ያልተነገረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሌላኛው ገጽታ
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ አስካሁን ማብቂያ ያላገኘው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን ማስከተሉ ሲዘገብ ቆይቷል።
የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያት የነበረውን ውጊያና የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ቢቢሲ ነዋሪዎችን አናግሮ ይህንን የቪዲዮ ዘገባ አቅርቧል።
ለስምንት ወራት ያህል በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ወደ አማራና የአፋር ክልሎች ተዛምቶ አሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው።
ጦርነቱ በትግራይ ክልል ውስጥ በነበረበት ጊዜ በተፋላሚ ኃይሎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች መፈጸማቸውን ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በስፋት ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተመሳሳይ የህወሓት ኃይሎች ከትግራይ ክልል ተሻግረው በአፋር እና በአማራ ክልል ውስጥ ጥቃት በከፈቱበትና በቆዩባቸው ጊዜያት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
ቢሆንም ግን ሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግፎችና ጭፍጨፋዎችን አለመፈጸማቸውን ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት ሰዎች የተገደሉባቸው፣ ንበረት የወደመባቸውና የተለያዩ አይነት ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ነዋሪዎች አሁንም ከደረሰባቸው ሰቆቃ አልወጡም።