ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ያንዣበባቸው ሩሲያውን ባለጸጎች የትኞቹ ናቸው?

ቭላድሚር ፑቲንና ሮማን አብራሞቪች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ ዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት የዩናይትድ ኪንግደም ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ሰዎች ናቸው በሚባሉት ቢሊየነሮች ላይ ከባድ ማዕቀብ በመጣል ምላሽ ሰጥተዋል።

በተለይ ክሬሚያን በሃይል ወደ ሩሲያ ከቀላቀሉ በኋላ ፑቲን አጋሮቻቸው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት ሃገሮች እርምጃዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለዓመታት አስጠንቅቀዋል።

ጥቂቶቹ ምክሩን ተቀብለው በሩስያ ብቻ ኢንቨስት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ ገንዘባቸውን የእግር ኳስ ክለቦችን ጨምሮ በተለየዩ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ላይ ገንዘባቸውን አፍስሰዋል።

አሁን እጅግ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕቀቦቹን ለማምለጥና ንብረታቸውን ለመያዝ በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ባለጠጎች መካከል ስለአንዳንዶቹ የምናውቀው እነሆ።

አሊሸር ኡስማኖቭ

ግምታዊ ሃብት፡ 17.6 ቢሊዮን ዶላር

ማዕቀብ የተጣለባቸው በአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ

ከፑቲን ተወዳጅ ባለጠጎች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አሊሸር ኡስማኖቭ በ17.6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት እንዳላቸው ፎርብስ ዘግቧል። የቀድሞውን ፕሮፌሽናል ፌንሰር (በጎራዴ መሳይ መሳሪያ የሚደረግ የውድድር ዓይነት መሆኑን ልብ ይሏል) ፑቲን የንግድ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ የሚረዳው "ነጋዴው-ባለስልጣን" ተብሎ የአውሮፓ ህብረት ይገልፃል።

ኡዝቤኪስታን (የሶቪየት ህብረት አካል እያለች) የተወለዱት ባለሃብቱ ዩኤስኤም ሆልዲንግስ የተባለ በማዕድንና በቴሌኮም የሚሠራ ግዙፍ ኩባንያ ያስተዳድራሉ። ከእነዚህ አንዱ ሜጋፎን የተባለው ሁለተኛው የሩሲያ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ነው።

የአውሮፓ ህብረት የካቲት 28 ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል። አሜሪካ እና እንግሊዝም ተመሳሳይ እርምጃ ወሰዱ። ማዕቀቡን ኢ-ፍትሃዊ ነው ያሉት ባለጠጋው የቀረበባቸውን ክሶች በሙሉ ሃሰት ሲሉ አጣጥለዋል።

ከዩኤስኤም ሆልዲንግስ ከ 50 በመቶ በታች የሆነ ድርሻ ስላላቸው የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብን እንደማይነካቸው ተስፋ ያደረጉ ይመስላል። በእናቱ ስም ዲልባር ተብሎ የተሰየመው ቅንጡ መርከብ በሃምቡርግ ጥገና እየተደረገለት ሲሆን የመወረስ አደጋም ተጋርጦበታል።

በእንግሊዝ ያላቸው ዋና ዋና ኢንቨስትመንቶች ንብረት ናቸው። በለንደን የቢችዉድ ሃውስ በ65 ሚሊዮን ፓውንድ ከሚገመተው ቤት በተጨማሪ ከከተማዋ መውጫም ሌላ ግዙፍ ቤት አላቸው። ሁለቱም ቤቶች በዩኬ ባለስልጣናት ታግደዋል።

የቢዝነስ አጋሩ ፋርሃድ ሞሺሪ የኤቨርተን ባለቤት ናቸው። የኡስማኖቭ ኩባንያዎች ዩኤስኤም፣ ሜጋፎን እና ዮታ የክለቡ ቁልፍ ስፖንሰሮች ሲሆኑ የባለሃብቱ ተሳትፎ የበለጠ ቅርብ እንደነበር ጠቋሚ ናቸው። ኤቨርተን የስፖንሰርሺፕ ስምምነቱን ያቋረጠ ሲሆን ሞሺሪም የዩኤስኤም የቦርድ አባልነቱን ለቀዋል።

ሮማን አብራሞቪች

ግምታዊ ሃብት፡ 12.4 ቢሊዮን ዶላር

የተጣለ ማዕቀብ: የለም

በእግር ኳስ ክለባቸው ቼልሲ አስደናቂ ስኬት ምክንያት ከፍተኛ ዕውቅና ላይ ከሚገኙት የሩሲያ ቢሊየነሮች አንዱ ሮማን አብራሞቪች ናቸው። ምናልባትም ከሌሎች የፑቲን አጋሮች ያነሰ ተፅእኖ ስላላቸው ነው በሚል ምክንያት እስካሁን እገዳ አላጋጠማቸውም።

