"እዚህ ከመኖር ዩክሬን ሄዶ መዋጋት የተሻለ ነው” ናይጄሪያዊ ወዶ ዘማች

ጠመንጃ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ወር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ስትከፍት የ27 ዓመቱ ናይጄሪያዊ ኦታህ አብራሃም ተበሳጭቶ ነበር።

ውጊያው ከሚካሄድበት የጦር ግንባር በ8,700 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘው የናይጄሪያዋ ትልቅ ከተማ ሌጎስ ውስጥ ባለች ትንሽዬ ክፍሉ ሆኖ፤ በሞባይሉ ትዊተር ገጹ ላይ "ወታደሮቹን መቀላል እፈልጋለሁ" በማለት ለመዝመት እንደሚፈልግ ጽፎ ነበር።

ይህ የፍልስፍና ተመራቂ ናይጄሪያዊ በአገሩ፣ በኬንያ፣ በሴኔጋል፣ በደቡብ አፍሪካ እና በአልጄሪያ ካሉ ተመሳሳይ ፍላጎትን ካሳዩ በመቶዎች ከሚቆጠሩ አፍሪካውያን መካከል አንዱ ነው።

ወጣቶቹ ከሩሲያ ጋር ከምትፋለመው ዩክሬን ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት የፈለጉት በከፊል በየአገራቸው ያለውን የጨለመ ተስፋን ለማምለጥ በሚል ነው።

"ጦርነት እንጂ የህጻናት ጨዋታ እንዳልሆነ እናውቃለን" ሲል ለቢቢሲ የተናገረው ኦታህ "ነገር ግን ዩክሬን ውስጥ የሚዋጋ ወታደር እዚህ ካለ ሰው የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው" ይላል።

"ጦርነቱ የሚያበቃ ከሆነ እዚያው እንድቆይ ሊፈቀድልኝ ይችላል፣ በተጨማሪም ጠላትን በመዋጋትም ጀግና እሆናለሁ።"

የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ኩሌባ እንዳሉት ከመላው ዓለም ለዩክሬን ተሰልፈው ለመዋጋት ፈቃደኛ የሆኑ 20,000 ሰዎች ለመመልመል አመልክተዋል።

ይህ ጥያቄ የቀረበው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዓለም አቀፍ ተዋጊዎች ከአገራቸው ጎን ተሰልፈው እንዲፋለሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።

የዩክሬን መንግሥት ለጊዜው የቪዛ ግዴታን በማስቀረት ሕጋዊ ፓስፖርትና ወታደራዊ ሥልጣና ላላቸው ፈቃደኞች መሳሪያና ደሞዝ ለመስጠት ወስኗል። ነገር ግን ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ተዋጊዎቹ ዩክሬን ውስጥ እንዲኖሩ እንደሚፈቀድላቸው ይፋዊ ማረጋገጫ የለም።

በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ነዋሪ የሆነው ኬሬቲ ኡሶሮ እንደሚለው ለዩክሬን በፈቃደኝነት ለመዋጋት የሚፈልገው ለገንዘብ ጥቅም ወይም ዜግነት ለማግኘት አይደለም።

"አሁን ያለኝ ምቹ ሕይወት ነው። ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ፍላጎት ቢኖረኝ ለጦርነት ሳይሆን ለትምህርት መሄድ እችላለሁ" ይላል የ29 ዓመቱ ጠበቃ ኡሶሮ።

"መዝመት የምፈልገው ጉልበተኛን ልክ ማስገባት ነው፤ ለአንዱ ኢፍትሃዊ የሆነ ነገር ለሁሉም ኢፍትሃዊ ነው።"

የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጥሪን ተከትሎ የዩክሬን ዲፕሎማቶችን ልብ በደስታ በሞላ ሁኔታ፣ በርካታ ተስፈኛ በጎ ፈቃደኞች በወታደርነት ለመመልመል አቡጃ ውስጥ ወደሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ አቅንተው ነበር።

ቅጥረኛ ተዋጊዎች ተቀባይነት የላቸውም

አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደ ዩክሬን ሄደው በውጊያ ውስጥ እንዲሳተፉ ስላልፈለጉ ናይጄሪያ ውስጥ ያለው የዩክሬን ኤምባሲን ጨምሮ ሌሎቹም ፊታቸውን ለማዞር ተገደዋል።

