ሕይወት ከጦርነት በኋላ በደሴ፣ በወልድያ እና በላሊበላ

ከአዲስ አበባ ወደ ኮምቦልቻ ያቀናነው በከሰዓቱ በረራ ነበር። ትኬቴ ላይ የተጻፈው የወንበር ቁጥር ላይ አንዲት ልጅ የያዘች ሴት ተቀምጣበታለች። ሙሉ አስፋው ነበረች። "ግድ የለም" ብዬ ሌላኛው ወንበር ላይ ተቀመጥኩ።
እንዲሁ በዕይታ ከአንደበቷ ቁጥብ ትመስላለች። በዚያ ላይ አራስ ልጇን ማባበሉ አንድ ተጨማሪ ሥራ ስለሚሆን ከሌላ ሰው ጋር የምታወራበት ጊዜ እንደማይኖራት ግልጽ ነው።
የበረራ አስተናጋጆቹ የሚቀመስ ነገር ካቀረቡልን በኋላ "የሚጠጣ ነገር ምን ይሁንልሽ"? ብያት ዝምታችንን ሰበርን። ሙሉ የአስር ቀን አራስ እያለች ከደሴ ወደ አዲስ አበባ ተሰድዳ በአራተኛ ወሯ ወደ ቤቷ እየተመለሰች መሆኑን የነገተችኝ ከእዚህ ሁሉ በኋላ ነበር።
ጦርነቱ በደሴ ዙሪያ ሲካሄድ ሙሉ ምጥ ላይ ነበረች። በወቅቱ ሙሉ አገልግሎት ይሰጥ በነበረው ደሴ ሆስፒታል የመጀመሪያ ልጇን ተገላግላ ወደ ቤቷ አመራች። ነገር ግን ጦርነቱ እዚያው አልቆመም። ወደ ደሴ እየተጠጋ መጣ። ሙሉ በወለደች በአስረኛው ቀን የራሷንና የልጇን ሕይወት ለማትረፍ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመረች።
የመኪና ትራንስፖርት ያገኘችው እስከ ኮምቦልቻ ድረስ ብቻ ነበር። ከእዚያ በኋላ ያለውን መንገድ በእግር መጓዝ ነበረባት። ከኋላዋ የሚከተላትን ጦርነት ለማምለጥ ፍጥነቷን ጨምራ ተጓዘች።
አራስነቷ ሳይበግራት ብዙ ርቀት ተጓዘች። በአጋጣሚ መኪና አግኝታ ጉዞዋን ወደ ከሚሴ ቀጠለች። እንዲያም ሆኖ ከኋላዋ ጥላው የሸሸችው ጦርነት ከፊት ቀድሞ ጠበቃት።
ከሚሴ ላይ ኦነግ-ሸኔ የከፈተው ነው በተባለው ጦርነት ምክንያት ማለፍ አልቻሉም። የጥይት ሩምታ እየወረደባቸው መኪና ውስጥ ተቀምጠው አምስት ሰዓታትን አሳለፉ። ከአምስት ሰዓት ቆይታ በኋላ ከሚሴን አለፉ። በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው ሙሉ እና ቤተሰቧ ደብረ ብርሃን ደረሱ።

በእዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ለመድረስ አምስት ቀን ፈጅቶባታል። ጉዞ ላይ ባሳለፈቻቸው አምስት ቀናት አጠገቧ ሰዎች ሲሞቱና ሲቆስሉ አይታለች። ያንን ክስተት ያየችበትን መንገድ ድጋሚ ማየት አትፈልግም። ለእዚያም ነው በአውሮፕላን መሄድን የመረጠችው።
ኮምቦልቻ አየር ማረፊያ ደረስን። እቃችንን የተቀበልነው ለየት ባለ መልኩ ነው። ከአውሮፕላኑ ወርዶ ወደ ተሽከርካሪ ተጫነ። ወደ እቃ መቀበያው ክፍል አልገባም። ከተሽከርካሪው ላይ እያነሳን እንድንወስድ ተደረገ።
ምክንያቱ የሚገመት ነው። የእቃ መቀባያ ማሽኑ ምናልባትም በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት አገልግሎት ባለመጀመሩ ሊሆን ይችላል። ከሙሉ ጋር ተለያየን።