በክሬምሊን ያላቸው ተደማጭነትም ብዙ አከራካሪ ነው። አንዳንዶች የፕሬዚዳንት ፑቲን ትዕግስት ገጥሟቸው ነው ሲሉ ሌሎች ግንኙነቱ የበለጠ ያቀርቡታል።

አብራሞቪች ከፑቲን ወይም ከክሬምሊን ጋር የጠበቀ ግንኙነት የለኝም ሲሉ አጥብቀው ይገልጻሉ። ማዕቀብ ከመጣ ግን 12.4 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው ሃብታቸው ለአደጋ ይጋለጣል። ረቡዕ ዕለት ቼልሲን በሦስት ቢሊዮን ፓውንድ ለመሸጥ እንደሚፈልግ አሳወቁ። በለንደን ኬንሲንግተን ፓላስ ጋርደንስ የሚገኘውና 150 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያወጣው ቤትም ለሽያጭ መቅረቡ ተነግሯል።

አብራሞቪች ገንዘቡን በ1990ዎቹ ያፈሩ ሲሆን በቦሪስ የልሲን የፕሬዚዳንትነት ዘመን ከነበሩ የመጀመሪያዎቹ ባለጠጋዎች አንዱ ነበሩ። ትልቁ ለውጥም ሲብኔፍት የተባለውን የነዳጅ ኩባንያ በአነስተኛ ዋጋ መግዛታቸው ነው። ከንብረቶቻቸው መካከል ኤክሊፕስ የተሰኘው በዓለም ሦስተኛው ረዥሙ ጀልባ እና ሌላው ውድ መሆኑ የተነገረለት ሶላሪስ የተሰኘው ጀልባም ይገኝበታል።

ባለሃብቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከእንግሊዝ መውጣት መጀመራቸው ይነገራል። በአውሮፓውያኑ 2018 የእንግሊዝ ቪዛቸውን ለማደስ አላመለክትም ያሉ ሲሆን በምትኩ አዲስ ያገኙትን የእስራኤል ፓስፖርት ለንደንን ለመጎብኘት ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ቀደም ሲል ቼልሲ በሜዳው የየሚያደርገው ጨዋታ የማያመልጣቸው አብራሞቪች አሁን እምብዛም በስታምፎርድ ብሪጅ ሲታደሙ አይታይም።

ኦሌግ ዴሪፓስካ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Kremlin/EPA

የምስሉ መግለጫ, ኦሌግ ዴሪፓስካ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር

ኦሌግ ዴሪፓስካ

ግምታዊ ሃብት፡ 3 ቢሊዮን ዶላር

ማዕቀብ የተጣለባቸው በአሜሪካ

ፕሬዝዳንት ፑቲን ወደ ስልጣን ሲመጡ ኦሌግ ዴሪፓክሳ እጅግ ባለጠጋ ነበሩ። ሃብታቸው 28 ቢሊየን ዶላር አካባቢ ደርሶ ነበር። አሁን ግን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንዳላቸው ይገመታል።

ሃብት የሰበሰቡት በ1990ዎቹ እንደሆነ ይነገራል። በተለይም በሉሚኒየም ኢንዱስትሪ ውስጥ የበላይ መሆናቸው ቀድሞ ይጠቀሳል። ዩናይትድ ስቴትስ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሙስና፣ ቅሚያና ማጭበርበር ውስጥ ተሳትፈዋል ብላ ትከሳለች። "አንድ ነጋዴ እንዲገደል አዟል። ከሩሲያ የተደራጀ የወንጀል ቡድን ጋርም ግንኙነት እንዳለው" ክሱ ያክላል። እሳቸው ሁሉንም ክሱን ይክዳሉ።

እአአ በ2008ቱ የገንዘብ ቀውስ ወቅት ክፉኛ በመክሰራቸውም የፑቲንን ድጋፍ አስፈልጓቸዋል። ፕሬዝዳንት ፑቲን እአአ በ 2009 ብዕር እንደሰረቁ በአደባባይ ገልጸው አዋርደዋቸዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለፕሬዝዳንቱ መስራት የጀመሩ ሲሆን እንደ ሙለር ዘገባ (ሩሲያ በ 2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ መግባት ዙሪያ ተደረገ የአሜሪካ ምርመራ ነው) ከሆነ ከፕሬዚዳንቱ ጋር "በቅርብ የተቆራኙ" ናቸው።