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "በየትኛውም የዓለም ክፍል ውስጥ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን መጠቀምን ናይጄሪያ አታበረታታም፣ ለዚህ ተግባርም የሚደረግን ምልመላን አትታገስም" ብሏል።

ናይጄሪያ ውስጥ በሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ውስጥ ባለሥልጣን የሆኑት ቦህዳን ሶልታይስ እንዳሉት፣ አፍሪካውያን በውጊያው እንዲሳተፉ እንደማይከፍሉና ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ወደ አውሮፓ ለመሄድ የሚያስፈልጋቸውን የአውሮፕላን ትኬት እራሳቸው መቁረጥ አለባቸው።

ባለሥልጣኑ "በፈቃደኞች እና በቅጥረኛ ተዋጊዎች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ጠባብ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሩሲያን የሚደግፍ ሰልፍ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ባንጉይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያን የሚደግፍ ሰልፍ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ባንጉይ

ዲፕሎማቱ ጨምረውም በሰጡት ማብራሪያ በፈቃደኝነት ለመዝመት ለመመዝገብ ወደ ኤምባሲያቸው የሚመጡ ሰዎችን እንዲመልሱ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።

ሴኔጋል በበኩሏ ዜጎቿ በጦርነቱ ለመሳተፍ እንዳይመዘገቡ ያስጠነቀቀች ሲሆን፣ የዩክሬን ኤምባሲ በፌስቡክ ገጹ ላይ ለምልመላ ያቀረበው ጥሪ "ሕገወጥ እና በሕግ የሚያስቀጣ" መሆኑን በመግለጽ እንዲያነሳ አዛለች።

የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለዩክሬን ኤምባሲ ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

"አገሬ እንድሄድ አልፈቀደችልኝም። ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመጻፍ ሞክሬያለሁ። መልስ አልሰጡኝም፣ በድጋሚ እሞክራለሁ" ሲል የ28 ዓመቱ አልጄሪያዊ ቤልሃጂ ሃኒ አሚር ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ወደ ዩክሬን መሄድ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን ጦርነቱ በቶሎ እንደሚያበቃ ተስፋ አድርጋሉ።"

በደቡብ አፍሪካ፣ በሞዛምቢክ እና በቦትስዋና የዩክሬን አምባሳደር የሆኑት ሊዩቦቭ አብራቪቶቫ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፈቃደኝነት ለመዋጋት ወይም በሰብአዊ ተግባራት ለመሰማራት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።

ነገር ግን ከየአገራቸው መንግሥታት የሚሰጡ መመሪያዎችን እየጠበቁ በመሆናቸው በሰዎቹ ጥያቄ መሠረት ምላሽ ለመስጠት እንዳልቻሉ አምባሳደሯ አመልክተዋል።

ደቡብ አፍሪካ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ ያላት አገር ናት።

ፈቃደኛ ዓለም አቀፍ ተዋጊዎችን ለመመልመል የሚያግዝ እና በየአገሩ ያሉ ኤምባሲዎች ዝርዝር መረጃ የሚሰራጭበት የዩክሬን ይፋዊ ድረ ገጽም በአፍሪካ አገራት ያሉ ኤምባሲዎቹን ዝርዝር አንስቷል።

ፕሬንስ ወጣት ሳለ ሩሲያ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Prince Nkem Nduche

የምስሉ መግለጫ, ከዓመታት በፊት ሩሲያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደው ፕሪንስ (ከግራ) ዩክሬን ውስጥ ለመዋጋት ፍላጎት አለው

'የሩሲያ ወንድሞች'

የተባበሩት መንግሥታት የዩክሬንን ወረራን ለማውገዝ ባካሄደው ስብሰባ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት 17ቱ ድምጻቸውን አቅበዋል። ከእነዚህ አገራት መካከል አልጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል። አገራቱ ሩሲያን መቃወም ባለመፈለጋቸው ይጠቀሳሉ።

