ከኦሱ ጋር ትዳር አንመሠርትም ይላሉ” ትላለች።

ከአሥር ዓመት በፊት የምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት ስትወዳደር መገለል እንደገጠማት ታስታውሳለች። እሷን በመቃወም ፊርማ ሲሰባሰብ ነበር። የዩርባ ተወላጅ የሆኑት የፓርቲዋ መሪም ሊደግፏት አልቻሉም።

በዮሩባ እና ሀውሳ ማኅበረሰቦች የባርያ ቤተሰቦችን ማግለል የተለመደ አይደለም። እንደ ማሊና ሴኔጋል ባሉ አገሮች ግን መድልዎ ይስተዋላል።

ቄስ አንቶኒ እንደሚናገሩት፤ አንዳንድ ከባርያ ቤተሰብ ልጆች ጋር የተጋቡ ሰዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ተከላክለዋል።

የኖሊውድ ሚና

አመለካከቱ እንደ ቺንዋ አቼቤ ባሉ አፍሪካውያን ደራሲያን ሥራዎችም እንደሚንጸባረቅ ኦግዲማ ታምናለች።

‘ቲንግስ ፎል አፓርት’ የመሰሉ መጻሕፍትን የሚያነቡ ናይጄርያውያን ወጣቶች ስለ ኦሱዎች ምን አይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል ትጠይቃለች።

በኢንጉ ግዛት ቄስ የሆኑት አሎይሰስ አግቦ የኖሊውድ ፊልሞች ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብለው ያምናሉ። “መሠረተ ቢስ ብለን ችላ ያልናቸው አመለካከቶች አሁን እውነት መስለው በቴሌቭዥን መርሀ ግብሮች እየመጡ ነው። ባህላችንን እያሳዩ ይመስላቸዋል። ማኅበረሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና አያስቡም” ይላሉ።

እንደ ‘ብላክ ላይቭስ ማተር’ አይነት ለጥቁሮች መብት የሚሟገቱ ንቅናቄዎች የሰውን አመለካከት ይቀይራል ብላ ኦግዲማ ተስፋ ታደርጋለች።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ሁለት ኃይማኖት አንድ ትዳር!