ሩሲያ እና የክሬን፡ የሩሲያ ጦር ለምን ኪዬቭን አስካሁን አልተቆጣጠረም? የሳምንቱ ቅኝት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ ሳምንት ያለፈው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከባድ ውደመትን አስከትሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳለው ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከዩክሬን ወጥተው ወደ አጎራባች አገራት ተሰደዋል።
የሩሲያ ኃይሎች በርካታ የዩክሬን ከተሞችን በከባድ መሳሪያ እያጠቁ ሲሆን የተወሰኑትንም በቁጥጥራቸው ስር አስገብተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የዩክሬን ቁልፍ የወደብ ከተማ ኬርሶን በፑቲን እጅ ወድቃለች።
ባለፉት ቀናት ውስጥ ዋና ከተማዋ ኪዬቭን ጨምሮ ኬርኪቭ፣ ቸርሰን፣ ሌቪቭ፣ ሉሃንስክ፣ ፖልታቫና ማሪዮፖል በሚሳኤል ተደብድበዋል።
ይሁንና ይህ ብዙ አላነጋገረም። ላለፉት ቀናት ያለና የነበረ ስለሆነ።
ይልቅ እያነጋገረ ያለው እስከ አፍንጫቸው የታጠቁት የፑቲን ወታደሮች እንዴት ዩክሬንን ለመጨበጥ ዘገዩ? የሚለው ነው።
በእርግጥ ኪዬቭ እስከዛሬ እንዴት ላትያዝ ቻለች? በዩክሬን ጥንካሬ ወይስ ሌላ?
ይህ ቁልፍ ጥያቄ ነው።
ምክንያቱም የፑቲን ወታደሮችና ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ከኪዬቭ ወጣ ብሎ ባለ ጎዳና መሰለፋቸው የተዘገበው ከቀናት በፊት ነበር።
የእነዚህ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና ወታደሮች ሰልፍ በኪሎ ሜትር ሲመተር ከ60 ኪሎ ሜትር ያልፋል።
ይህ ማለት ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ አልፎ እንደማለት ነው።
ይህን የሚያህል ሠራዊት፣ ያውም ስንቅና ትጥቅ ጎደለብኝ የማይል፣ ያውም ብረት ለበስ እንዴት እስከ ዛሬ ኪዬቭ ደጅ ላይ ቆሞ ቀረ? እንዴት ዋና ከተማዋ መግባት ተሳነው?
የሩሲያ ባላንጣ አሜሪካ ለዚህ መልሳ አላት።
የሩሲያ ወታደሮች ባሉበት ቆመው የቀሩት በነዳጅና በምግብ እጥረት እንደሆነ ደርሼበታለሁ ብላለች ዋሺንግተን።
በዚህ ጉዳይ አሜሪካንን አለማመን ይከብዳል። ምክንያቱም የፑቲን ወታደሮች ከኪዬቭ ደጅ መሰለፋቸውን በሳተላይት አጮልቃ ለዓለም የነገረችው እሷው መሆኗ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጦርነቱ በተጀመረ በሳምንት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዩክሬናዊያን ከአገር ተሰደዋል። ይህ የማይታመን ነው።
የፈራረሰችው ሶሪያ ራሷ እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ መንፈቅ ዓመት ወስዶባት ነበር። ይሁንና አሃዙ የወጣው ከተባበሩት መንግሥታት ስለሆነ ቅቡልነቱ አሌ አይባልም።
እንዲህ ዓይነቱ በአጭር ጊዜ ያጋጠመ የሰዎች ስደት በአውሮፓ ታሪክ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ይሁንና ዩክሬን ከአገር ለመውጣት በሚጣጣሩ ጥቁር ስደተኞች ላይ ያሳየችው መድሎ ትዝብት ውስጥ ጥሏታል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባካሄደችው ጥቃት የተገደሉ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር 498 ደርሷል ብላለች፣ ዩክሬን ግን ቁጥሩ በሺዎች ነው ትላለች።