በመሆኑም ሩሲያ በአፍሪካ ድጋፍ የላትም ማለት አይቻልም።

ሩሲያ እንደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያ፣ ማሊ እና ሱዳን ያሉ አገራት እስላማዊ ታጣቂዎችን እንዲዋጉ በመርዳት በአህጉሪቱ ውስጥ በተለይ በወታደራዊ ኃይል ያላትን ተጽዕኖ አስፍታለች።

ጦርነቱን ተከትሎም ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የመጡ ወታደሮች "የሩሲያ ወንድሞቻቸውን" ለመቀላቀል ቃል ሲገቡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ታይቷል።

ይሁን እንጂ ቢቢሲ የዚህን ተንቀሳቃሽ ምሥል ምንጭ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም። በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በቢቢሲ የተጠየቁ የመንግሥት ባለሥልጣንም ምልሽ አልሰጡም።

ባለፈው አርብ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ከመካከለኛው ምሥራቅ የተውጣጡ ከ16 ሺህ በላይ ተዋጊዎች ከሩሲያ ጦር ጋር በመሆን ለመዋጋት ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር። ይህ ቁጥር ግን ከሰሜን አፍሪካ የሚመጡትን የሚጨምር ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ መንግሥታት የዜጎቻቸውን ምልመላ እየተከላከሉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ወደ ጦር ግንባር የዘመተ ስለመኖሩ ግልጽ መረጃ የለም። የውጭ በጎ ፈቃደኞችን የሚመዘግቡ የዩክሬን ባለሥልጣን ግን አንድም አፍሪካዊ ዩክሬን አለመድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አዝኛለሁ"

ዴቪድ ኦሳጌ አዴሌኬ በናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ኦዮ ግዛት ነዋሪ ነው።

እንደ ዴቪድ ላሉ አንዳንድ ሰዎች መዝመት አለመቻላቸው የሚጎዳ ነው።

ለቀይ መስቀል የአደጋ ጊዜ የነፍስ አድን ሠራተኛ ሆኖ ሲሰራ የነበረው የ21 ዓመቱ ወጣት፣ ለተዋጊነት ለመመዝገብ የድጋፍ ደብዳቤን ጨምሮ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሰባሰብ ሲዘጋጅ ነበር።

"መረጃዎቹን ለመሰብሰብ በቀጥታ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ነበር ያመራሁት" ሲል ለመመዝገብ ከወንጀል ነጻ መሆኑን የሚያመልክት ማስረጃ ማቅረብ አንደኛው መስፈርት እንደነበር ያስረዳል።

ይሁን እንጂ ለዩክሬን ኤምባሲ ለላከው የኢሜይል መልዕክት ምላሽ እኛን አፍሪካውያንን እንደማይወስዱ በመስማቴ ቅር ብሎኛል ብሏል።

ዴቪድ ወደ ዩክሬን ድንበር የሚያደርሱትን ሌሎች አማራጮች እያማተረ ነው።

"በናይጄሪያ በሚገኘው የፖላንድ ኤምባሲ ቃለ መጠይቅ ተደርጎልኛል " ብሏል።

እዚያው በአቡጃ በዩክሬን ኤምባሲ ውስጥ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ፕሪንስ ንከም ዱቼ ስለ ዩክሬን ሁኔታ የተሻለ እውቀት አለው።

ፕሪንስ ወጣት እያለ በሩሲያ የተወሰነ ጊዜ አሳልፏል። ሁለት ዜግነትም አለው። በሩሲያ የጦር አካዳሚ ውስጥም በአባልነት ተመዝግቦ ሰልጥኗል። ቢሆንም ግን በአንድ ወቅት በአሜሪካ ኤምባሲ አካባቢ ከታየ በኋላ ሰላይ ነው ተብሎ ለአጭር ጊዜ ታስሮ ነበር።

ከዚያም ከሰባት ዓመት በፊት በዩክሬን በኩል አድጎ ከአገሪቱ መውጣት ችሏል። "አሁን ግን ምንም እንኳን መሆን ባይኖርበትም፤ በደስታ ከሩሲያ ጋር እዋጋለሁ" ብሏል።

"በራሴ መሄድ እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የናይጄሪያ መንግሥት መሄድ አትችሉም ብሏል። ይህንን አከብራለሁ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

line

ስለጦርነቱ ተጨማሪ ዘገባዎች

line