በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በ13 ዓመት ያልታየ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የነዳጅ ዋጋ ከፈረንጆቹ 2008 ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጭማሪ አሳየ፡፡
ይህ የሆነው የሩሲያና ዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካና አጋሮቿ በሩሲያ ነዳጅ አቅርቦት ላይ እቀባ ለመጣል ንግግር መጀመራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ብሬንት ክሩድን መሠረት ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው አሁን በአማካይ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 139 ደርሷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ተከትሎ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር፡፡
በመላው ዓለም በበርካታ አገራት የዚህ ነዳጅ ዋጋ መግነን ያመጣውን ተጽእኖ በስፋት እየታየ ይገኛል፡፡
በኢሲያ ዛሬ ሰኞ የስቶክ ማርኬት ያሽቆለቆለ ነው፡፡
ትናንት እሑድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስተዳደራቸው ከአጋር አገሮች ጋር በሩሲያ ነዳጅ ላይ እቀባ ለማድረግ ንግግር ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በኋላ ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ የሩሲያ ነዳጅን ላለመቀበል የሕግ ማእቀፍ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለዩክሬን ደግሞ የ10 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ለማድረግም ኮንግረስ ውሳኔ ያሳልፋል ብለዋል፡፡
ፒሎሲ ጨምረው እንዳሉት ሩሲያን ከዓለም ገበያ ለመነጠል ሌሎች የሕግ ማእቀፎች እየተፈተሹ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ይህ የሆነው አሜሪካ እና አጋሮቿ ዩክሬንን ለመደገፍ በቂ ድጋፍ አላደረጉም የሚል ትችት እያየለ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
በሩሲያ ላይ የሚጣለው የነዳጅ ማዕቀብ በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ሁነኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡
አንድ የኃይል አቅርቦት ጉዳዮች ተንታኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ አሜሪካ የሩሲያ ነዳጅን ወደ አገሯ ላለማሰገባት እቀባ የመጣል አቅም ቢኖራትም አውሮጳዊያን ግን ህመሙ ይሰማቸዋል ብለዋል፡፡
ፑቲን በተለይ የጋስ ሥርጭትን ለአውሮጳ እንዳይደርስ ሲያደርጉ በርካታ የአውሮጳ አገራት ችግር ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም ይላሉ እኚሁ ተንታኝ፡፡
ይህ የሩሲያ ወረራ ከተጀመረ ወዲህ የነዳጅ ገበያ መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ20 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በአሜሪካም የፔትሮል ዋጋ በ11 ከመቶ መጨመሩን የአሜሪካ አውቶሞቢል ማኅበር አስታውቋል፡፡
በዩኬ ደግሞ በአማካይ የነዳጅ ዋጋ በ1.50 ፓውንድ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ትናንት እሑድ ሼል ኩባንያ የሩሲያን ድፍድፍ ነዳጅ መግዛቱን እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል፡፡
ኩባንያው እንዳለው አሁን ባለው ሁኔታ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቱ ቀላል ውሳኔ እንዳልሆነ አብራርቶ ሆኖም ግን ያን ከማድረግ ውጭ አማራጭ እንዳልነበረ ገልጧል፡፡
ሼል ይህን በማድረጉ ውግዘት እየደረሰበት ሲሆን የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትዊተር ሰሌዳቸው "የሩሲያ ነዳጅ የዩክሬናዊያንን ደም ደም አይሸትህም ወይ?" ሲሉ የሰላ ትችት አኑረዋል፡፡












