ሕይወት ከመሠረታዊ አቅርቦቶች ውጪ በሆነችው ትግራይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኑሮውን ሱዳን ካርቱም ያደረገው እና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ በቅርቡ መቀለ ለሚገኙ ቤተሰቦቹ የዕለታዊ ፍጆታ መግዣ ገንዘብ መላኩን ይናገራል።
የባንክ አገልግሎት ከተቋረጠ ወራት ወደ ተቆጠረባት መቀለ 40 ሺህ ብር መላክ ማሰቡን ያወቁ እና ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ ግለሰቦች፣ ገንዘቡን ለቤተሰቦቹ ለማድረስ 20 ሺህ 800 ብር እንዲከፍላቸው እንደጠየቁት ለቢቢሲ ገልጿል።
ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ በሕጋዊነት የሚሰራ አንድም የፋይናንስ ተቋም ባይኖርም፣ መቀለ ለሚገኙ ቤተሰቦቹ ገንዘቡን እናደርሳለን ላሉት ግለሰቦች የተጠየቀውን ክፍያ በባንክ ሂሳባቸው ገቢ ማድረጉን ገልጿል።
ይህ ግለሰብ አክሎም ይህንን እድል ያገኙ ሌሎች ሰዎችም በተመሳሳይ መንገድ መላክ ያሰቡትን ገንዘብ ግማሽ ያህል ክፍያ ለአቀባባዮች እየከፈሉ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ያስረዳል።
ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የትግራይ አማፂያን የመቀለ ከተማን እና አብዛኛውን የትግራይ አካባቢ ከተቆጣጠሩ በኋላ ትግራይ ለአስር ወራት ያህል እቀባ ላይ ትገኛለች።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በጀመረው በዚህ ጦርነት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለተወሰኑ ወራቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረው የነበሩ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ዳግም ሙሉ በሙሉ ቆመዋዋል።
'የተራበች ከተማ'
የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ገብራይ ገዛኸኝ ከመስከረም ወር ጀምሮ 'ራሳችን ለራሳችን' [ባዕልና ንባዕልና]' በተሰኘ ፕሮጀክት ዘወትር ማለዳ ዳቦ እና ሻይ ይቀርብላቸዋል።
እኚህ የዕለት እንጀራቸውን ከበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያገኙ አዛውንት ቢቢሲ ቃለመጠይቅ ሲያደርግላቸው ችግራቸውን እና ብስጭታቸውን የገለፁት በዘፈን ነበር።
" ድሮ ኪሮስ አለማየሁ . . . ወላጅ ከልጁ ተለያየ፤ በከፋ ረሃብ ሬሳ መሰለ. . . በአፈሙዝ ሰላሙን አጣ. . . ብሎ ነበር። ዛሬም ይህ ተደገመ" ካሉ በኋላ "የሚላስ የሚቀመስ አጥተን የልጆቻችን ድምጽ ርቆብን እየኖርን ነው" ሲሉ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና ሕይወት እየከፋ መሄዱን ይናገራሉ።
ከጦርነቱ በፊት የመቀለ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ የነበራት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን ከተለያዩ የክልሉ ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች በመጡ ተፈናቃዮች ተጨናንቃለች።
በክልሉ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በመቶ ሺህ ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየትምህርት ቤቱ፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ በአብያተ ክርስትያናት ውስጥ ተጠልለው በገንዘብ እና በየፍጆታ እቃዎች አቅርቦት እጥረት ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ።
አቶ ገብራይ "ረሃቡ ሁሉም ላይ ደርሷል፤ ትልቁም ሆነ ትንሹ ተርቦ ግራ ገብቶት ይገኛል። ገንዘብ፣ መጓጓዣ የለም። በቀን አንዴ በልተን 'ያልፋል' እያልን እንውላለን" ሲሉ የሚገኙበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዓለም ሰላም ፋውንዴሽን ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት፣ በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ በሦስት ክፍል ባሳተሙት ጥናት ውስጥ "ያለውን ተጽዕኖ አልፋችሁ መግባት የምትችሉ ከሆነ ወደ መቀለ እንድትመጡ እንጋብዛችኋለን፤ እንደገባችሁ መጀመሪያ የምታይዋት የተራበች ከተማን ነው" በማለት ያለውን ችግር ገልፀውታል።
