በዩክሬን አፍሪካውያን እና ሕንዳውያን ተማሪዎች የበዙት ለምንድን ነው?

በርካታ አፍሪካውያን ተማሪዎች ከየክሬን ወደ ፖላንድ ሸሽተዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በርካታ አፍሪካውያን ተማሪዎች ከየክሬን ወደ ፖላንድ ሸሽተዋል

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ከአፍሪካ፣ ከእስያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡና በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን ለስደት ዳርጓል።

በአገሪቱ ከ76,000 በላይ ከውጭ አገራት የመጡ ተማሪዎች እንደሚገኙ እንደ አውሮፓውያኑ 2020 የዩክሬን መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል።

ከጠቅላላ ተማሪዎቹ ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆኑት መነሻቸው የአፍሪካ አገራት ሲሆኑ ከፍተኛ ቁጥር የሚሸፍኑት ደግሞ ከናይጄሪያ፣ ከሞሮኮ እና ከግብፅ የመጡት ናቸው።

ከ20 ሺህ በላይ ሕንዳውያን ተማሪዎች በዩክሬን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ሲሆን ከየትኛውም አገር የበለጠውን ቁጥር ይዘዋል።

በዩክሬን የሚገኙ በርካታ ተማሪዎቹ ሕክምና፣ ምህንድስና እና ቢዝነስ ያጠናሉ። ይህም በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ወሳኝ ቦታ የሚሰጠው ነው።

ሆኖም ሩሲያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ ትልቅ የተባለውን ወረራ መክፈቷን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መውጫ አጥተው ተቸግረዋል። በርካቶች ደግሞ የትምህርታቸው ጉዳይ ምን እጣ ፈንታ እንዳለው እርግጠኛ አይደሉም።

ተማሪዎች ዩክሬንን ለምን ይመርጧታል?

ዩክሬን በተማሪዎች ተመራጫ እንድትሆን ሥራዎች የተጀመሩት አገሪቱ የሶቪየት ሕብረት አካል በነበረችበት ወቅት ነው። አገሪቱ ያኔ በከፍተኛ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ከቅኝ ግዛት ነጻ እየወጡ ከነበሩ የአፍሪካ አገራት ተማሪዎችን ለመቀበል ሥራዬ ብላ ትሰራ ነበር።

አሁን ላይ የዩክሬን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአውሮፓ የሥራ ዕድል ለማግኘት እንደ አንድ መንገድ ተደርገው ይቆጠራሉ። ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚጠይቁት ኪስ የማይጎዳ ዋጋ፤ ቀለል ያለው የቪዛ ሥርዓት እና የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ያለው ቀላል ሂደት ዩክሬንን በተማሪዎች ተመረጭ አድርጓታል።

በዩክሬን መማር ለሚፈልጉ የምዕራብ አፍሪካ ተማሪዎች መንገዶችን የሚያመቻች አንድ ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ፓትሪክ ኢሱጉኑም "የዩክሬን ዲግሪዎች በስፋት የሚታወቁ እና ከፍተኛ የትምህርት ግምት የሚሰጣቸው ናቸው" ብሏል።

"የህክምና ትምህርት ተቋማቱ ጥሩ ደረጃ ስላላቸው በተለይ ብዙ የህክምና ተማሪዎች ዩክሬን ሄደው መማር ይፈልጋሉ" ሲሉም አክለዋል።

ዴዝሞንድ ቻይናዛ ሙውኮኮዶ የተባለው ናይጄሪያዊ ተማሪ በዩክሬን በዲኒፕሮ ከተማ እየኖረ ትምህርቱን ይከታተላል። ዩክሬን ከሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ጋር ስትነጻጸር ብዙም የማያጨናንቅ የመግቢያ ፈተና የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ርካሽ ኑሮ መኖሩም በተማሪዎች ተፈላጊ እንድትሆን አድረጓታል ብሏል።

ዴዝሞንድ በጉምሩክ እና ፋይናንስ የትምህርት ዘርፋ ለመማር ዩኒቨርሲቲ ከተመዘገበ ሦስት ወር እንኳን አልሞላውም።

በአገሪቱ በርካታ ትምህርቶች የሚሰጡት በእንግሊዘኛ ነው። ነገር ግን የ30 ዓመቱ ተማሪ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከማጥናቱ በፊት በጀማሪ ደረጃ የዩክሬን ቋንቋ ኮርስ እየተማረ ነበር።

ግጭቱን ሸሽቶ ፖላንድ ከሚገኝ ሆስቴል የሚኖረው ተማሪው ለቢቢሲ ሲናገር "ናይጄሪያ እያለሁ ብረት ብየዳ እሰራ ነበር። የምፈልጋቸውን ነገሮችን ለማከናወን መማር እፈልግ ነበር" ብሏል። "ዩክሬን ለእኔ ምርጥ አማራጭ ነበረች" ሲልም አክሏል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ጦርነቱን በመሸሽ ከዩክሬን ለመውጣት የሞከረችው አፍሪካዊት ገጠመኝ

ተማሪዎቹ አሁን የት ይገኛሉ?