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
ምን አውርተው ይሆን?
እንደ ሙሉ የእግር ኳስ ጨዋታ ለ90 ደቂቃ ስልኩን አልዘጉትም። ምን ዋጋ አለው?
ከስልክ ውይይቱ አንድም ጠብ ያለ ሰላም አልተሰማም።
እንዲያውም በስልክ ውይይቱ ወቅት ፑቲን ቆጣ ብለው ኪዬቭ አደብ የማትገዛ ከሆነ የሞስኮ ፍላጎቶች ይጨምራሉ ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጦርነቱ ከጀመረ ለሁለተኛ ጊዜ የሁለቱ አገር ተደራዳሪዎች የተገናኙ ሲሆን ዩክሬን ቅድሚያ የምትሰጠው ዜጎቿ በሰላም ከአገር እንዲለቁ ሩሲያ መውጫ መንገድ ትክፈት የሚል ሐሳብ አቅርባለች። ነገር ግን ከውይይቱ ተስፋ ሚሰጥ ነገር አልተሰማም።
በሌላ በኩል ዩክሬንና ሩሲያን ማን ያደራድር በሚለው ጉዳይም ዓለም ሲመክርበት የቆየ ሲሆን አንደኛ ምርጫ ሆነው የቀረቡት የቀድሞ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ናቸው።
አንጌላና ፑቲን በተመሳሳይ ዘመን ምሥራቅ ጀርመን ኖረዋል። ሁለቱ ሲገናኙ ሩስኪ ሳይሆን ጀርመንኛ ይቀናቸዋል ነው የሚባለው።
ፑቲን ድሮ ወጣት ሰላይ ሳሉ ምሥራቅ ጀርምን ይኖሩ ነበር። ያን ጊዜ ነው ጀርመንኛን የቻሉት።
አንጌላ ካልሆኑ የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ሺን ፒንግ ጥሩ ሽማግሌ ይወጣቸዋል ተብሏል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለአልጀዚራ ብቻ በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ አገራቸው በኃይል የያዘቻትን ክሬሚያን ከእንግዲህ ለዩክሬን እንደማትመልስ እቅጩን ተናግረዋል።
ክሬሚያ የሞስኮ አካል መሆኗን ዩክሬን እየመረራትም ቢሆን ትዋጠው ብለዋል ላቭሮቭ።

የጥቃት አድማሳቸው እየሰፋ የመጣው የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬኗ ማሪዮፖሎ ከተማን በከበባቸው ውስጥ አስገብተዋታል።
ኢንተርኔት መብራት ተቋርጧል። ዙሪያ ገባው ገደል ሆኗል።
የዩክሬን ወታደሮች ተወዳጅ ከተማቸው ማሪዮፖል በፑቲን ሰዎች አጅ እንዳትወድቅ እየተዋደቁ ይገኛሉ።
ሩሲያ መርዛማና ተቀጣጣይ የሆነውን የክላስተር ቦምብ በዩክሬን ላይ እየተጠቀመች ስለመሆኑ ማስረጃ ተገኝቷል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ ኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ ናቸው ይህን ይፋ ያደረጉት።


የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ሳምንት አንድ አስፈሪ ዜና ተሰምቷል። የአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ጣቢያ በሩሲያ እጅ ወድቋል። ዛፖሪዢዢያ ይባላል።
በዚህ የኒክሊየር ጣቢያ አንዳች ውድመት ቢከሰት በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች አለቀላቸው። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት የሚወለዱ የልጅ ልጆቻቸው ራሱ ጤነኛ ላይሆኑ ይችላሉ።
አይበለውና የዚህ ኒውክሌር ነዳጅ ማቀዝቀዝው ከተረበሸ ማን ያውቃል መጠነ ሰፊ የራዲዮ አክቲቭ ጨረር ሊያፈተልክ ይችላል።
ይህ ምን ማለት ነው? የሰው ልጅን ሰውነት በሳስቶ የሚገባ ጨረር ይኖራል ማለት ነው። ሰዎች ሰውነታቸው እንደ ጮማ ይቀልጣል ማለት ነው።
ይህን በይበልጥ ለመረዳት ከአስርት ዓመታት በፊት እዚያው ዩክሬን ውስጥ ቼርኖቤል በተባለው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ የደረሰውን አደጋ ማስታወስ ነው።
ይህንን የቼርኖቤል የኒውክሌየር ጣቢያ ላይ ከሦስት አስርታት በፊት የደረሰውን የሚያውቅ የዓለምን ስጋት ይጋራል።
በዚህ ኒውክሌየር ጣቢያ ላይ አንድ ነገር ቢከሰት አሉ ሳይንቲስቶች፣ ጉዳቱ ከጃፓን ሂሮሺማም የከፋ ነው።

የሩሲያ ሞገደኝነት ያሰጋቸው ጎረቤት ጆርጂያ እና ሞልዶቫ ለአውሮፓ ሕብረት ደብዳቤ አስገብተዋል። እባካችሁ የሕብረቱ አባል አድርጉን ሲሉ ተማጽነዋል። ሩሲያን ለብቻ ሆኖ መጎራበት አስፈሪ የሆነባቸው መስለዋል።
በተጨማሪም ፑቲን በአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ምዕራባዊያን ተጨማሪ ማዕቀብ በሩሲያ ላይ እንዳይጥሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህን እየተናገሩ ታዲያ የምዕራብ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በብራስልስ ስለ ተጨማሪ ማዕቀብ እየመከሩ ነበር።
ፑቲን ለሕዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት በዩክሬን ላይ የተከፈተው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ በታቀደለት መልኩ እየሄደ ነው፤ በጭራሽ አታስቡ ብለዋል።














