ሩሲያ እና ዩክሬን፡ ጦርነቱ እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል? ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችሉ አምስት ሁኔታዎች

የዩክሬን ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጦርነቱ ጭጋግ ውስጥ ሆኖ ስለወደፊት ማሰብ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ከጦር አውድማ የሚሰሙት ዜናዎች፣ የዲፕሎማሲው ጩኸት፣ የሐዘንና የተፈናቃዮች ስሜት፤ ይህ ሁሉ ከአቅም በላይ ሊሆን ይችላል።

እስቲ ለአፍታ ከዚህ ሁሉ አረፍ ብለን በዩክሬን ያለው ግጭት እንዴት ሊያበቃ እንደሚችል እናስብ። ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ ባለሙያዎች እያጤኗቸው የሚገኙት ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

ጥቂቶች ብቻ ናቸው ስለወደፊቱ በልበ ሙሉነት ሊተነብዩ የሚችሉት። አንዳንድ ሊሆኑ የሚችሉ ውጤቶችን እነሆ።

አጭር ጦርነት

ይህ እንዲሆን ሩሲያ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን ታሳድጋለች። በመላ ዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች እና የሮኬት ጥቃቶች ይፈጸማሉ። እስካሁን ዝቅተኛ ሚና የነበረው የሩሲያ አየር ኃይል አውዳሚ የአየር ድብደባዎችን ይጀምራል።

ቁልፍ የሆኑ ብሔራዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች በዩክሬን ላይ ይደርሳሉ። የኃይል አቅርቦቶች እና የመገናኛ አውታሮች ይቋረጣሉ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰዎች ይሞታሉ።

በጀግነነት ቢከላከሉም ኪዬቭ በቀናት ውስጥ እጅ ትሰጣለች። በሞስኮ የሚደገፍ የአሻንጉሊት አገዛዝ መንበሩን ይቆጣጠራል። ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ይገደላሉ ወይም የግዞት መንግሥት ለመመስረት ወደ ምዕራብ ዩክሬን ካልሆነም ወደ ባሕር ማዶ ይሸሻሉ።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ማሸነፋቸውን ያውጃሉ። የተወሰኑ ኃይሎቻቸውን ወደ ሩሲያ በመመለስ ሌሎቹ ቁጥጥር ለማድረግ በዩክሬን ይቀራሉ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ምዕራብ መሸሻቸውን ይቀጥላሉ። ዩክሬን ቤላሩስን በመቀላቀል ለሞስኮ መገበር ትጀምራለች።

ይህ ላይሳካ የሚችል ቢመስልም ብዙ ነገሮች ላይ መለዋወጥ ሊከሰት ይችላል። በተለይም ደግሞ የሩሲያ ኃይሎች በተሻለ ሁኔታ ካጠቁ፣ በብዛት ከዘመቱ እና የዩክሬናውያን የውጊያ መንፈስ ከደበዘዘ ሊሳካ ይችላል።

ፑቲን በኪዬቭ የመንግሥት ለውጥ በማድረግ የዩክሬን ከምዕራባቡ ጋር የምታልመው ውህደት ሊያከትም ይችላል። ሆኖም ማንኛውም የሩሲያ ደጋፊ መንግሥት ሕጋዊነት የሌለውና እና ለአመጽ ተጋላጭ ይሆናል። ይህ ያለመረጋጋትን በመፍጠር እንደገና ግጭት የመከሰት ዕድሉን ከፍተኛ ያደርገዋል።

ረዥም ጦርነት

ምናልባትም ይህ ግጭት ወደ ረዥም ጊዜ ጦርነት የመቀየር ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ምናልባትም የሩሲያ ኃይሎች በሥነ ምግባር ማነስ፣ በደካማ ሎጅስቲክስ እና በብልህ አመራር ማጣት እየተደናቀፉ ይወድቃሉ።

በጎዳናዎች ላይ በሚደረጉ የመከላከል ውጊዎች ሳቢያ እንደ ኪዬቭ ያሉ ከተሞችን ለመቆጣጠር የሩሲያ ኃይሎች ረዥም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ረዥም ከበባ ይመጣል።

ጦርነቱ እአአ በ1990ዎቹ የቺቺኒያ ዋና ከተማ የሆነችውን ግሮዝኒን ለመያዝ እና ለማጥፋት ሩሲያ ያደረገችውን ረዥም እና ጭካኔ የተሞላበት ጦርነትን የሚያስታውስ ነው።

የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ከተሞችን መያዝ ከቻሉም ለመቆጣጠር ሊቸገሩ ይችላሉ። ምናልባትም ሩሲያ እንደዚህ ያለውን ሰፊ አገር ለመሸፈን በቂ ወታደሮችን ማሰማራት አትችል ይሆናል። የዩክሬን ኃይሎች ወደ ሽምቅ ተዋጊነት ለመቀየር ተነሳሽነት ያላቸው እና በአካባቢው ሕዝብ የሚደገፉ ሊሆኑ ይችላሉ።

