ኤችአር 6600 'ጦርነት የሚያስቆም' ወይስ 'ኢትዮጵያን የሚጎዳ' ረቂቅ ሕግ'?

የፎቶው ባለመብት, congress.gov
የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ አስተዋውቀዋል።
ይህ ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ ቢሆን የጦርነቱ ተሳታፊዎች ተገደውም ቢሆን ወደ ድርድር እንዲመጡ ያስችላል የሚሉ እንዳሉት ሁሉ፤ በረቂቅ ሕጉ ላይ የፕሬዝደንቱ ፊርማ ቢያርፍ፤ ተራው ዜጋ ሰርቶ እንዳይገባ እና በልቶ እንዳይደር ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ብለው የሚሞግቱ አሉ።
በቅድሚያ የረቂቅ ሕጉ ይዘት ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት አጥብቀው የተቃወሙት ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንት ባይደን የሚጸድቅ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ በሁለቱ አገራት ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች።
'የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሕግ' በሚል ርዕስ የቀረበው ረቂቅ ሕግ፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ በደኅንነት እና ፀጥታ ላይ የምታደርገው ድጋፍ ላይ ገደብ ይጥላል።
ይህ ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ ከሆነ አሜሪካ ተሰሚነቷን እና ድምጽ የመስጠት መብቷን ተጠቅማ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ብድሮች ወይም የብድር ማራዘሚያዎች እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፎች እንዳያገኙ እንድትሰራ ይጠይቃል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ በኢትዮጵያ መረጋጋት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳይኖር ምክንያት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ የንብረት እግድ እና የቪዛ ማዕቀቦች ይጣላሉ።
'ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ አደገኛ ረቂቅ ሕግ ነው'
ብርሃኑ ታፈሰ (ዶ/ር) ይህ ረቂቅ ለአገር አደገኛ ስለሆነ ሕግ ሆኖ መውጣት የለበትም ይላሉ።
በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑት ብርሃኑ ታፈሰ (ዶ/ር)፤ ኤችአር 6600 በአገር ደረጃ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በማንሳት መረጃ የሚያቀርበው ጌትፋክት አባል ናቸው።
ጌትፋክት ለትግራዩን ጦርነት መከሰት ምክንያቱ ህወሓት ነው ብሎ ያምናል።
ብርሃኑ ታፈሰ (ዶ/ር) ምንም እንኳ የረቂቅ ሕጉ ርዕሱ 'ሰላም ማስፈን እና ዴሞክራሲን ለመገንባት' ቢልም ጠቅላላ ይዘቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።
"ኢትዮጵያውያንን በጠቅላላ የሚጎዳ አደገኛ ረቂቅ ሕግ ስለሆነ መጽደቅ የለበትም" ይላሉ።
'ረቂቁ እንደውም የዘገየ ነው'
መዓዛ ግደይ በበኩሏ ይህ ረቂቅ ሕግ 'እንደውም የዘገየ ነው' በማለት ረቂቁ ሕግ ሆኖ መውጣት እንዳለበት አበክራ ትከራከራለች።
ተመራማሪ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነችው መዓዛ ግደይ፤ ከኦምና ትግራይ ጋር ትሰራለች። ኦምና የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ የተመሰረተ ድርጅት ነው።
በዚህ ጦርነት በትግራይ ሕዝብ ላይ 'የዘር ማጥፋት ወንጀል' ተፈጽሟል ብሎ የሚያምነው ኦምና፤ በአድቮኬሲ እና ለትግራይ ተወላጆች የምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ይሰራል።
"ይህ ረቂቅ ሕግ እንደውም የዘገየ ነው። ይህን ጦርነት ለማስቆም፤ የፌደራሉ መንግሥት እና አጋሮቹ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያቆሙ ይህ ሕግ ያስገድዳል" ትላለች መዓዛ።

የፎቶው ባለመብት, AEPAC/FB
በአገር ላይ ጉዳት?
ብርሃኑ ታፈሰ (ዶ/ር) ይህ ረቂቅ ሕግ ጦርነቱን ያስቆማል የሚለውን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም ይላሉ።
"በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ ማዕቀብ መጣል ሰላም ያመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ችግሩ ሌላ፤ መፍትሄ ብሎ ያቀረቡት ደግሞ ሌላ" ይላሉ።
ለምሳሌ ይላሉ ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ "ኢትዮጵያ በደኅንነት ረገድ ከአሜሪካ ጋር ያላት ትስስር ላይ ረቂቅ ሕጉ ክልከላ ይጥላል። ኢትዮጵያ ብዙ የደኅንነት ስጋቶች ባሉበት የአፍሪካ ቀንድ የሰላም አስከባሪ ሚና ስትወስድ የቆየች አገር ነች። ይህ ድጋፍ ተቋረጠ ማለት፤ ቀጠናው ሰላም እንዲያጣ ነው የሚያደርገው" ይላሉ።
ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የውጪ የፋይናንስ ድጋፎችን እንደምትቀበል የሚገልጹት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ "በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ ግንባት ዙሪያ የመሠረተ ልማቶች ግንባት ለማስቀጠል ብድር ያስፈልጋል" ይላሉ።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ግንባታዋን እንዳታስቀጥል እክል የሚፈጥር ከሆነ ተጎጂው መንግሥት ሳይሆን ተራው ዜጋ ነው ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊስ ለውጥ በማድረግ በተለያዩ ዘረፎች ግዙፍ የውጭ ኩባንያዎች ገበያውን እንዲቀላቀሉ እየፈቀደች መሆኑን በማስታወስ፤ ረቂቅ ሕጉ ኢትዮጵያ ላይ የሚጥለው የኢንቨስትመንት ገደብ የረዥም ጊዜ ጉዳት በአገር ላይ ያደርሳል ይላሉ ብርሃኑ (ዶ/ር)።
