ምርጫ ቦርድ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብ በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የረጅም ጊዜ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተከልክለው በቁም እስር ላይ እንደቆዩ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ገለጸ።
ይህም ድርጊት ከሕግ ውጪ በመሆኑ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብ በአፋጣኝ እንዲነሳ ቦርዱ ለፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን እና ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በደብዳቤ ጠይቋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ለሁለቱ የፀጥታ ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዳመለከተው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር ለረጅም ጊዜ ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የቀረበውን አቤቱታ አጣሪዎችን በማሰማራት ማረጋገጡን ገልጿል።
በዚህም መሠረት ከቦርዱ የተላኩት አጣሪዎች የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ወደ ሚገኘው የአቶ ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ በሄዱበት ጊዜ ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሠራተኞች በር እንደከፈቱላቸውና ማንም ሰው መግባት እንደማይችል መረዳታቸውን ደብዳቤው አመልክቷል።
ወደ መኖሪያ ቤቱ በመግባት ሊቀመንበሩን ለማግኘትም ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው፣ በዚህም መሠረት አጣሪዎቹ ከየት እንደመጡና ማንነታቸውን ተጠይቀው አቶ ዳውድን እንዲጎበኙ እንደተፈቀደላቸው ገልጸዋል።
የኦነግ ሊቀመንበርን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከማግኘታቸው በፊትም በፀጥታ ሠራተኞቹ ቦርሳቸው መፈተሹ እንዲሁም ስልክ ይዘው መግባት እንደማይችሉ እንደተነገራቸውና ይህንኑ በማድረግ በመጨረሻ አቶ ዳውድን እንዳገኙ ቦርዱ በደዳቤው ላይ ጠቅሷል።
አጣሪዎቹ ከኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ባደረጉት ውይይት ከመጋቢት 24፣ 2013 ዓ.ም በቤታቸው እንዲገደቡና እንዳይወጡ መከልከላቸውን አስረድተዋል።
የታጠቁ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ተመድበውም እንደከለክሏቸውም ምርጫ ቦርድ በመግለጫው አስፍሯል።
ከዚህም በመነሳት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ የመንቀሳቀስ መብት ተገድቦ በቁም እስር በቤታቸው ውስጥ እንዳይወጡ መደረጋቸውን መገንዘቡን በደብዳቤው ላይ አመልክቷል።
በመሆኑም ቦርዱ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የተፈጸመው ይህ የመንቀሳቀስ ገደብ በየትኛውም ሕግ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ያሉበት የቁም አስር በአፋጣኝ እንዲነሳ ጠይቋል።
ቦርዱ ፌደራል ፖሊስ እና ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በጻፈው ደብዳቤ በሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ ቤት የተመደቡት ጥበቃዎች በአስቸኳይ እንዲነሱና የግለሰቡ የመንቀሳቀስ መብታቸው እንዲከበር አድርገው ለቦርዱ በአስቸኳይ እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
ከዚህ ቀደም የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ መሆናቸው እንዳሳሰበው የመብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማስታወቁ ይታወሳል።
ሊቀ መንበሩ ምንም አይነት ክስ ሳይቀርብባቸው በቁም አስር ላይ የሚገኙት ከሚያዝያ 25/2013 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑንም ገልጾ ነበር።
አቶ ዳውድ ከቤት መውጣት የተከለከሉት ፖሊስ ካለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መኖሪያቸውን ፈትሾ ኮምፒውተሮችናን የሞባይል ስልኮችን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚያ ቀን በኋላ ፖሊስ ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣና ወደ ቤቱም እንዳይገባ የከለከለ ሲሆን አሁን በቤቱ ውስጥ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች አልቀው ወይም እያለቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ አቶ ዳውድ ያሉበት ሁኔታና ደኅንነታቸው አሳሳቢ መሆኑን አምነስቲ አመልክቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጉዳዩን በማስመልከት በወቅቱ የሰላም ሚኒስትር ለነበሩት ሙፈሪያት ካሚል ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፤ በዚህም የአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሕግ ውጪ በቁም አስር ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸው እንዳሳሰበው አመልክቷል።
አምነስቲ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በተቀበለችው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታ መሠረት ሃሳብን የመግለጽና የመደራጀት መብትን እንዲያከብሩና እንዲጠብቁና ጠይቋል።
አምነስቲ መንግሥትን አቶ ዳውድ ኢብሳን በአስቸኳይ ከቁም አስሩ እንዲለቅ ወይም የፈጸሙት ጥፋት ካለና በቂ ማስረጃ ካለውም በተገቢው ሁኔታ ክስ እንዲመሰርት ጠይቆ ነበር።
አቶ ዳውድ ኢብሳ ለረጅም ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን ግንባሩ በሽብርተኛ ቡድንነት በተፈረጀበት ጊዜ መቀመጫቸውን ኤርትራ ውስጥ በማድረግ የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መጥተው ፖለቲካዊ ለውጥ በአገሪቱ ሲደረግ በኦነግ ላይ ተጥሎ የነበረው የሽብርተኛ ድርጅትነት ፍረጃ ተነስቶለት በአገሪቱ ፖለቲካዊ መድረክ ውስጥ ለመሳተፍ መሪዎቹ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ የተወሰነው የቡድኑ ተዋጊም ወደ ተሃድሶ መግባቱ ይታወሳል።
በግንባሩ ውስጥ በተደጋጋሚ መከፋፈል ያጋጠመ ሲሆን አቶ ዳውድ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ የተወሰኑ የቡድኑ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ሳይፈቱ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሰቀሰው መንግሥት ሸኔ የሚለውና እራሱን የአሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ቡድን በሚፈጽማቸው ጥቃቶች ምክንያት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ተሰይሟል።
ከቡድኑ ታጣቂ ኃይል በተጨማሪ አዲስ አበባ በገቡት የፖለቲካ አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ በግንባሩ የመሪነት ሚና ላይ መከፋፈል መፈጠሩ ይታወቃል። ከአቶ ዳውድ ኢብሳ የተለየውን ቡድን የሚመሩት አካላት ትክክለኛው የኦነግ መሪዎች መሆናቸውን በመግለጽ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ ሙከራ አድርገው ነበር።
ይህ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን ኦነግ እውቅና የነፈገውና የግንባሩ ትክክለኛ አመራር መሆኑን የሚገልጸው አካል ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ በኋላ መንግሥት ተቃዋሚዎችን በሚመሰርተው መንግሥት ውስጥ ለማሳተፍ በገባው ቃል መሠረት የተወሰኑት በኦሮሚያና በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።