ምዕራባውያን የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ከዚያም ከብዙ ዓመታት በኋላ ምናልባት በሞስኮ አዲስ አመራር ሲቀየር የሩሲያ ኃይሎች አንገታቸውን ደፍተውና በደም ጨቅይተው መጨረሻ ዩክሬንን ለቀው ሊወጡ ይችላሉ።

ይህም የሶቪየት ኃይሎች እአአ በ1989 በአፍጋኒስታን ውስጥ ተሰማርተው ሙጃሂዲን እስላማዊ አማፂያንን ሲዋጉ ቆይተው ከአስር ዓመታት በኋላ የወጡበት መንገድ ዩክሬን ውስጥ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

የቼቺኒያ ተዋጊዎች በዋና ከተማዋ ግሮዝኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቼቺኒያ ተዋጊዎች በዋና ከተማዋ ግሮዝኒ

የአውሮፓ ጦርነት

ይህ ጦርነት ከዩክሬን ድንበር ውጪ ሊቀጥል ይችል ይሆን? ፕሬዚዳንት ፑቲን የኔቶ አባል አገራት ያልሆኑትን እንደ ሞልዶቫ እና ጆርጂያ ያሉትን የቀድሞ የሶቪየት ሪፐብሊኮች ጦራቸውን በማዝመት የቀድሞ የሩሲያ ግዛትን መልሶ ማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። ወይም የተሳሳተ ስሌት እና የጦርነት መባባስ ሊኖር ይችላል።

ፑቲን የምዕራባውያን ለዩክሬን ኃይሎች የሚያደርጉትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ጠብ ጫሪ በማለት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ሊወስኑ ይችላሉ። ከሩሲያ የባሕር ዳርቻ ከሌኒንግራድ ጋር የመሬት ኮሪደር ለመመስረት ወታደሮቻቸውን እንደ ሊቱዌኒያ ወዳሉ የኔቶ አባል አገር የባልቲክ ግዛቶች እንደሚልኩ ሊያስፈራሩ ይችላሉ።

ይህ በጣም አደገኛ ሲሆን ከኔቶ ጋር ጦርነትን ሊቀሰቅስ ይችላል። የወታደራዊ ሕብረቱ ቻርተር አንቀፅ 5 እንደሚለው በአንድ አባል ላይ የሚደረግ ጥቃት በሁሉም ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው።

ፑቲን ሥልጣናቸውን ለማዳን ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ከተሰማቸው ይህንን መንገድ ሊመርጡ ይችላሉ። ምናልባትም በዩክሬን ሽንፈት ከገጠማቸውም ጦርነቱን የበለጠ ለማስፋት ሊሞክሩም ይችላሉ።

ፑቲን ለረዥም ጊዜ ዓለም አቀፍ ደንቦችን ለመጣስ ወደኋላ እንደማይሉ ታይቷል። ይህ አመክንዮ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይም ሊተገበር ይችላል። ፑቲን የኒውክሌር ኃይላቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

በርካታ ተንታኞች ትዕዛዙ መሣሪያውን ስለመጠቀማቸው ወይም መጠቀማቸው የማይቀር መሆኑ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ሆኖም የሩሲያ አስተምህሮ በጦር ሜዳ ላይ ስልታዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም እንደሚቻል የሚያስታውስ ነው።

በሩሲያ ሠራዊት የከባድ መሳሪያ ድብደባ የወደመው በካርኪቭ ከተማ የሚገኘው አደባባይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሩሲያ ሠራዊት የከባድ መሳሪያ ድብደባ የወደመው በካርኪቭ ከተማ የሚገኘው አደባባይ

ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "አሁን የሚናገሩት ጠመንጃዎቹ ቢሆኑም የውይይቱ መንገድ ሁሌም ክፍት ሆኖ መቀጠል አለበት" ብለዋል። በእርግጠኝነትም ውይይቱ ይቀጥላል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል። በሚገርም ሁኔታም የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት ቤላሩስ ድንበር ላይ ለመነጋገር በተደጋጋሚ ተገናኝተዋል። ረብ ያለው ነገር ላይ አልደረሱ ይሆናል። ነገር ግን ፑቲን ለመነጋገር መስማማታቸው ቢያንስ በድርድር የተኩስ ማቆም ዕድል መኖሩን የተቀበሉ ይመስላል።

ዋናው ጥያቄ የአሜሪካንን ቃል ማስቀየር ይቻላል ወይ? የሚለው ነው። ዲፕሎማቶች እንደሚናገሩት የሩሲያው መሪ የምዕራባውያን ማዕቀቦችን ለማስነሳት ምን እንደሚያስፈልግ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ሲሆን፣ ለዚህም ቢያንስ ራስን የማዳን ስምምነት ሊደረስ ይቻላል ።