ከአምስት ዓመት በፊት ጧሪ እና ተንከባካቢ የሌላቸው አረጋውያን ለማገዝ የተቋቋመው ከራዲዮን የአረጋውያን እርዳታ ድርጅት በአሁኑ ወቅት መቀለ ከተማ ውስጥ ለስደተኛ ሕጻናት እና እናቶች ምግብ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።
በከተማዋ ውስጥ ከቀን ወደ ቀን ለምጽዋት እጃቸውን የሚዘረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንዳለ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አማኑዔል ገብረ ጻድቃን ይገልጻል።
በጦርነቱ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማዋ የመጡ እና በርከት ያሉ ተንከባካቢ ወይንም ደጋፊ የሌላቸው ሕጻናት ጎዳና ላይ ወድቀው እንደሚገኙ ተናግሯል።
"ሁሉም ነገር ተዘግቶ ምግብ እና መድኃኒት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ገጠር እና ሌሎች አካባቢዎችን ይቅር እና መቀለን ብቻ ብንመለከት የከፋ ችግር ውስጥ ናት። ሐብታም የምትለው ደሃ ሆኗል፤ ደሃ የነበረው ደግሞ ከድህነት በታች ወርዶ ከባድ ችግር ውስጥ ይገኛል" ይላል።
ከመስከረም 07/2014 ዓ.ም ጀምሮ የቁርስ ድጋፍ እየሰጠ የሚገኘው ይህ ማኅበር በአሁኑ ጊዜ ከ300 በላይ ተረጂዎች እንዳሉት አማኑኤል ይገልጻል።
መጀመሪያ አካባቢ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ይተጋገዝ የነበረ ቢሆንም እጁ ላይ የነበረውን እየጨረሰ በመምጣቱ ይህ መደጋገፍ መቀነሱን አክሎ ተናግሯል።
"ከተማዋ ውስጥ ከእንባው ጋር የሚታገል፣ በጎዳናዎች ላይ ብቻውን እያወራ የሚሄድ፣ እጆቹን ዘርግቶ የሚለምን፣ በርካታ ሰው ማየት እየተለመደ ነው" ሲል አሁን በከተማዋ ያለውን ሕይወት ለቢቢሲ ገልጿል።
"እስካሁን ሕዝቡ ተስፋ አልቆረጠም" የሚለው አማኑዔል፣ የመቀለ ነዋሪ ካለው ላይ እየሰጣቸው ለከፋ ችግር የተጋለጡትን እንደሚደግፉ ይናገራል።
ትግራይ ውስጥ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈሉ ግለሰብ ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት ከሰኔ 21/2013 ዓ.ም በኋላ ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ "በጣም የሚሰቀጥጥ" እንደሆነ በተለይ ደግሞ ከባድ ውጊያ በተደረገባቸው እና "የኤርትራ ሠራዊት በነበረባቸው ቆላ ተንቤን እምባሰነይቲ፣ ማይ ቅነጣል እና ዕዳጋ ዓርቢን ውስጥ የከፋ ረሃብ አለ" ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ የተነሳ በርከት ያሉ ሰዎች የቤት እቃ፣ ጌጣጌጥ እና አልባሳትን እንዲሁም ቤታቸውን እስከ መሸጥ የደረሱ መኖራቸውን፣ በተጨማሪም ላለፉት ወራት ደመወዝ ያላገኙ መምህራን፣ ሐኪሞች እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች መለመን እንደጀመሩ ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።
በተለያየ ወቅት ይፋ የሆኑ የዓለም ምግብ ድርጅት ሪፖርቶች ሰሜን ምዕራብ፣ ምሥራቅ እና ማዕከላዊ የትግራይ ዞኖች ከፍ ያለ የምግብ እጥረት የታየባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, KERADION
ደመወዝ አልባ የመንግሥት ሠራተኞች
የትግራይ ክልል እርሻ እና ገጠር ልማት ቢሮ በክልሉ ውስጥ ከዘጠኝ ወራት በላይ ደመወዝ ያልተከፈላቸው "220ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች ከባድ ችግር ውስጥ ይገኛሉ" ሲል ገልጾ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የመቀለ ዩኒቨርስቲ ሕክምና ፋኩሊቲ መምህር በበኩሉ ከ7000 በላይ የዩኒቨርስቲው ሠራተኞች ላለፈው አንድ ዓመት ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግሮ ነበር።
"ምንም ምንኳ የፌደራል አካል ብንሆንም የፌደራል መንግሥት ግን በጀት ሊልክልን አልቻለም" ሲልም ቅሬታውን አቅርቦ ነበር።