ኮምቦልቻ ላይ ምንም ጊዜ አላጠፋንም። ወድያውኑ ወደ ደሴ መንገድ ጀመርን። ከሹፌሩ ጎን ያለውን መቀመጫ ይዤ ስለነበር የጦርነቱን ተፅዕኖ ለማንበብ ዓይኔ በሦስት አቅጣጫ ይቀላውጣል። ወደፊት፣ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ።
ጦርነቱን በሁለቱም ዙር በአንክሮ የታደመው የሐረጎ ጠመዝማዛ መንገድ እኛ እንመለከተው ዘንድ ያስቀመጠው ምልክት አልነበረም። መንገዱ ከዓመት በፊት ሳየው ከነበረው የትራፊክ ፍሰት አንፃር የጎደለው አንድ ነገር ብቻ ነው።
ለወትሮው መንገዱን የሚያጨናንቁት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሐራ ገበያ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ከሚታወቁበት "Yapi Merkezi" ጽሑፍ ጋር በእዚህ መንገድ አንዳቸውም የሉም። በኋላ ከፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ እንደሰማሁት ንብረቶቹ በመዘረፋቸው ኮንትራክተሩ ሥራ አቋርጦ ወደ ቱርክ አምርቷል።
ስለሐረጎ የደን ክምችት እየተደነቅን ወደ ደሴ ተቃረብን። ዓይኔ ለማየት ሲቀላውጥለት የነበረውን የጦርነት ምልክት ሐረጎን ከመሰናበታችን በፊት አገኘ። አንድ ዙ-23 ተመትቶ ጭራሮ መስሎ ጥግ ይዞ ቆሟል። ትንሽ አለፍ እንዳልን በተመሳሳይ ሁኔታ የወደመ መድፍ አገኘን።

ሐረጎን እንደጨረስን የጉጉፍቱ መገንጠያ ላይ የፍተሻ ኬላ ጠበቀን። የፍተሻውን ኬላ እንዳለፍን ደሴን ተንተርሶ የተጋደመ የነዳጅ ቦቴ አገኘን። ጋቢናው ፈራርሶ ወገቡ ደሴን ከልሎ የያዛት ተራራን ተደግፎ ተጋድሟል። ነጭ መደቡ ላይ በጥቁር ቀለም የተለያዩ መልዕክቶች ተፅፈውበታል። ወደ ደሴ አቅጣጫ እንደዞረ የወደቀ በመሆኑ ምናልባት የህወሓት ኃይሎች ሲመለሱ በሰው አልባ አውሮፕላን የተመታ ሊሆን ይችላል።
ደሴ
ጠመዝማዛውን መንገድ አገባደን የደሴ መግቢያ በሮች ደረስን። ደሴ መግቢያዋ ላይ ብዙም የተለየ ነገር አይስተዋልባትም። የመብራት ተሸካሚ ምሰሶዎች አረንጏዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ተሸላልመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደሴ መገለጫ እየሆነ የመጣው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የወሎ ጭስ አሁንም ከእነ ሙሉ ክብሩ በቦታው ተሰድሯል።
ከጭሱ ተራ ትንሽ ራቅ ብለው የመንገዱን የቀኝ ጥግ የያዙ የረጅም ርቀት ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎቻቸውን ያወርዳሉ። የከተማ ታክሲ እና ባጃጆች እንደወትሮው ትራፊኩን አጨናንቀውታል። ሁሉም ሱቆች ክፍት ናቸው። የተዘጋ ቤት እንዳለ በወፍ በረር ፈልጌ አላገኘሁም።
የአውቶቡስ መናኽሪያው በሰው ተጨናንቋል። የመኪና ረዳቶች አስፋልት ዳር ወጥተው ከሐይቅ እስከ ቆቦ፣ ከኮምቦልቻ እስከ ከሚሴ የሚጓዙ ደንበኞቻቸውን ይጣራሉ። ግራ ቀኙን በአንክሮ ብከታተልም የጦርነቱ ሰለባ የሆነ ቁስ ደሴ ከተማ ውስጥ ማየት አልቻልኩም።