እንደ ዴዝሞንድ ሙውኮኮዶ ያሉ ከ10,000 በላይ አፍሪካውያን ተማሪዎች ግጭቱን ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገራት መግባታቸውን የአውሮፓ ሕብረት አስታውቋል።

ጦርነቱን ሸሽተው የሚወጡ የውጭ አገራት ተማሪዎች በድንበር ላይ የዘረኝነት ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል። በሌላ በኩል የዩክሬን ባለሥልጣናት ተማሪዎች ድንበር እንዳያቋርጡ ሲከለክሉ የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በኩል የተጋሩ ምስሎች ያሳያሉ።

ትክክለኛውን ቁጥር ማረጋገጥ አዳጋች ቢሆንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሁንም በጦርነት በምትታመሰው ዩክሬን ውስጥ እንደሚገኙ ይታመናል። አንድ ሕንዳዊ ተማሪ ምግብ ለመግዛት ከመኖሪያ ቤቱ በወጣበት አጣሚታሚ መገደሉም ተዘግቧል።

አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት ዩኒቨርሲቲዎቻቸው የገጽ ለገጽ ትምህርት አቁመው ትምህርቱን በኢንተርኔት እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ አለማግኘታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ዩኒቨርሲቲው የእኛን ተማጽኖ እና ስጋቶች ችላ ብሎታል" ስትል የገለጸችው ናይጄሪያዊቷ የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪ ሜሪ ናት።

ሜሪ ከዩንቨርስቲው በጊዜያዊነት ለመውጣት ጠይቀው ቢጠይቁም ትምህርታቸውን ካቋረጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እንደተናገራቸው ገልጻለች። በአንዳንድ የዩክሬን ዩኒቨርስቲዎች ይህ የተለመደ ደምብ በመሆኑ ከመቆየት ውጪ "አማራጭ አልነበረንም" ስትል ገልጻለች።

ሜሪ አሁን በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ሱሚ ውስጥ ትገኛለች። ከተማው ላይ ደግሞ የሩሲያ ኃይሎች ተከታታይነት ጥቃት እየፈጸሙ ይገኛሉ። "ወደ ዩክሬን የመጣነው ለዚህ አለነበረም። ትምህርታችንን ተከታትለን ወደ አገራችን ለመመለስ ነበር" ብላለች።

እሷም ሆነች ሌሎች ጓደኞቿ የምግብ እጥረት እያጋጠማቸው እንደሆነና በየጊዜው በሚደረገው የአየር ድብደባ ምክንያት አስቤዛ ለመሸመት መውጣት አስተማማኝ አለመሆኑን ተናግራለች።

ሜሪ ትምህርቷን የምትከታተልበት ዩኒቨርሲቲ ሩሲያ ዩክሬንን ታጠቃለች የሚል እምነት እንዳልነበረው ገልጿል። ነገር ግን ከወረራው በፊት አገሪቱን ለቀው ለመውጣት የወሰኑ ተማሪዎችን እቀጣለሁ አላልኩም ብሏል።

የሩስያ ጦር ወደ ዩክሬን ከመግባቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሁሉም ተማሪዎች በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲማሩ ወስኖ እንደነበርም ገልጿል።

"ወደ ውጭ የማንወጣው ስለፈራን ነው" ሲል የ22 ዓመቱ ካሜሩናዊ ተማሪ ክሪስቶፍ ለቢቢሲ ተናግሯል። እሱ እና ከ20 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ያለፈውን ሳምንት ብርሃን በሌለበት ምድር ቤት ውስጥ የፍንዳታ እና የተኩስ ድምጽ እየሰሙ እንዳሳለፉ ገልጿል። ያለበትን ከተማ "የሙታን ከተማ መስላለች። ውጭ ማንም የለም" ሲል አክሏል።

በጦርነቱ ወቅት አፍሪካውያን ላይ የተለየ ጉዳት ለማድረስ የሚያስብ ምንም አዝማሚያ እንዳላስተዋለ የተናገረ ሲሆን በቤት ውስጥ መቆየት የተሻለ ነው ብሎም ያምናል። "ወደ ውጪ አለመውጣት መደረግ ያለበት በጣም አስተማማኝ ነገር ነው። እራሳችንን አደጋ ላይ መጣል አንፈልግም" ብሏል።

ሌላው ከጊኒ ወደ ዩክሬን ያቀናው የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ማማዲ ዱምቡያ "ወደ አገሬ መመለስ እፈልጋለሁ። ጦርነት ውስጥ መማር አንችልም" ሲል ተደምጧል።

ዱምቡያ ይህንን ለቢቢ ሲናገር ከጋቦን፣ ከሴኔጋል እና ከካሜሩን ከመጡ የክፍል ጓደኞቹ ጋር በጨለማ ምድር ቤት ውስጥ ሆኖ እንደሆነ ተናግሯል። "ውሃ የለንም። ብርሃንም የለንም" ሲል ጨምሮ ገልጿል።

አንዲት አፍሪካዊት በፖላንድ ድነበር አቅውራቢያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

መንግሥታት ተማሪዎችን ለመርዳት ምን እያደረጉ ነው?