"በአሜሪካ የምንኖር 'ለመንግሥት ድጋፍ ታደርጋላችሁ ብሎ' ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳናደርግ የሚከለክል ሕግ ነው። ኢሚግሬሽንን በተመለከተም፤ ይህ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያውያን ከአገር የመውጣት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው" በማለት ይናገራሉ።
መዓዛ በበኩሏ፤ ይህ ረቂቅ ሕግ አገር ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሳይሆን፤ "አምባገነን እና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሚደረገው መንግሥትን ነው" ትላለች።
"ለአገር የሚያስብ፤ የሚጨነቅ፤ በዜጎች ላይ ግፍ እንዲፈጸም አይፈቅድም። በኢትዮጵያ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደር ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲ እንጂ ጦርነት እንዲቆም የሚያስገድድ የውጪ አገር ሕግ አይደለም" በማለት መዓዛ ትከራከራለች።
"የሕጉን ዝርዝር ከተመለከተን አብዛኛው ትኩረቱ፤ በመንግሥት እና ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ተፈጽመዋል በተባሉ ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ላይ የሚያጠነጥን ነው። ስለዚህ ረቂቅ ሕጉ በአገር ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ይልቅ ግለሰቦችን፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥትን ነው ተጠያቂ የሚያደርገው" በማለት ሃሳቧን ታስረዳለች።
"ኢትዮጵያ እያገኘች ያለችውን ብድር እና ድጋፍ በትግራይ እየተካሄደ ላለው ጦርነት ማስፈጻሚያ እየሆነ ነው ያለው" የምትለው መዓዛ፤ ጦርነቱ እስካልቆመ ድረስ ረቂቅ ሕጉ ብድር እና ድጋፍ ኢትዮጵያን መከልከሉ ትክክል ነው ስትል ሃሳቧን ታጠናክራለች።
"ሰላም የሚሻ መንግሥት ከሆነ ሰላም የሚያመጡ አማራጮችን መውሰድ አለበት። የሰላም ሻምፒዮን ነኝ የሚለው መንግሥት ሚሊዮኖችን እያስራበ ነው። . . . በሲቪሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይህ ረቂቅ ሕግ የሚጎዳው አገርን ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትን ነው።"
'ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ጥረትን ያጨናግፋል'
ብርሃኑ (ዶ/ር) መንግሥት ከዚህ ቀደም የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጎ ከትግራይ ከወጣ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በአጎራባች ክልሎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን፣ በቅርቡም የህወሓት ኃይሎች በአፋር በኩል አዲስ ወረራ መሰንዘራቸውን እና የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናትን ከእስር መፍታቱን በማስታወስ፣ ይህ ረቂቅ ወደ ሕግ ቢቀየር የመንግሥትን የሰላም ጥረት የሚያከሽፍ ነው በማለት ይሞግታሉ።
መዓዛ ግን ይህ እንደ መከራከሪያ መቅረብም የለበትም ትላለች።
"አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ በጣለው ይፋዊ ያልሆነ ዕቀባ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል። በትግራይ ያሉ ሐኪሞች መድሃኒት አጥተው ሰዎች እየሞቱ፤ የትግራይን ሕዝብ ሆነ ብለው እያስራቡ እንዴት ስለ ሰላም ወይም ግጭት በሰላማዊ መንገድ ስለ መፍታት ልናወራ እንችላለን?" በማለት ትጠይቃለች።
መዓዛ ይፋዊ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቃባ ሳይነሳ፣ የውጭ ኃይሎች ከያዟቸው ስፍራዎች ሳይለቁ ስለ ሰላም ማውራት የሚቻል አይመስለኝም ትላለች።
'ረቂቁ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ የተቻለንን እናደርጋለን'
መዓዛ ግደይ ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ በአሜሪካ መንግሥት ተፈጻሚ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ትላለች።
"ጦርነቱን ተከትሎ በንፁኀን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ ማንነትን መሠረት ያደረጉ እስሮች በራሳቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እኛም የሕዝባችን ስቃይ እንዲሰማ የተቻለንን ነገር እያደረግን ነው። በዲያስፖራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የአድቮኬሲ ስራ እየሰሩ ነው። እኛም በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር እየተነጋገርን ነው" ትላለች።
በሌላ በኩል ይህ ረቂቅ ሕግ ሆኖ እንዳያልፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ብርሃኑ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
ብርሃኑ (ዶ/ር) ይህ ረቂቅ ሕግ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰበት ሁኔታ በራሱ ከዚህ ቀደም የውጭ መንግሥታትን በሚመለከት ከሚረቀቁት የሕግ አካሄድ በተለየ መንገድ ነው ይላሉ።
"ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ረቂቅ ሕጎች ሲወጡ የኢትዮጵያ-አሜሪካ ማሕብረሰብ አባላት አስተያየት ለመቀበል ጥሪ ይቀርብ ነበር። የሚወጣው ረቂቅ ሕግ 'በትክክል ኢትዮጵያውያንን ይረዳል? አሜሪካንን ይጠቅማል' በሚለው ላይ ሰዎች ሃሳባቸውን መግለጽ ነበረባቸው። ይህ ግን ግራ በሚያጋባ መልኩ ይህ ሳይሆን ወደ ምክር ቤቱ ሄዷል" ይላሉ።
ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅም ፊርማዎችን የማሰባሰብ፣ ጉዳዩን ለምክር ቤት አባላት የማሳወቅ፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስክሪፕት ተጽፎ ሰዎች ለተመራጭ አካላት ስልክ እንዲደውሉ በማድረግ ኤችአር6600 ተፈጻሚ እንዳይሆን ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ።















