"በረሃብ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው የሚቀሩ የጤና ባለሙያዎች አሉ" አይደር ሪፈራል ሆስፒታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው ዋነኛ የሕክምና ተቋም አይደር ሪፈራል ሆስፒታል በቀን ከ4 እስከ 6 አስክሬኖች የሚሸኝበት ደረጃ እንደደረሰ ለቢቢሲ ገለጸ።
በመድኃኒትና ሕክምና አገልግሎት እጥረት ከሞቱት መካከል የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበትም አስታውቋል።
ቢቢሲ ያነጋገረው የሆስፒታሉ የነርሲንግ አገልግሎት ኃላፊ ቴዎድሮስ ካህሳይ ከጦርነቱ በፊት ከትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሆስፒታል አሁን ግን እጅግ መዳከሙን ገልጿል።
ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው የሰሜኑ ጦርነት ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል እና ከዓለም ተቆራርጣ ባለችው ትግራይ ክልል በሕክምና ቁሳቁሶች፣ መድሃኒቶችን እና የሰብዓዊ እርዳታዎች እጥረት በርካቶች ለከፋ ችግር መዳረጋቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ የጤና ማዕከላት በአስፈላጊ መድኃኒት እጥረት ሳቢያ ሥራ ማቆማቸውን ያስታወቀ ሲሆን በትግራይ ክልል የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በበኩላቸው ህፃናትን ጨምሮ ህሙማን በከፍተኛ መድኃኒት እጥረት ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቆ፤ የትግራይ ኃይሎች ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች አፋር ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቆ ነበር።
ይህንን ተከትሎም የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዳደረጉና ከአፋር ክልል ኤረብቲ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት ደግሞ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ህወሓት ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት ዘላቂ፣ ያልተገደበ፣ ወቅታዊ እና በቂ የሆነ እርዳታ ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።
ቀደም ሲል የተደረገውን ስምምነት ተከትሎም ከሁለት ሳምንት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም 47 ምግብና ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ማድረሱን ገልጿል።
አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያዎችና የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ከስድስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ መጋቢት 24፣ 2014 ወደ ትግራይ መግባታቸውን አስታውቋል።
አሜሪካም በሰሜን ኢትዮጵያ ለተከሰተው ችግር የሚውል 313 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የሰብዓዊ እርዳታ ማድረጓን ከትናንት በስቲያ አስታውቃለች።
የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል የነርሲንግ አገልግሎት ኃላፊው ቴዎድሮስ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ለሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው ድጎማ እና የሕክምና ቁሳቁስ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰው ላለፈው አንድ ዓመት ግን ሆስፒታሉ ካለምንም በጀት እየሠራ እንደሆነ ተናግሯል።
" በአሁኑ ሰዓት 30 በመቶ በሚሆን አቅም ነው አገልግሎት እየሰጠን ያለነው፤የመድሃኒት ክምችታችን ወደ 10 በመቶ ወርዶ ነበር። ከዓለም ጤና ድርጅት የመጣ እርዳታ ተጨምሮበት ክምችቱ ወደ 20 በመቶ ደርሶ ነበር። ነገር ግን ይህ ለሆስፒታሉ የተሰጠው መድሃኒት ያለቀው በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው" ይላል።
ኃላፊው እንደሚሉት ድጋፍ የተደረጉላቸው መድሃኒቶች በዓይነትም እጅግ አነስተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።
ኃላፊው እንደ ካንሰር፣ ደም ግፊት ላሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች ምንም ዓይነት መድሃኒት አለመግባቱን በመግለፅም ለሳንታት ታይቶ የነበረው የሆስፒታሉ አገልግሎት መሻሻል ተመልሶ መውረዱን አክለዋል።