በለንደን የአክሲዮን ገበያ ላይ የሚገኘውን ኤን+ ግሩፕ የተባለ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ብረታ ብረት ኩባንያ አቋቋሙ። እአአ በ2018 የአሜሪካ ማዕቀብ ሲጣልባቸው የአክሲዮን ድርሻቸውን ከ50 በመቶ በታች ዝቅ አድርገዋል። ከባለሃብቱ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ቤዚክ ኤለመንት ማዕቀቡን "መሠረተ ቢስ፣ አስቂኝ እና የማይረባ" ሲሉ መግለጫውን አውጥቷል።

ከብዙዎቹ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ባለጠጎች በተቃራኒ ዴሪፓስካ ስለ ጦርነቱተናግረዋል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሠላም ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። "ድርድሩ በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት!" ብለው ጽፈዋል።

ኢጎር ሴቺን

ግምታዊ ሃብት፡ አይታወቅም

ማዕቀብ የተጣለባቸው በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት

ኢጎር ሴቺን ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ያላቸው ግንኙነት ረዥም እና ጥልቅ ነው ያለው የአውሮፓ ህብረት የካቲት 28 ማዕቀብ ጥሎባቸዋል። ባለጠጋው ከፑቲን በጣም ታማኝ እና የቅርብ አማካሪዎች አንዱ ሲሆኑ የግል ጓደኛ መሆናቸው ይነገራል። ሁለቱ ግለሰቦች በየቀኑ እንደሚገናኙ ይገመታል።

ለውጡ የተገኘው ተፎካካሪዎቸን ወደ ጎን በመግፋት ሲሆን በሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዳርት ቫደር በሚል ቅጽል ስም ይታወቃሉ። እአአ በ 2008 የተለቀቀው የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ "ጥላ የሆነ ግለሰብ ምናልባትም ብህእወት የሌለ ሊሆን ይችላል። ክሬምሊን ፍርሃትን ለመፍጠር የፈጠረው ምናባዊ ተረት ነው እተባለ እንደሚቀለድም" ጽፏል። አሜሪካ እአአ በ 2014 ዩስ ማዕቀብ የጣለችባቸው ሲሆን ይህንንም "ፍፁም ፍትሃዊ ያልሆነ እና ህገ-ወጥ" ብለው ተከራክረዋል። ተጨማሪ አዲስ ማዕቀብ የካቲት 24 እንደተጣለባቸው አስታውቀዋል።

ሴቺን በፖለቲካ እና በቢዝነስ ውስጥ ሥራ በመቀያየር አሳልፈዋል። አንዳንዴም በሁለቱም ዘረፍ ከፍተኛ ኃላፊነቶች በተመሳሳይ ጊዜ ይዘዋል። ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። አሁን የሃገሪቱን ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ሮስኔፍትን ይመራሉ።

ሴቺን በ1990ዎቹ በሴንት ፒተርስበርግ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከፑቲን ጋር ሠርተዋል። በጣም በሚፈራው የኬጂቢ የስለላ ድርጅት ውስጥ እንደነበሩ በሰፊው ቢታመንም በግልፅ አምነው አያውቁም።

መቀመጫውን ሩሲያ ያደረጉት ሴቺን ምን ያህል ገንዘብ እንዳላቸው ማንም አያውቅም። ፈረንሳይ አሞር ቬሮ የተባለችውን ውድ ጀልባ ይዛለች። ምክንያት የተባለው ደግሞ ሁለተኛ ሚስታቸው ኦልጋ ሴቺና ከዚህችው ጀልባ ብዙ ፎቶዎችን በመልቀቋ በተፈጠረ ጥርጣሬ ነው።

ከዚህ ባለፈ በቀላሉ ሊጋለጥ የሚችል ትልቅ ሃብት በባህር ማዶ እንዳላቸው እና ተጨማሪ ንብረቶቻቸውን ለማግኘት እና ለማገድ ከባድ ሊሆን ይችላል።

ኢጎር ሴቺን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሌክሲ ሚለር

ግምታዊ ሃብት፡ አይታወቅም

ማዕቀብ የተጣለባቸው በአሜሪካ

አሌክሲ ሚለር ሌላኛው የቭላድሚር ፑቲን የቀድሞ ጓደኛ ናቸው። እሳቸውም በ 1990 ዎቹ በሴንት ፒተርስበርግ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ውስጥ የሚስተር ፑቲን ምክትል ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ለፕሬዚዳንቱ ታማኝ በመሆን ሥራቸውን ገንብተዋል።

