አሜሪካ ለትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልል ተጎጂዎች የሚሆን ተጨማሪ 300 ሚሊዮን ዶላር ለገሰች

የዩኤስኤይድ ድጋፎች

የፎቶው ባለመብት, USAID

ዩናይትድ ስቴትስት በሰሜን ኢትዮጵያ ለተከሰተው ችግር የሚሆን 313 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የሰብአዊ እርዳታ ማድረጓን ገለጸች፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት በሆነው (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) በኩል የተለገሰው ይህ ሰብአዊ እርዳታ በሰሜን ኢትዮጵያ በቀጠለው ግጭትና ያን ተከትሎ እየደረሰ ላለው ቀውስ፣ በዚህም ችግር ውስጥ ለገቡ ዜጎች የሚሆን ነው ተብሏል፡፡

ድርጅቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በቀጠለው ጦርነት 9 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ባለማግኘታቸው ለከፋ የምግብ ማጣት ችግር ተዳርገዋል፤ 2 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡

በተለይ በትግራይ 90 ከመቶ የሚሆነው ነዋሪ እርዳታን የሚሻ እንደሆነ ጠቅሷል ድርጅቱ።

በአፋር፣ አማራና ትግራይ በድምሩ ወደ 1 ሚሊዮን ዜጎች እስከ ሰኔ ድረስ ፈጣን እርዳታ ካላገኙ ቸነፈር ሊባል የሚችል የከፋ ረሀብ ሊገጥማቸው ይችላል ሲል ቀደም ብሎ መተንበዩን ድርጅቱ አስተዋሷል፡፡

ትናንት ሐሙስ ይፋ የተደረገው የአሜሪካ እርዳታ 7 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብና አልሚ ምግቦች እርዳታን ለማቅረብ፣ የአካባቢ ጤና ተቋማትን ግብአት ለማጠናከር፣ ተንቀሳቃሽ የጤና ክትትል ቡድኖች ተዛማጅ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት ይደግፋል ብሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሰብዓዊ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙና በጦርነቱ የተጎዱ ሕጻናትን ለመታደግ እንዲሁም አስፈላጊ ሰብዓዊ ቁሳቁሶችን ራቅ ባሉ ጠረፋማ አካባቢዎች ለማድረስ የሚያግዝ ይሆናል ሲል የልማት ድርጅቱ በጋዜጣዊ መግለጫው አትቷል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለማገዝ ቁርጠኛ ናት ያለው ድርጅቱ ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አጋር ድርጅቶች ጋር በመጣመር ይህን ሰብዓዊ እርዳታ በሦስቱ ክልሎች ለማድረስ እየተጋ እንደሚገኝ አስታውሷል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን፣ እንዲሁም ከፌዴራልና የአካባቢ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር በየብስ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሠሩ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ የአሜሪካ የልማት ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ኢ.ዲ) ከአጋሮች ጋር ለመነሻ ያህል ወደ ትግራይ በተላኩ ሁለት ኮንቮዮች ለ105ሺህ ዜጎች የሚበቃ የምግብና አልሚ ንጥረ ነገሮች መድረሱን አስታውሷል፡፡

ይህ በአጋሮቹ አማካኝነት የሚደረገው እርዳታ ተጠናክሮ በአሜሪካ የልማት ድርጅቱ ወጪ ከየብስ በተጨማሪ 600 ሜትሪክ ቶን የመድኃኒትና የአልሚ ምግቦችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ካለፈው ታህሳስ ጀምሮ አጋር ድርጅቶቹ ማድረሳቸውን ጠቅሷል፡፡

ይሁንና ትርጉም ያለው፣ ያልተቋረጠ በቂ የሚባል እርዳታ ለማድረስ የመንገዶች ክፍት መሆን እጅግ ወሳኝ እንደሆነ አስምሮበታል፡፡

በትግራይ ክልል የግንኙነት መስመሮችን መክፈት፣ የገንዘብ ዝውውር መንገዶችን ወደነበሩበት መመለስና ሌሎች ወሳኝ አገልግሎቶችን ማስጀመር ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

አሁን እየተለገሱ ያሉ ሰብአዊ ድጋፎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማድረስ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት ከሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋር በቅንጅትና ትብብር እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲደርሱ መሥራት ያሻቸዋል ያለው መግለጫው ትብብሩ በአፋርና በአማራ ክልል እርዳታ የሚሹትን ለመድረስም አስፈላጊ ነው ይላል፡፡

አሜሪካ ሰብአዊ እርዳታን ለኢትዮጵያ በማድረስ ትልቁን ድርሻ የምትይዝ አገር ስትሆን ከጦርነቱ ወዲህ ብቻ 995 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት እርዳታ መለገሷን ድርጅቱ ጠቅሷል፡፡

በዩክሬን ያለው ጦርነት የምግብ ዋጋ መናርን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳስከተለ ያስታወሰው መግለጫው ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ የምታስገባ አገር በመሆኗ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንደሚያደርጋትና ይህም ሰብአዊ እርዳታን ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ እንዲሆን እንደሚያደርገው ድርጅቱ ወቅታዊውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ተንትኗል፡፡

ይህም በመሆኑ ከችግሩ ዋንኛው የመውጫ ቀዳዳ የፖለቲካ ውይይት እንደሆነም አመላክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን ስቃይ ለማቆም የፖለቲካ መፍትሄ ዋናውና ብቸኛው አማራጭ እንደሆነም አስገንዝቧል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን ግጭት የማቆም ውሳኔን አወድሶ ይህን በጎ መንፈስ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንዲተጉና የሕዝብን ስቃይ እንዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