ለላብራቶሪ የሚውሉ ግብዓቶች ፣ መድሃኒቶች፣ ማሽኖችን ማንቀሳቀሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ፣ ተኝተው ለሚታከሙ የሚቀርብ ምግብ ፣ ለሠራተኞች የሚከፈል በሌለበት መስራትም አስቸጋሪ አንደሆነ ቴዎድሮስ ገልጿል።
"በረሃብ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው የሚቀሩ ባልደረቦቻችን አሉ"
በሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ነርስ የሆነው ገብረይ አቢዩ " ሰዎች ለሕክምና መጥተው እያየናቸው ሕይወታቸውን ሲያጡ እጅግ እናዝናለን" ይላል።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሆነው እየሠሩ እንደሆነ የሚናገረው አቶ ገብረይ "በረሃብ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው የሚቀሩ ባልደረቦቻችን ግን አሉ" ይላል።
"ከባድ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ሰዎች ሙያዊ ድጋፍ ፈልገው ሲመጡ ምንም ሳይደረግላቸው ሲቀር ሥራ ቦታ ብቻ ሳይሆን ቤት ሄደህም ሰላም አታገኝም። ለሊት ተኝተህ ወደ ህሊናህ የሚመጣ ብዙ ነገር አለ። ሕጻናት መጥተው በኦአርኤስ ወይም በሌላ ትንሽ ነገር ሕይወታቸውን ማትረፍ እየተቻለ ይህ ባለመኖሩ ስታጣቸው በጣም ከባድ ነው። እጆችህን አጣጥፈህ ነው ቆመህ የምታየው። ልብህን የሚያደማ እንጂ ደስ ብሎህ የምትሠራው ሥራ አይደለም።" ሲሉ በሆስፒታሉ ያለውን ችግር ያስረዳሉ።
ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፤ ድርብርብ ነው።
የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩም ለ11 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው ሠራተኞች እስከ 2 ሰዓት የሚወስድ መንገድ በእግር ተጉዘው ሆስፒታሉ እንደሚደርሱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
"የጤና ባለሙያዎችም በሕክምና አገልግሎት እጦት ሕይወታቸው አልፏል"
ቴዎድሮስ እንደሚለው የመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎት እጥረት የታካሚዎችን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችንም ሕይወት እየቀጠፈ ነው።
"በዚህ ሁለት ወር 2 ነርሶች ሞተውብናል። መዳን ይችሉ ነበር፤ ግን መድኃኒት ማግኘት አልቻሉም። በተለይ አንደኛዋ ነርስ ኤምአርአይ ማሽኑ እየሠራ ስላልሆነ በሽታዋን በግልጽ ማወቅ አልተቻለም። በዚህ ምክንያት ሕመሟ ጸንቶ ሞታለች። ሁለተኛው ነርስ ደግሞ ሊወስደው የሚገባ መድኃኒት እዚህ ሆስፒታል ስለሌለ ያጣነው ባልደረባችን ነው። አሁን በቀን እስከ 4 አልፎም እስከ 6 አስክሬን ከዚህ ሆስፒታል ይሸኛል። ከዚህ በፊት ግን በሁለት ወይም ሦስት ቀን አንድ ሬሳ ነበር የሚወጣው" ይላል።
በሕክምና እጦት ምክንያት ሕይወታቸው ከሚያልፍ የጤና ባለሙያዎች መካከል አብዛኞቹ የክሮኒክ በሽታዎች ተጠቂ መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጿል።
ትግራይ ባለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ሆስፒታሉ ለሚሰጠው አግልግሎት ከታካሚዎች የሚጠይቀው ገንዘብም እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ [ከቀድሞው ከ90 በመቶ ያነሰ) ነው።
"በሆስፒታሉ የማይገኙ መድኃኒቶችን ከውጭ ለመግዛት የተቸገሩ ሰዎች፣ ከሩቅ የትግራይ አካባቢ መጥተው መመለሻ ያጡ ሰዎች፣ የሞቱ ቤተሰቦቻቸውን አስክሬን ለመውሰድ የሚቸገሩ ሰዎችን ማየት የሠራተኞቹን ልብ በሐዘን ይሰብራል" ብሏል።
ለታካሚዎችና ለተወሰኑ ሠራተኞች ይቀርብ የነበረ ምግብ ላለፉት 10 ቀናት ውስጥ ስለተቋረጠ እስከ 240 ታካሚዎች ወደ ቤታቸው እንደተሸኙም አክሏል።
ከዚህ ቀደምም የአይደር ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ባወጡት መግለጫ በቀዶ ህክምና ወቅት የሚያስፈልጉ በደም ስር የሚሰጡ (intravenous fluids) እና የሰመመን መስጫ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ቀዶ ህክምና ማድረግ አለመቻላቸውን ነው። በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና ያልተሟላ የኦክስጂን አቅርቦት ለታካሚዎች ሞት ምክንያት ነው ብለዋል።
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ትራንስፖርትና የባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠው ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አስራ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።