በኋላ እንደገባኝ የጦርነቱ ጠባሳ ሦስት ቦታ ላይ ተቀምጧል። አንደኛው በህንፃዎች ውስጥ ነው፣ ሁለተኛው በሰው አዕምሮ ውስጥ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ልብስ በሸፈነው የሰዎች አካል ላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, ቢቢሲ
ያረፍንበት ጎልደንጌት ሆቴል ዘረፋና ውድመት ቢደርስበትም አሁን ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። በሁሉም የሆቴሉ ክፍሎች አንድም ቴሌቪዥን የለም። አስተናጋጆቹን ጠይቅኳቸው። "የህወሓት ወታደሮች ሁሉንም ዘርፈዋቸዋል" አሉኝ። በእርግጥ የሆቴሉ ግድግዳዎችም ይህንን ይመሰክራሉ። እያንዳንዱ የሆቴሉ ክፍሎች ባዶ የቴሌቪዥን ማስቀመጫ ፍሬም ብቻ ተለጥፎባቸው ይታያሉ።
ሆቴሉ ዋና ዋና አገልግሎቶችን ይሰጣል። ድንገት የጎደለ አገልግሎትን ከጠየቅን የሚሰጠን መልስ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። "ጁንታው አውድሞታል" የሚል ነው። በህንፃዎች የተሸፈነው የጦርነቱ ጠባሳ ወደ ውስጥ ሲዘለቅ በአብዛኛው በእዚህ ሁኔታ የሚገለጽ ነው።
ደሴ በምሽት
ደሴ ቀን ደማቅ ነች። ምሽት ግን በጊዜ ነው የምትተኛው። ሦስት ሰዓት ላይ ብዙ አገልግሎቶቿ ይዘጋጋሉ። ለወትሮው የሚጨናነቀው ዋና መንገዷ በእዚህ ሰዓት ባዶ ነው። በመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉት ህንፃዎች መብራታቸውን አጠፋፍተው ስለሚዘጋጉ ለዋናው መንገድ የሚመግቡት ብርሃን ይቀንሳል።
በእዚህም ምክንያት ከዋናው አስፋልት ውጪ የሚገኙ መንገዶች በጨለማ የተዋጡ ናቸው። የሰዎችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም እጅግ የተገደበ ነው። የፀጥታ አካላት አልፎ አልፎ በቡድን ይታያሉ። ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ ትመስላለች።

ደሴ በጊዜ መተኛቷ ማልዳ እንድትነሳ ምክንያት አልሆናትም። አረፋፍዳ ነው የምትነሳው። የምሥራቋ ጮራ የጦሳ ተራራን ጫፍ ዘይራ በእርጋታ ተንከባላ ደሴ ከደረሰች በኋላ ነው ከተማዋ መንቃት የምትጀምረው።
ደሴን ከመሰናበታችን በፊት ይመቸናል ባልነው ቦታ ሁሉ ተገኝተን የፎቶና የቪዲዮ ምስሎችን ቀረፅን። አንድም ሊያስተጓጉለን የሞከረ ሰው አልነበረም። ነፃነታችን አጃኢብ የሚያሰኝ ነበር። ከሕዝቡ ጋር አብረው የሚንቀሳቀሱት የመከላከያ እና ልዩ ኃይል መለዮ ለባሾች የተለየ ፊት ሳያሳዩን የደሴ ቆይታችንን አጠናቀቅን።
ጉዞ ወደ ወልዲያ
ወልዲያ ከደሴ ወደ ሰሜን አቅጣጫ 120 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። ሐይቅ፣ ውጫሌና መርሳ በሁለቱ ከተሞች መካከል የሚገኙ መካከለኛ ከተሞች ናቸው። ሐይቅ መሃል ከተማ ላይ የጦርነቱ ምልክት በግልጽ ይታይባታል።