የትግራይ ቴሌቪዝን የክልሉ ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደባልቀውን ጠቅሶ ባሰራጨው ዘገባ "በቅርብ ጊዜ እርዳታ ካልገባ ከግማሽ በላይ የትግራይ ሕዝብ ያልቃል" ሲል አስጠንቅቀዋ።
"እቀባው እየበረታ በመሄዱ በመጥፋት አፋፍ ላይ እንገኛለን፤ እቀባው እስከ ሚያዚያ 09/2014 ድረስ ከቀጠለ ግማሽ የትግራይ ሕዝብ ያልቃል፤ ብዙዎች በመድኃኒት እጥረት እየሞቱ ነው። ለቤተሰቦቻቸው መሰረታዊ አቅርቦት ማቅረብ ባለመቻላቸው ደግሞ በርካቶች ራሳቸውን እያጠፉ እንዳሉ ሪፖርቶች እደረሱን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ሻማ 30 ብር
የፌደራል መንግሥቱ ለስድስት ወራት ክልሉን ባስተዳደረበት ወቅት ትልልቅ ከተሞች ባንክ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት እና መጓጓዣ ተጀምሮ የነበረው አገልግሎት ዳግም የትግራይ አማፂያን መቀለን ሲቆጣጠሩ ሙሉ በሙሉ ተቋጧል።
ከዚህ ወዲህ በክልሉ የሚገኙ የፋይናንስ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው የገንዘብ እጥረት አጋጥሟል። የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋም ከእጥፍ በላይ ጭማሪ እንዳሳየም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
ክልሉ ከዋናው የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት መስመር ጋር ስለተቆራረጠ መደበኛ እና ያልተቆራረጠ የመብራት አገልግሎት ማግኘት አለመቻሉንም ጨምረው ተናግረዋል።
በርከት ያለ ሰው ሻማ እንደሚጠቀም የሚናገሩት እነዚህ ነዋሪዎች፣ በፊት ሦስት ብር ይገዙት የነበረውን ሻማ አሁን 30 ብር እንደሚከፍሉበት ያስረዳሉ።
በክልሉ በርከት ያለ ገንዘብ በጥቂት ባለሃብቶች እና ነጋዴዎች ካዝና እንደሚገኝ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ክልሉ የሚገቡ ሸቀጦች እና የሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ከእጥፍ በላይ እንደጨመሩ አማኑዔል ይናገራል።
ባለፉት ሳምንታት ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በክልሉ ውስጥ የባንክ፣ ነዳጅ እና የመድኃኒት ችግሮች እንዳሉ በማስታወስ አቅርቦቶች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች አሉ በሚል ወቅሰዋል።
አክለውም "በዚህ ጭንቀት ውስጥ እበለጽጋለሁ ብሎ ማሰብ ወንጀል ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, keradion
ከክልሉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚያመሩ ነዋሪዎች
የህወሓት ሊቀመንበር ባለፈው ወር ላይ በሰጡት መግለጫ "እቀባው ከባድ ነው፤ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፤ ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ ነው ያለው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
"በየወቅቱ ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከምዕራብ ትግራይ የሚመጡ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነው። . . ." በማለት በክልሉ ያለው እቀባ እና ግጭቱ ያስከተለውን ጫና ዘርዝረው ነበር።
እቀባው በትግራይ ክልል ውስጥ የሚፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር እንዳይጨምረው ስጋት እንዳላቸው የሚናገሩት ትግራይ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚሰሩት ግለሰብ ናቸው።
ይህ ግለሰብ አሁንም ወጣቶች ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ከክልሉ እየወጡ ናቸው ብሏል። ". . . በተለይ በደቡብ ትግራይ፣ በራያ ቆቦ እና አፋር አድርገው ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ የሚሄዱ አሉ። በራያ አላማጣ መስመር ብዙ ሰው ከትግራይ እየወጣ ነው። ገንዘብ ከፍለው በደላላ ነው የሚወጡት" ይላል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ምን ይላሉ?
በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሉ የሚገባው የሰብኣዊ እርዳታ አነስተኛ በመሆኑ እና በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ስለሚደናቀፍ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንደተፈጠረ የዓለም አገፍ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ትግራይ ውስጥ ብቻ 4.6 ሚሊዮን ሰዎች፣ ማለትም ከአምስት ሰዎች መካከል አራቱ የምግብ እህል እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውን ይናገራል።
ድርጅቱ አክሎም ከግማሽ በላይ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉም አስታውቋል።
በተጨማሪም የፌደራል መንግሥት እና የህወሓት አማፂያን ወደ ክልሉ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ሲጠይቅ ቆይተዋል።
ወደ ክልሉ ሰብዓዊ እርዳታ ላለመግባቱ ግን ህወሓት አመራሮች እና የፌደራል መንግሥቱ እርስ በእርስ ይወነጃጀላሉ።
ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት እስከ 454ሺህ የሚደርሱ ህጻናት በምግብ እጥረት እንደተጎዱ፣ ከ115 ሺህ ህጻናት ደግሞ በከባድ የምግብ እጥረት እንደተጠቁ አመልክቷል።
አክሎም እስከ 120ሺህ የሚደርሱ ነፍሰጡር እና እንዲሁም ከ25 ሺህ በላይ ከእድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በምግብ እጥረት መጎዳታቸውን ገልጿል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጥር ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ 40 በመቶ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ "ለከባድ የምግብ እትረት" ተጋልጧል ብሏል።
ይህ ሪፖርት 83 በመቶ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ምግብ እንደጨሰና ልመና ላይ ተሰማርተው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እየተመገቡ እንዳሉ ያመለክታል።
በተጨማሪም አሁን በአፋር ክልል በኩል በቀጠው ግጭት የተነሳ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ሚያልፍበት ብቸኛው የሰመራ-አብዓላ መንገድ እንደዘጋው በተደጋጋሚ ተገልጿል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በክልሉ ውስጥ ያላቸው የእርዳታ አቅርቦት እና ነዳጅ ክምችት እንደተሟጠጠ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በመጓጓዣ እና ነዳጅ እጥረት ምክንያት እርዳታቸውን ለመቀነስ እንደተገደዱ አስታውቀዋል።
እስከ መጋቢት 08/2022 (እኤአ) ባለው ጊዜ ውስጥም በአጠቃላይ 600 ሊትር ነዳጅ ብቻ እንደቀራቸው ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ በትግራይ ክልል ያለው እቀባ መቀጠሉ እንደሚያሳስባቸው ገልፀው ነበር።
አክለውም ". . .የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ጨምሮ ሁሉም ወገኖች ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለው ነበር።
የዓለም ማኅበረሰብ በሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆም እንዲሁም በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ተኩስ እንዲያቆሙ እና ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲፈቅዱ ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ ግን የታየ ተጨባጭ ለውጥ የለም።
ክልሉን የሚያስተዳድረው ህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን (ዶ/ር) ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በተዘዋዋሪ ንግግር እየተደረገ ነው ቢሉም ውይይቱ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቶ አልታየም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የመጀመሪያውን ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄደው ብልጽግና ፓርቲ በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚጠቀም ገልጿል።
ይህ ግን ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ መገመት እጅጉን ከባድ ነው።















