በዩክሬን ጦርነት ወቅት ህንድ ዓለምን መመገብ ትችል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የእህል አቅርቦት መስተጓጎልና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬን ለማስተካከል ህንድ መዘጋጀቷን አስታውቃለች።
ባለፈው ሳምንት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሃገራቸው ለተቀረው አለም የእህል ምርቶችን ለማጓጓዝ መዘጋጀቷን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ህንድ ለ1.4 ቢሊዮን ህዝቦቿ "በቂ ምግብ" እንዳላት እና የዓለም ንግድ ድርጅት ከፈቀደ በመቼውም ወቅት ለአለም የምግብ ክምችት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
ከአለም አቀፉ ምርት ጋር ተያይዞ በዩክሬን ጦርነት ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን የሸቀጦች ዋጋ በአስር አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል።
በተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) የምግብ ዋጋ መረጃ መሰረት ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ ንሮ ከአውሮፓውያኑ 1990 በኋላ ከፍተኛ ማሻቀብ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁሟል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከስንዴ ላኪዎች መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ከዓለም አቀፍ ዓመታዊ የስንዴ ሽያጭ አንድ ሦስተኛውን ይይዛሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአለም አቀፍ ዓመታዊ የሱፍ አበባ ዘይት ሽያጭም 55 በመቶ፣ እንዲሁም 17 በመቶ በቆሎ እና ገብስ ምርቶችን ይሸፍናሉ።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመትም ሁለቱ አገራት ተደምረው 14 ሚሊየን ቶን ስንዴ እና ከ16 ሚሊየን ቶን በላይ በቆሎና ገብስ ወደ ውጭ ይልካሉ ተብሎ ይጠበቅም እንደነበር ፋኦ አስታውቋል።
"በሩሲያ ላይ የገጠመው የአቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም የተጣለባት የእቀባ ስጋት ወጪ ንግድ እንደማይኖር ማሰብ አለብን። ይህንንም ክፍተት ለመሙላት ህንድ በቂ የስንዴ ክምችት ሲኖራት ልትልክ ትችላለች" ሲሉ የተመድ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ኡፓሊ ጋልኬቲ አራትቺላጅ ይናገራሉ።
ህንድ በአለም ሁለተኛዋ ሩዝ እና ስንዴ አምራች ናት። በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ያላትን ምርት ስናይም 74 ሚሊዮን ቶን ስንዴና ሩዝ ክምችት አስቀምጣለች።
ከዚህ ውስጥ 21 ሚሊዮን ቶን የሚሆነው ምርት ለአገሪቱ መጠባበቂያ እንዲሁም ከ700 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ድሆች በተመጣጣኝ ዋጋ ምግብ እንዲያገኙ የሚሰራጭ ነው።
በተጨማሪም ህንድ በአለም አቀፍ ደረጃ ርካሽ የስንዴ እና ሩዝ ምርቶች አቅራቢዎች አንዷ ናት። በአሁኑ ወቅት ሩዝ ወደ 150 ለሚጠጉ ሀገራት ስንዴ ደግሞ ወደ 68 ሃገራት ትልካለች። በአውሮፓውያኑ 2020-2021 ወደ 7 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ወደተለያዩ አገራት ልካለች።
በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ ያለውን የምርት ፍላጎትን ለሟሟላትም ነጋዴዎች ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ወር ባለው ወቅት ከ3 ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ ውል መግባታቸውን የህንድ ባለስልጣናት ተናግረዋል። በ2021/20022 ያለው የግብርና ምርቶች ወጪ ንግድም ከ50 ቢሊዮን ዶላር አልፏል።
ህንድ በተያዘው አውሮፓውያኑ ዓመት 22 ሚሊየን ቶን ሩዝ እና 16 ሚሊየን ቶን ስንዴ ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንዳላት በህንድ የአለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ምርምር ምክር ቤት የግብርና ፕሮፌሰር የሆኑት አሾክ ጉላቲ አስረድተዋል።
"የዓለም ንግድ ድርጅት የመንግሥት ክምችት ወደ ውጭ እንዲላኩ የሚፈቅድ ከሆነ የበለጠ ከፍ ሊል ይችላል። ይህ ደግሞ የናረውን የአለም ዋጋ በማረጋጋት ረገድ እንዲሁም ምርቶችን ለማስገባት እየታገሉ ያሉ ሃገራትን ጫናን ይቀንሳል" ይላሉ።
ሆኖም አንዳንድ ጥርጣሬዎች መፈጠራቸው አልቀረም።