እአአ ከ2001 ጀምሮ ትልቁን የመንግስት የነዳጅ ኩባንያን ጋዝፕሮም ሲመሩ ቆይተዋል። ሹመቱ አስገራሚ ሲሆን የቀድሞ አለቃቸውን ትዕዛዝ እየፈፀሙ ነው ተብሎም በብዙዎች ዘንድ ተገምቷል። በሞስኮ የአሜሪካ አምባሰደር እአአ በ 2009 ጋዝፕሮምን "ውጤታማ ያልሆነ፣ በፖለቲካ የሚመራ እና በሙስና የተዘፈቀ" ሲሉ ገልጸውታል።

ሚለር እአአ በ 2014 ክራይሚያ ወደ ሩሲያ ከተቀላቀለች በኋላ ማዕቀብ አልተጣለባቸውም ነበር። እአአ በ 2018 በአሜሪካ የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ ሲካተቱ ግን ኩራት ይሰማኛል ብለዋል ። "በመጀመሪያው ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቴ እንዲያውም አንዳንድ ጥርጣሬዎች ነበሩኝ። ምናልባት የሆነ ችግር ተከስቶ ይሆን? ግን በመጨረሻ ተካትቻለሁ።ይህም ሁሉንም በትክክል እየሠራን ነው ማለት ነው" ብለዋል።

ከሩሲያ ውጭ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ ንብረቶች የሌላቸው ሲሆን ስለ ሃብታቸው ምንም መረጃ የለም።

አሌክሲ ሚለር ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Kremlin/EPA

የምስሉ መግለጫ, አሌክሲ ሚለር ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር

ፒዮትር አቨን እና ሚካሂል ፍሪድማን

የአቨን ግምታዊ ሃብት፡ 4.8 ቢሊዮን ዶላር

የፍሪድማን ግምታዊ ሃብት፡ 12.6 ቢሊዮን ዶላር

ማዕቀብ የተጣለባቸው በአውሮፓ ህብረት

የአውሮፓ ህብረት ፒዮትር አቨን ከፕሬዚዳንት ፑቲን የቅርብ ባለጠጎች አንዱ እንደሆኑ ይገልጻል። ሚካሂል ፍሪድማንን ደግሞ የፑቲንን የቅርብ አገልጋይ እንደሆኑ ይገልፃል። ሁለቱ ሰዎች በጋራ በሩሲያ ውስጥ ትልቁን የግል ባንክ የሆነውን አልፋ-ባንክ መሠረቱ።

የሙለር ዘገባ እንደሚገልጸው አቨን በክሬምሊን እየተገኙ በዓመት አራት ጊዜ ከፑቲን ጋር ተገናኝተው ይነጋገራሉ። "ፑቲን በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት ያቀረቧቸው ማናቸውንም ጥቆማዎች ወይም ትችቶች የተረዱት መመሪያዎች በመሆናቸው አቬን ትዕዛዝ ካልተከተሉ መዘዝ ይኖረዋል" ብሏል።

እአአ በ2016 ሃብታቸው ከወደፊት ማዕቀቦች እንዲጠብቁ በፑቲን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የአውሮፓ ህበረትን ማዕቀብ ተከትሎ በዚህ ሳምንት ሁለቱ ግለሰቦች ከ10 ዓመታት በፊት ከመሰረቱትና መቀመጫውን ለንደን ካደረገው ሌተርዋን የኢንቨስትመንት ቡድን ኃላፊነታቸውን ለቀዋል። አቨን በለንደን የሮያል ጥበባት አካዳሚ ከባለአደራ ኃላፊነታቸውም ተነስተዋል።

ሁለቱ ባላሃብቶች "እነዚህን ማዕቀቦች ለመጣል አስመሳይ እና መሠረተ ቢስ የሆነውን ክስ ለመቀልበስ ጠንክረ ባገኟቸው መንገዶች እንደሚሠሩ" ተናግረዋል.

ፍሪድማን በ12 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት አላቸው ተብሎ ይታሰባል። መኖሪያቸውን ለንደን ያደረጉ ሲሆን በሰሜን ለንደን የሚገኘው አትሎን ሃውስ እአአ በ2016 ሲገዙ 65 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍለውበታል።

ማክሰኞ በለንደን በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዩክሬን ጦርነት "አሳዛኝ" ቢሆንም ክሬምሊንን በቀጥታ አላወገዙም። ይህን ማድረግ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን የሥራ ዋስትናን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለዋል።