8 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ይሻሉ

8 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን እርዳታ ይሻሉ

የፎቶው ባለመብት, YONAS TADESSE

የምስሉ መግለጫ, 8 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን እርዳታ ይሻሉ

በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በቀጣይ አንድ ዓመትም የ1.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

አቶ ምትኩ ካሳ አክለውም ወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ የእርዳታ ስራውን አላስተጓጎለም ብለዋል።

በሀገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የድርቅ ክስተት ተደጋጋሚነቱ እየጨመረ መጥቷል ሲሉ የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ ከፍተኛ እርዳታ የሚፈልግ ሕዝብ የሚገኘውም በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ገልፀዋል።

"ከጥር 2010 እስከ ጥር 2011 ድረስ ባለው ጊዜ ለ7.8 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ለማቅረብ 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል። ከዛ ውስጥ መንግሥት ለመጀመሪያው ዙር 138 ሚሊዮን ዶላር መድቧል" ይላሉ ኮሚሽነሩ።

ከተጎጂዎቹ መካከል 6.8 ሚሊዮን የሚሆኑት ከድርቅ፣ መሬት መንሸራተት እንዲሁም ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ ነው እርዳታ የሚያሻቸው የሚሉት አቶ ምትኩ የተቀሩት 1 ሚሊዮን ደግሞ ከግጭት ጋር በተገናኘ መኖሪያቸውን ጥለው የተፈናቀለቁ ናቸው ሲሉ ነግረውናል።

እርዳታ ከሚያሻቸው መከካል 41 በመቶ ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ሲሆን 23 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ 13 በመቶዎቹ በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል እንዲሁም 9 በመቶ ትግራይ ክልል የሚገኙ ናቸው።

አሁን ሃገሪቱ ላይ ያለው ሁኔታ የእርዳታ አሰጣጡ ሂደት ላይ ተፅዕኖ ምን ያህል ነው ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ ኮሚሽነሩ ምላሽ ሲሰጡ "ከድርቅ ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ጎልቶ የሚታየው በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ በመሆናቸው ያን ያህል ችግር አልፈጠረብንም። ከግጭት ጋር ተያይዞ በነበረው ሁኔታ ግን አንዳንድ አካባቢዎች መስተጓጎል አጋጥሞን ነበር" ብለዋል።

"ምንም እንኳ ችግር ቢያጋጥመን ከክልሎች እና ፌዴራል አካላት ጋር እንዲሁም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር እርዳታው እንዲደርስ አድርገናል። አሁንም ይህንን በማድረግ ላይ ነን" ባይ ናቸው ኮሚሽነሩ።