ይህንን ሁኔታ እንመልከት፤ ጦርነቱ ለሩሲያ መጥፎ ሆኖ እየሄደ ነው እንበል። ማዕቀቡ ሞስኮን ማነቃነቅ ጀመሯል። አስከሬን ወደ አገር ቤት ሲመለስ ተቃውሞ እየጨመረ ይሄዳል። ፑቲን መዋጥ ከሚችሉት በላይ ጎርሰው እንደሆነ ሊያስቡ ይችላሉ። ጦርነቱ እንዲቀጥል በማድረግ ከሚመጣው ውርደት ይልቅ ለስልጣናቸው ትልቅ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ይገመግማሉ።

ቻይና ጣልቃ ገብታ የሩሲያን ዘይትና ጋዝ ጦርነቱ እስካልቆመ ድረስ እንደማትገዛ በማስጠንቀቅ በሞስኮ ላይ ጫና አሳድራ እንድትስማማ ታደርጋለች። ስለዚህ ፑቲን መውጫ መንገድ መፈለግ ይጀመራሉ።

የዩክሬን ባለሥልጣናት በበኩላቸው በአገራቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በመመልከት የፖለቲካ ስምምነት ማድረግ ከእንደዚህ አይነት አሰቃቂ የህይወት መጥፋት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብለው ይደመድማሉ። ስለዚህ ዲፕሎማቶች ጣልቃ ይገቡና ስምምነት ይደረሳል።

እንበልና ሩሲያ ክራይሚያ እና ዶንባስ እንድትወስድ ዩክሬን ትፈቅዳለች፤ በምላሹ ደግሞ ፑቲን የዩክሬን ነፃነት እና ከአውሮፓ ጋር ያላትን ግንኙነት የማጠናከር መብትን ይቀበላሉ። ይህ የማይመስል ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከደም አፋሳሽ ግጭት ሊመጣ የሚችልም ጭምር ነው።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ከተቃወሙ ሰልፈኞች መካከል አንዱ በፖሊስ ተይዞ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ከተቃወሙ ሰልፈኞች መካከል አንዱ በፖሊስ ተይዞ

የፑቲን ከሥልጣን መወገድ

ቭላድሚር ፑቲን ራሳቸው ወረራውን ሲጀምሩ "ለማንኛውም ውጤት ዝግጁ ነን" ብለው ነበር።

ውጤቱ ሥልጣናቸውን ማጣት ቢሆንስ? የማይታሰብ ሊመስል ይችላል። ዓለም ባለፉት ቀናት በመቀየሯ እንደዚህ ያሉ ነገሮች አሁን ይታሰባሉ። በለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የጦርነት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ሰር ላውረንስ ፍሪድማን በዚህ ሳምንት "እንደ ኪዬቭ ሁሉ በሞስኮም የመንግሥት ለውጥ ሊኖር ይችላል" ሲሉ ጽፈዋል።

ይህን ለምን ሊሉ ቻሉ? ምናልባት ፑቲን አስከፊ ጦርነትን ስለጀመሩ ሊሆን ይችላል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች እየሞቱ ነው። የኢኮኖሚ ማዕቀቡ ጉዳት ይኖረዋል። ፑቲን የሕዝብ ድጋፍ ሊያጡ ይችላሉ። ምናልባትም የሕዝባዊ አብዮት ስጋት አለ። ያንን ተቃውሞ ለማፈን የሩሲያን የፀጥታ ኃይሎች ይጠቀማሉ።

ይህ ሁሉ አሰልቺ ሆኖ የሩሲያ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልሂቃን ፊታቸውን ሊያዞሩባቸው ይችላሉ። ምዕራባውያን በግልጽ እንደሚናገሩት ፑቲን ከሄዱ እና ለዘብተኛ መሪ ከተተካ አንዳንድ ማዕቀቦችን በማንሳት መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንደሚመለስ ግልፅ ነው።

ደም አፋሳሽ መፈንቅለ መንግሥት ተካሄዶም ፑቲን ሊነሱ ይችላሉ። ይህም ምናልባት አሁን ላይመስል ይችላል። ነገር ግን ከፑቲን ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንደማይችሉ ካመኑ ሊሆን ይችላል።

እንደ ማጠቃለያ

እነዚህ መላ ምቶች ራሳቸውን ችለው ብቻ የሚቆሙ ላይሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶቹ የተለያዩ ውጤቶችን ለማምጣት ሊጣመሩ ይችላሉ። ነገር ግን በዚህ ግጭት ዓለም ተለውጧል። ወደ ቀድሞው ሁኔታው አይመለስም። ሩሲያ ከውጭው ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት የተለየ ይሆናል። አውሮፓ ለደኅንነት ያላት አመለካከት ይለወጣል።