ዩክሬን ሁሉንም መደበኛ የአውሮፕላን በረራዎች ያቆመችው ወረራው እንደተጀመረ ነበር።

የአፍሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸውን በጦርነት ከምትታመሰው ዩክሬን ለማስወጣት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የተወሰኑ አገራት ዜጎቻቸን ጦርነት ሸሽተው ከሚገኙበት አገራት ወደ አገራቸው ለመመለስ በረራዎችን እያደረጉ ነው።

ጋና በዩክሬን የነበሩ ተማሪዎችን በመመለስ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ አገር ናት። ባለፈው ማክሰኞ ተማሪዎችን የያዘ አውሮፕላን ዋና ከተማ አክራ ላይ አርፏል።

ወደ አገሩ የገባው የዩክሬን ተማሪ ጃሬድ ኦቱምፉኦ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት "ከጥቂት ቀናት በፊት እዚህ እንደምገኝ እርግጠኛ አልነበርኩም። ይህ በመሆኑ ደስ ብሎኛል። አሁን ደኅንነት ተሰምቶኛል" ብሏል።

ናይጄሪያም በሩሜኒያ፣ በሃንጋሪ እና በፖላንድ በኩል ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ተማሪዎች በረራዎችን አዘጋጃለሁ ብላለች።

ለደኅንነታቸው ሲሉ ዩክሬንን ለቅቀው መውጣታቸውን የገለጹት በዩክሬን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ደቡብ አፍሪካውያን እና ሌሎች የውጭ አገር ዜጎች ከዩክሬን በሰላም እንዲወጡ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በፖላንድ እና በሃንጋሪ የሚገኙ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደሮችም ዜጎቻቸው በድንበር ሲያልፉ ችግር እንዳይገጥማቸው ለመርዳት ወደ አገራቱ ድንበር ድርስ ተጎዘው ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል የዩክሬን መንግሥት ከጦርነት እየሸሹ ያሉ አፍሪካውያን እና እስያውያንን ለመርዳት የሚውል የአደጋ ጊዜ የስልክ መስመር ይፋ ማድረጉን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቀዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዲሚትሮ ኩሌባ በትዊተር ገፃቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት የአፍሪካ እና የእስያ ተማሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰሩ ነው ሲሉ አስፍረዋል።

ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን የመጨረስ እድል አላቸው?

በዩክሬን ለትምህርት ብዙ ገንዘብ አውጥተው እየተማሩ ያሉ በርካታ ተማሪዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ ወይም በአውሮፓ ቆይተው ትምህርታቸውን ለመጨረስ በሚሉ ሁለት አጣብቂኝ ሃሳቦች ውስጥ እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቴርኖፒል ናሽናል ሜዲካል ዩንቨርስቲ የስድስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ የሆነችው ጄሲካ ኦራክፖ የሩሲያ ወታደሮች የክሬንን በወረሩበት ወቅት እሷ ለመመረቅ የቀራት አራት ወራት ብቻ ነበሩ።

ወደ ሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት እያቀናች ያለችው ተማሪዋ "አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ነኝ። ሁሉም የትምህርት ሰነዶቼ በትምህርት ቤቱ እጅ ናቸው። ስለዚህ በትምህርቴ መግፋት አልችልም" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች። "ትምህርቱን እንደገና ለመጀመር ጊዜ የለኝም የምፈልገው ዲግሪዬን ብቻ ነው። የማስተርስ ትምህርቴን ሌላ ቦታ ልጨርስ እችላለሁ" ብላለች።

በዩክሬን ውስጥ ያሉ የውጭ አገራት ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ጊዜያዊ መኖሪያ ይቀርብላቸዋል። ነገር ግን ይህ በጎረቤት አገሮች ውስጥ አይሰራም። ሙኮኮዶ ትምህርቱን በሌላ የአውሮፓ አገር ለመጨረስ እንደሚሞክር ተናግሯል።

"እዚህ ቆይቼ ሁኔታው ይሻሻል ይሆን አይሆን የሚለውን አያለሁ። ወደ ናይጄሪያ መመለስ ግን አማራጭ አይደለም" ብሏል።