በረጅም ተሽከርካሪ ላይ የተጫነ መድፍ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ቆሟል። ሌላ ወታደራዊ የውሃ/ነዳጅ መጫኛ ቦቴም እዚያው ከተማ ላይ ይገኛል። ከተማዋን ተዘዋውሮ የመቃኘት ጊዜ አልነበረንም። ከዋና መንገዱ ዳር እና ዳር የሚታየው እንቅስቃሴዋ የተለመደው አይነት ነው።
ከከተማዋ ወጥተን ትንሽ እንደተጓዝን ታንክና ኦራል ተመትተው ቆመዋል። ከጀርባ የአካባቢው አርሶ አደር የእርሻ ሥራቸውን ይከውናሉ። የውጫሌን ዳገት ወጥተን ወደ ውርጌሳና መርሳ ተጓዝን። ውርጌሳም ጉዳት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች እዚህም እዚያም ቆመው ይታዩባታል።
ሊብሶ በሐብሩ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። ጦርነቱ የከፋ ጉዳት ካደረሰባቸው መካከልም ነች። ምናልባትም ካየናቸው ከተሞች የጦርነቱ ትውስታ በጉልህ የሚታይባት ናት።

የህወሓት ኃይሎች ከሰሜን ሸዋ ተሸንፈው ሲመለሱ የአካባቢው ነዋሪ በእዚህች ከተማ አድፍጦ ተኩስ ይገጥማቸዋል። ይዘዋቸው የነበሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በእሳት ጋዩ። እሳቱ ግን መኪኖቹ ላይ አልቆመም።
ከመንገዱ ዳር ምሥራቃዊ አቅጣጫ ወደ ተደረደሩት አነስተኛ የንግድ ቤቶች ተሸጋገረ። በንብረትና በሰው ላይ ሰፊ ጉዳት ደረሰ። በቤቶቹ ውስጥ የነበረው የሲሚንቶና ሌላ ሸቀጥ በእሳት ተጠብሶ እንደተከዘነ ይታያል።
በቦታው ያገኘነው የአካባቢው ነዋሪ በአደጋው ከ10 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ነገረን። ሞቱን ያደረሰው እሳቱ ብቻ ሳይሆን ታጣቂዎቹም እንደነበሩ መስክሯል። እንደ እዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን ለመመልከት በየስፍራው እየቆምን ስለነበር ወልድያ ለመድረስ ከአራት ሰዓት በላይ ወስዶብናል። ከሰዓት 9:00 ሰዓት አካባቢ ነበር ወልድያ የደረስነው።
ወልድያ
ወልድያ ከአስር በላይ ለሚሆኑ የሰሜን ወሎ ወረዳዎች ማዕከል ነች። በአካባቢው የከተማ አውራም ነበረች። ወልድያ በብዙ መልኩ ቁልፍ የምትባል ከተማ ናት።
ከጅቡቲ ወደብ በአንፃራዊነት ቅርብ ከሚባሉ ከተሞች መካከል አንዷ ነች። በእዚህም ምክንያት አብዛኛው የውጭ ምርት ወደ አገር ውስጥ የሚገባባት በር ነች።
ከሰሜን ትግራይን፣ ከምሥራቅ አፋርን፣ ከደቡብ ደሴ እና አዲሰ አበባን እንዲሁም ከምዕራብ ባሕር ዳር እና ጎንደርን የምታገናኝ እምብርት ከተማ ነች። ባለፈው ክረምት የሰሜኑ ጦርነት ወደ ደቡብ አድማሱን እያሰፋ ሲመጣ ወልድያ በህወሓት እጅ የወደቀች የመጀመሪያዋ የዞን ከተማ ነች።
ሆቴል ውስጥ እቃዬን እንዳስቀመጥኩ ወዲያውኑ ወጣ ብዬ በከተማዋ የተወሰነ አካባቢ መጠነኛ ቅኝት አደረግኩ። የማውቃት ወልዲያ ፍፁም ተቀይራለች። በተለምዶ 'ፒያሳ' የሚባለው አካባቢ የመንገድና አደባባይ ቅርፁን አጥቷል።
ተሽከርካሪዎች ወዲህና ወዲያ ከማለታቸው ውጪ መለስተኛ የእግር ኳስ ሜዳ መስሏል። በተሽከርካሪዎችና በሰው ፋና እየቦነነ የከተማውን ግራ ቀኝ የሚያፍነውን አቧራ ለመቀነስ በቦቴ የሚመጣ ውሃ ይርከፈከፍበታል። እንዲያም ሆኖ የመንገዱን ዳር ይዘው የተገነቡ ሕንፃዎች አፈር ከመልበስ አልዳኑም።
መንገዱ ባለፈው ዓመት በግንባታ ላይ ነበር። የጦርነቱ መስፋፋት ባለበት አቁሞታል። ወልዲያ በመንግሥት እጅ ከሆነች ወራት ቢቆጠሩም መልሶ ግንባታው ስለመጀመሩ አመላካች ነገር የለም።
እንዲያም ሆኖ ወልዲያ እጅ አልሰጥም አይነት ትግል ላይ ናት። ልክ እንደ ደሴ ሙሉ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየጣረች ነው። የሕዝብ ትራንስፖርት ከሁሉም አቅጣጫዎች ይገባል፤ ይወጣል። ካፌዎች በረንዳ ላይ ወንበራቸውን ደርድረው ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ።
ወልድያ መብራት አላት። እኛ በሄድንበት ወቅት ግን ጠፍቷል። ያረፍንበት ሆቴል ጄኔሬተር ነበረው። ደሴ ያላየሁትን ዜና ወልዲያ ባገኝ ብዬ ወደሆቴል ተመለስኩ። ተመሳሳይ ነው። እዚህም የቴሌቪዥን ማስቀመጫ ፍሬሙ እንጂ ቴሌቪዥኑ የለም። መልሱን ስለማውቀው ለምን ብዬ አልጠየቅኩም።
የሆቴሉ እቃዎች በሙሉ እንደተዘረፉና አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ቤተ ክርስቲያን ተደብቀው የነበሩ መሆናቸውን የሆቴሉ አስተናጋጆች ቀደም ብለው ነግረውኛል።
ጉዞ ወደ ላሊበላ
ወደ ላሊበላ ያመራነው ቅዳሜ ከሰዓት ነበር። ቅዳሜ በአብዛኛው የገበያ ቀን ነው። ገበያተኛው የመንገዱን ጥግ ይዞ ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው።
ከገበያተኞች እና ከእረኞች ጋር ሰላምታ እየተለዋወጥን የሳንቃ ሸንኮራ አገዳን እየመጠጥን፣ የድልብ ጠመዝማዛ መንገድን ታጥፈን፣ ተራራማውን የግዳን ወረዳ እየቃኘን፣ ጥንታዊቷን የኩል መስክ ከተማን አቋርጠን፣ የተከዜ ወንዝን ተሻግረን፣ በገነተ ማርያም በኩል ተረማምደን ከጋሸና-ላሊበላ-ሰቆጣ የሚወስደውን ዋናውን መንገድ ተቀላቀልን።

ናኩቶ ለአብን አልፈን ወደ ጥንታዊቷ የንጉሥ ላሊበላ ከተማ ብቅ አልን። እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ወደ ላሊበላ ስንገባ መጀመሪያ ያገኘነው ባጃጆችን ነው።
ላሊበላ
የአስፋልት መንገዱ መጠናቀቅ ለከተማዋ ዕድገት የሚኖረውን ሚና እያሰብኩ ጉዟችንን ቀጠልን። ነገር ግን አስፋልቱ አልዘለቀም። የከተማዋ መግቢያ እንጅ መሃል ከተማው አሁንም አስፋልት እንደናፈቀው ነው።
ላሊበላ ከህወሓት ኃይሎች እጅ ወጥታ በመንግሥት ቁጥጥር ከገባች ሁለት ወር አልፏታል። እስካሁን መሠረታዊ የሚባሉ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ሥራ አልጀመሩም። ትልልቅ ሆቴሎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት የሚቆይ ጀኔሬተር ይጠቀማሉ።
