በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የምግብ ዋጋ ጣራ እንደሚነካ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለማችን ግዙፉ የምግብ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ አለቃ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የምግብ ዋጋ ጣራ እንደሚነካ ተናገሩ።
ያራ ኢንተርናሽናል የተሰኘውና በ60 የዓለማችን ሃገራት የሚንቀሳቀሰው ድርጅት ከሩሲያ እጅግ ብዙ የምግብ ጥሬ ዕቃ ይገዛል።
የማዳበሪያ ዋጋ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት እንዲሁም ተወዶ ነበር። የያራ አለቃ ስቬይን ቶር ሆልስተር እንዳስጠነቀቁት ሁኔታው እየከፋ ሊሄድ ይችላል።
"ሁኔታዎች በየሰዓቱ እየተቀያየሩ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሰጀመር ከጦርነቱ በፊት እንኳ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ነበርን። አሁን የምግብ ማዳበሪያ በፍጥነት መጓጓዝ በነበረበት ወቅት የአቅርቦት ሰንሰለቱ እክል ሲያጋጥመው ደግሞ ሁኔታዎች ይብስ ይከፋሉ።"
ሩሲያና ዩክሬን በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የግብርና ምርቶች አምራቾች ናቸው።
ሩሲያ ከግብርና ምርቶች ባለፈ ለማዳበሪያ እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ፖታሽና ፎስፌት የተሰኙ ነጥረ ነገሮች በገፍ የምታመርት ሃገር ናት።
"ከግማሽ በላይ የዓለም ሕዝብ ምግብ የሚያገኘው በማዳበሪያዎች ምክንያት ነው። ይህ ማዳበሪያ ከእርሻ ሥፍራ ከጠፋ ምርት 50 በመቶ ቀነሰ ማለት ነው" ይላሉ ሆልስተር።
ኪየቭ የሚገኘው የያራ ኢንተርናሽናል ቢሮ በሚሳዔል ቢመታም አስራ አንዱም የድርጅቱ ሠራተኞች አልተጎዱም።
መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገው ይህ ድርጅት ምንም እንኳ ሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት ቀጥተኛ ጉዳት ባይደርስበትም ምርትን ማጓጓዝ ግን እንደከበደ ኃላፊው ይናገራሉ።
ኃላፊው ለቢቢሲ ድምፃቸውን ከመስጠታቸው ከአንድ ሰዓት በፊት ሩሲያ የማዳበሪያ ምርት እንዲቆም አዛለች።
ኃላፊው እንደሚሉት አውሮፓ ውስጥ ምግብ ለማምረት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ግብዓቶች ከሩብ በላይ የሚመጣው ከሩሲያ ነው።
"እኛ ባለን አጭር ሰዓት ሌላ ምንጭ ለማግኘት የተቻለንን ሁሉ እያደርግን ነው" ይላሉ።
ተንታኞች እንሚሉት ማዳበሪያ የለም ማለት ገበሬዎች ብዙ ወጭና ትንሽ ምርት ሆነባቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ የምግብ ዋጋ የሚያንር ነው።
የማዳበሪያ ንጥረ ነገር ብቻ አይደለም በዚህ ጦርነት ምክንያት እክል ያጋጠመው።
ሌላኛው የማዳበሪያ ቁስ አሞኒያ የሚባለው ሲሆን ይህንን ለማምረት ደግሞ በርካታ የተፈጥሮ ጋዝ ያስፈልጋል። ያራ ኢንተርናሽናል አውሮፓ ውስጥ ይህንነ ለማምረት በሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ ጥገኛ ነው።
የምግብ ማጓጓዝ ዋጋ መጨመር፣ ቤላሩስ ላይ የተጣለውን ማዕቀብና የአየር ንብረት ለውጥ ባለፈው ዓመት የማዳበሪያ ዋጋን ከሰቀሉ ምክንያቶች መካከል ነበሩ።
ኩባንያው አሁን በየቀኑ የሚከሰቱ ጉዳዮችን እየተከታተለ መሆኑን ጠቁሞ ሁኔታው እየከፋ ሲመጣ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው ብሏል።
የያራ ኢንተርናሽናል አለቃ ወደፊት ዓለም ከሩሲያ ጥገኝነት መላቀቅ አለባት ይላሉ።
"በአንድ በኩል ለግብርና ምርት ስንል የማዳበሪያ ምርት እንሻለን። በሌላ በኩል ሩሲያ ዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ እናወግዛለን። ይህ እውነት ለመናገር ከሁለት አንድ እንደማጣት ነው።"
የድርጅቱ ዋን ሥራ አስፈፃሚ የዩክሬንን ጦርነት "እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" ሲሉ ይገልፁታል።
ይህ ጦርነት ባላደጉ ሃገራት የምግብ አቅርቦትን የበለጠ እንደሚጎዳው ኃላፊው ይናገራሉ።
"ባለፉት ሁለት ዓመታት 500 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች እየራባቸው ወደ አልጋቸው አንደሚሄዱ ሰምተናል። አሁን ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ከባድ ነው።"