"በአሁኑ ጊዜ በቂ የምርት ክምችት አለን። ሆኖም ዓለምን ስለመመገብ ከፍተኛ ጉጉት ሊፈጠርብን አይገባም " ሲሉ በደልሂ ተቀማጭነቱን ያደረገው የፖሊሲ ምርምር ማእከል ከፍተኛ ባልደረባ የሆኑት ሃሪሽ ዳሞዳራን ይናገራሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ከተጠበቀው ያነሰ ምርት ይኖራል የሚሉ ፍራቻዎች አሉ። ህንድ የስንዴ ሰብሏን እየተጠባበቀች ሲሆን ባለስልጣናቱ በተከታታይ እንደተመዘገበው የሰብል ወቅት በዘንድሮውም ከፍተኛ የሚባለውን 111 ሚሊዮን ቶን ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ይዘዋል።
ነገር ግን እንደ ሃሪሽ ዳሞዳራን ያሉ ባለሙያዎች ይህንን ያህል ምርት ስለመገኘቱ እርግጠኛ አይደሉም።
በማዳበሪያ እጥረት እና ከመጠን በላይ ዝናብና በበጋው መጀመሪያ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ምርቱ በጣም ዝቅተኛ እንደሚሆን ያምናሉ።
"ምርቱን ከመጠን በላይ እንደሚሆን እየገመትነው ነው። ሆኖም በመጪዎቹ 10 ቀናት ውስጥ እናውቃለን" ይላሉ።
ባለሙያዎች የሚያነሱት ሌላኛው ጥያቄ የእርሻ መሰረታዊ ግብዓት የሆነው ማዳበሪያ ጉዳይ ነው። ህንድ ዲ-አሞኒየም ፎስፌት እንዲሁም ናይትሮጅን ፣ ፎስፌት ፣ ሰልፈር እና ፖታሽ የያዙ ማዳበሪያዎችን ከውጭ ታስገባለች። ጦርነቱንም ተከትሎ የህንድ የማዳበሪያ ክምችት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሩሲያ እና ቤላሩስ ከዓለማችን የፖታሽ ወጪ ንግድ 40 በመቶውን ይሸፍናሉ። በተጨማሪም በአለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቧል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሚቀጥለው የመኸር ወቅት የማዳበሪያ እጥረት በቀላሉ ምርትን ሊጎዳ ይችላል ተብሏል። ለዚህም መፍትሄ ለማበጀት አንዱ መንገድ ህንድ እንደ ግብፅ ወይም በአፍሪካ ካሉ ሀገራት ጋር "ማዳበሪያ ለስንዴ" አይነት ስምምነቶች ላይ መድረስ ነው ይላሉ ሃሪሽ ዳሞዳራን።
እንዲሁም ጦርነቱ ከተራዘመ ህንድ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ ረገድ የሎጂስቲክስ ፈተናዎች ሊገጥሟት ይችላል።
"ግዙፍ የእህል ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ እንደ ማጓጓዣ፣ ማከማቻ፣ መርከቦች ያሉ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን ያካትታል። እንዲሁም በተጨማሪ በከፍተኛ መጠን የመላክ አቅምን ይጠይቃል" ይላሉ ኡፓሊ ጋልኬቲ አራትቺላጅ
ይህም ማለት ከፍተኛ የጭነት ወጪዎች እንዴት ነው የሚሸፈነው የሚል ጥያቄን ያስነሳል።
በመጨረሻም ሌላ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ በህንድ ውስጥ የተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር ነው። የምግብ የዋጋ ግሽበት በመጋቢት ወር በባለፉት አስራ ስድስት ወራት ከፍተኛ የተባለው የ7.68 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህ በዋናነትም መንስኤው ዘይት፣ አትክልት፣ እህል፣ ወተት፣ ስጋ እና አሳ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ነው።
የሕንድ ማዕከላዊ ባንክ በዓለም አቀፉ መሰረታዊ የምግብ ግብዓቶች መጨመር ምክንያት በአገሪቱም ውስጥ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የሩስያ ወረራ በአለምአቀፍ የምግብ ዋስትና ላይ "ከባድ መዘዝ ሊኖረው ይችላል" ሲል አይኤፍፒአርኢ የተባለ የተባለ የጥናት ተቋም ገልጿል።
ከሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ውጭ የሚላኩ ስንዴ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ምርቶች ላይ ለረዥም ጊዜ መቋረጥ በአለም ላይ ያሉ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሰዎች ቁጥር ከስምንት ወደ 13 ሚሊዮን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ፋኦ ግምቱን አስቀምጧል።
በህንድ ውስጥ የተትረፈረፈ ሰብል እና በቂ የምግብ ክምችት ቢኖርም ከሦስት ሚሊዮን በላይ ህጻናት የምግብ እጥረት እንዳለባቸው መንግሥት አምኗል። የጠቅላይ ሚኒስትር የትውልድ ቦታ ጉጅራት በምግብ እጥረት ከሚሰቃዩ ህፃናት ካሉባቸው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
" ምግብ ዋስትና ላይ ቸልተኛ መሆን አይቻልም። ለድጎማ የተመደበውን ምግብ እንደፈለጉ ማድረግ አይቻልም"በማለት ሃሪሽ ዳሞዳራን ያስጠነቅቃሉ።
የህንድ ፖለቲከኞች የሚያውቁት አንድ ነገር ቢኖር ምግብ መኖር ወይም መታጣት እጣ ፈንታቸውን እንደሚወስን ነው፡። ከዚህ ቀደም የክልሎች እና የፌደራል መንግስታት በሽንኩርት ዋጋ መናር ምክንያት እንዲንገዳገዱና እንዲወድቁ ሆነዋል።