የወልድያ ቆይታችንን አሳጥረን ወደ ላሊበላ ያመራነው የሰንበት ድባብ እንዳያመልጠን ነበር። ተሳክቶልናል። በጠዋቱ ከአራቱ ምድብ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በቀዳሚው ቤተ መድህኔዓለም ተገኝተናል።
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ለብዙ ጊዜ ያየኋቸው ቢሆንም አሁንም እንደ አዲስ ጎብኚ በአድናቆት ጎበኘኋቸው። በእርግጥ ይህ ለማንኛውም የላሊበላ ጎብኚ የሚያጋጥም ነው።
ዕለቱ ሰንበት ከመሆኑም በተጨማሪ የፆም መግቢያ ስለነበር በርከት ያለ ምዕመን ተገኝቷል። ለወትሮው የውጭ ዜጎች ያጥለቀልቁት የነበረው የላሊበላ ቤተ ክርስቲያን አሁን ግን አንድም ቱሪስት ለማየት አልቻልንም። ምክንያቱ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ለስምንት ወራት አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሆኖ መቆየቱ ነው።

ላሊበላ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገቢ ምንጯ ቱሪዝም ነው። ወረርሽኙና ጦርነቱ ይህንን ገቢዋን እንዳታገኝ ተደራርበውባታል። ነዋሪዎች "ወረርሽኙ አቁስሎ ጦርነቱ ገደለን" በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል።
መጠኑ ተሰልቶ የማይገለጽ ግን ደግሞ ወደ እያንዳንዱ ነዋሪ ኪስ በተለያየ መንገድ ሊገባ የሚችል የቱሪዝም ሃብት በሁለቱ ክስተቶች ምክንያት ላሊበላ አልደረሰም። በእዚህም ምክንያት ብዙ ነገሮች መልካቸውን የቀየሩ ይመስላሉ።
ወጣቶች አዲስ ሰው በተመለከቱ ወቅት ተመራጭ አስጎብኚ ለመሆን ይሻማሉ። መስቀል፣ ባህላዊ ቅርጻ ቅርጾችን እና ሌሎች ማጌጫዎችን የሚሸጡትም ይገዟቸው ዘንድ ደንበኞችን አብዝተው ይማፀናሉ። ሁሉም በተቻለው አቅም እንግዶችን አግዞ አስርም አምስትም ለማግኘት ይሯሯጣል። ግን እንግዳ ከየት ይምጣ?
ከላሊበላ ቱሪዝም የመጀመሪያዎቹ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ሆቴሎችና አስጎብኝዎች ናቸው። የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ እንግዶችን የሚያስተናግዱት ቅንጡ የላሊበላ ሆቴሎች ከጦርነቱ በኋላ የህወሓት ኃይሎች መዘረፋቸውን ይናገራሉ።
መንግሥት አካባቢውን መልሶ ከተቆጣጠረ ከሁለት ወር በኋላም መልሶ መቋቋም ተስኗቸው አሁንም በራቸውን እንደቆላለፉ ናቸው። ሮሐ፣ ማውንት ቪው እና ቤን አበባ ሆቴሎች በእዚህ ደረጃ የሚጠቀሱ ናቸው።
የመጣ የሄደውን 'ዓለምዬ ሶራ'ን የሚያስጨፍሩት ባሕላዊ ምሽት ቤቶች አዝማሪዎቻቸውን አሰናብተው ሥራ ካቆሙ ወራት ተቆጥረዋል።
ከጦርነቱ እና ወረርሽኙ የተጠቀሙት የላሊበላ በቅሎዎች ብቻ ናቸው ይላሉ ነዋሪዎች። ወደ አቡነ ዮሴፍና አሽተን ተራሮች የሚሄዱ እንግዶችን ማመላለስ መደበኛ ሥራቸው የነበረው የላሊበላ በቅሎዎች የእርፍት ጊዜ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ጎብኚ የለማ!
