"በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የዲፕሎማቶች ቡድን ወደ ዩክሬን እያመራ ነው"

በጦርነት እየተናጠች ባለችው ዩክሬን በእስር ላይ የሚገኙ ስድስት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ለማስለቀቅ በርሊን ከሚገኘው ኤምባሲ የዲፕሎማቶች ቡድን ወደ ዩክሬን እያመራ መሆኑ ተገለጸ።
በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚስዮን መሪ የሆኑት አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ ለቢቢሲ እንደገለፁት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ከኤምባሲው የተውጣጡ የዲፕሎማቶች ቡድን ወደ ዩክሬን ለማምራት ረቡዕ ጠዋት ጉዞ ጀምሯል።
በእስር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች በዩክሬን ጦርነቱ ከመነሳቱ ከስምንት እና ከአምስት ወራት በፊት ወደ አውሮፓ ሕብረት (ሸንገን) አገራት ለመግባት ሲሞክሩ ድንበር ላይ ተይዘው የታሰሩ መሆናቸውን አምባሳደር ተፈሪ ተናግረዋል።
"ተማሪዎቹ ወንጀል ሰርተው የታሰሩ ቢሆንም ለእነርሱ ድጋፍ ለመስጠት እና ሊሴ ፓሴ ተዘጋጅቶ ለማስፈታት እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ዜጎቹን ለማስፈታት ጉዞ የተጀመረው ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም አዲስ አበባ ከሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ መሆኑን አምባሳደሩ አክለዋል።
ተማሪዎቹ ታስረውበት የሚገኘውን እስር ቤት አስተዳዳሪ ረቡዕ ጠዋት በስልክ እንዳነጋገሩ የገለፁት አምባሳደር ተፈሪ "አስፈላጊውን መረጃዎች ይዛችሁ መጥታችሁ ውሰዱ" በማለት ፈቃድ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም ወደ ዩክሬን የተንቀሳቀሰው የዲፕሎማቶች ቡድን እዚያው እስር ቤቱ ድረስ ሄዶ ተማሪዎቹን እንደሚያስፈታ አምባሳደሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህ ውጪ በዩክሬን በትምህርት ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከዩክሬን መውጣታቸውን እንዲሁም ፖላንድና ጀርመን ገብተው የአውሮፓ ሕብረት የሰጠውን የአንድ ዓመት እድል እየተጠቀሙ መሆኑን አመልክተዋል።
"የመኖሪያ ፈቃድም ያገኙ አሉ። ወደ አገር ቤት መመለስ አይፈልጉም። እዚያው ሆነው ትምህርታቸውን መጨረስ ነው የሚፈልጉት" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ቢቢሲ ያነጋገራት በጎ ፈቃደኛ ጦርነቱን ሽሽት ድንበር አቋርጠው የወጡ ተማሪዎች የዕለት ድጋፍ የሚያገኙት በበጎ ፈቃደኞች እርዳታ መሆኑንና ለችግር መዳረጋቸውን ገልጻ ነበር።
ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደሩ በዩክሬንና ፖላንድ ድንበር ድረስ ሄደው ፖላንድ ውስጥ ካሉ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አመራሮች ጋር መነጋገራቸውንና ተማሪዎቹን ለመደገፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አምባሳደሩ አስታውሰዋል።
ኤምባሲው "የዜጎችን መብት ማስከበር፣ ከድንበር እንዲወጡ ማገዝ እንጂ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የእያንዳንዱን ዜጋ የኢምግሬሽን ሂደት አይከታተልም" ያሉት አምባሳደሩ ተማሪዎቹ ጉዳያቸውን በየግላቸው እየጨረሱ ነው ብለዋል።
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለትምህርት ዩክሬን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛው ቁጥር የሞሮኮ ተማሪዎች ሲሆኑ (8,000)፣ ናይጄሪያ (4,000) እና ግብፅ (3,500) ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዩክሬን ውስጥ ይገኙ እንደነበር ቢቢሲ አረጋግጧል።

የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት እና ኢትዮጵያውያን