የላሊበላ ነዋሪዎች በህወሓት ወታደሮች ስር ያሳለፉትን ጊዜ በሁለት ምዕራፍ ይከፍሉታል። የመጀመሪያው አራት ወራትን ያሳለፉበት ሲሆን "ተመስገን" የሚሉት ነው።
ሁለተኛው ከአንድ ሳምንት ነፃነት በኋላ ድጋሚ በህወሓት እጅ የወደቁበትና "ከባድ ጊዜ" የሚሉት ነው። የህወሓት ኃይሎች ወደ ላሊበላ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ያለጦርነት መሆኑን ነዋሪዎች እንደ መልካም ነገር ይቆጥሩታል። አብዛኛው ነዋሪ ይህ የሆነው "ቅዱስ ላሊበላ እንዳይተኩሱ ስላሰራቸው ነው" ብሎ ያምናል።
የመጀመሪያውን አራት ወር የሚያመሰግኑት ጉዳት ስላልደረሰ አይደለም። "እህቶቻችን ተደፍረዋል፣ ወንድሞቻችን ተገድለዋል፣ ንብረታችን ተዘርፏል። በሌላ ከተማ ከምንሰማው አንፃር ግን የእኛው ተመስገን የሚያስብል ነው" የሚለው አገላለፅ ካናገርኳቸው ሰዎች የብዙዎቹን ይወክላል።
የመንግሥት ወታደሮች ከአራት ወራት በኋላ ታኅሳስ 03/2014 ዓ.ም ላሊበላን ተቆጣጠሩ። ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን ገለጸ። ወጣቶች ለፀጥታ ኃይሎች በየመንደሩ እየተዘዋወሩ ምግብ አሰባሰቡ። በእዚህ ሁኔታ የቀጠሉት ግን ለአንድ ሳምንት ነበር።
ከአንድ ሳምንት በኋላ የህወሓት ተዋጊዎች በድጋሚ ላሊበላን ያዙ። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የላሊበላ ከባዱ ጊዜ ይህ ወቅት ነበር። "የአራት ወሩን ሂሳብ ነው ያወራረዱብን" በማለት ይገልጹታል። በእርግጥ በዚህ ወቅት በላሊበላን የቆዩት አንድ ሳምንት ብቻ ነበር። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግን በአራት ወሩ ያልደረሰው ጉዳት የተከሰተው በእዚህች አንዲት ሳምንት ነው።
አሁን ላሊበላ በሙሉ አቅሟ ለመንቀሳቀስ ብርቱ ጥረት ላይ ነች። የሁሉም ነዋሪ ፍላጎት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲመለስ ነው። ያን ለማድረግ ብዙ ነገሮች የተስተካከሉ ይመስላሉ። ሁለት ጉዳዮች ግን አሁንም መፍትሄ ይሻሉ፤ መብራት እና ውሃ።
ደሴ የጀመርነውን ጉዞ ላሊበላ ላይ አጠናቅቀን ወደ አዲስ አበባ እየተመለስን ነው። ሙሉ አስፋውን ደወልኩላት። ሙሉ አሁን በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆና ነው ያወራችኝ። ወደ መኖሪያዋ [ሐይቅ] ተመልሳ ሥራ ጀምራለች።
ከደሴ የወጣችው በድንገት ስለነበረ ቤት ንብረቷን የመደበቅም ሆነ ለጉዞዋ የሚሆናትን ስንቅ እና ልብስ የምታዘጋጅበት ጊዜ አልነበራትም። አዲስ አበባ ስትቆይ መቀየሪያ ልብስ የሰጠቻት እህቷ መሆኗን ሙሉ ነግራኛለች። ወደ ቤቷ የተመለሰችውም ያንኑ ይዛ ነው።
ከቤቷ ስትደርስ ምንም ንብረት አላገኘችም። ግን ቢያንስ ሆስፒታል የመውለድ ዕድል በማግኘቷ እና ሕይወቷን ማትረፍ በመቻሏ ራሷን እንደ እድለኛ ትቆጥራለች። አሁን ልጇ አምስተኛ ወሯ እየደረሰ ነው። 'አብላካት' ስትል ሰይማታለች። "እንድንተርፍ አምላክ የላካት" የሚል ትርጉም እንዳለው ሙሉ ነግራኛለች።
















