ሩሲያ የሰመጠችውን የጦር መርከብ ሰራተኞች 'ለመጀመሪያ ጊዜ አሳየች'

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ሞስኮቫ የተሰኘችው ግዙፏ የጦር መርከብ በጥቁር ባህር መስመጧን ተከትሎ የመርከቡ ሰራተኞችን የሚያሳይ ምስልና ቪዲዮ አውጥቷል።
የሃገሪቱ ብሔራዊ አርማ የሆነችው ይህች መርከብ ከሰመጠች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመርከበኞቹ ምስል የታየው።
በዚህም ምስል ላይ በክሪሚያ የወደብ ከተማ ሴባቶፖል ውስጥ ትልቅ የመርከበኞች ቡድን በሰልፍ የታየ ሲሆን የባህር ኃይል ዋና አዛዡ አድም ኒኮላይ ዬቭሜኖቭ ጋር ተገናኝተዋል።
መርከቧ የሰመጠችው በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት በፍንዳታ ከተጎዳች ከሰዓታት በኋላ ሲሆን ይህ ሁኔታ የሩሲያን ሞራል በእጅጉ የሚያንኮታኩት ነው ተብሏል።
ሚኒስቴሩ በያዝነው ሳምንት ሐሙስ መገባደጃ ላይ እንዳስታወቀው ሞስኮቫ በማዕበል በተሞላው ውቅያኖስ ላይ መስመጥ የጀመረችው ከፍንዳታው በኋላ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ነው ብሏል።
ዩክሬን በበኩሏ መርከቧን በሁለት የኔፕቱን ሚሳኤሎች ከመታቻት በኋላ መስመጧን አስታውቃለች።
በወቅቱ ሩሲያ እንደገለፀችው መርከበኞቹ ወደ ክሬሚያ ዋና ወደብ ሴባስቶፓል መወሰዳቸውን ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም ነው መርከበኞቹ በህይወት መኖራቸውን ከሩሲያ በኩል ማረጋገጫ የተሰጠው።
የወጣው ቪዲዮም እንደሚያሳየው የባህር ኃይል አዛዡ አድም ኢቭሜኖቭ እና ሌሎች ሁለት መኮንኖች ወደ 100 የሚጠጉ የተሰለፉ መርከበኞች ፊት ለፊት ቆመው ያሳያል።
ይህ ሰልፍ መቼ እንደተካሄደ ግልጽ አይደለም።
በቪዲዮው መጨረሻ ላይ በሚታየው ቃለ ምልልስ ላይ አድም ኢቭሜኖቭ፣ መኮንኖች እና መርከበኞች በአሁኑ ጊዜ በሴባስቶፖል በሚገኘው የጦር ሰፈር እንዳሉ እና በባህር ኃይል ውስጥ አገልግሎታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, MAX DELANY/AFP
ሩሲያ በመርከቧ ላይ በተነሳው እሳት ወይም ከመስመጡ ጋር ተያይዞ በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰው ጉዳት ሪፖርት አላደረገችም።
ይሁንና አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው አሜሪካ የሰው ህይወት መጥፋቱን ታምናለች።
ዩክሬን በበኩሏ የመርከቧ ካፒቴን አንቶን ኩፕሪን ተገድሏል ያለች ሲሆን ቢቢሲ ግን ይህንን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
የጦር መርከቧ በሶቭየት ኅብረት ጊዜ ተገንብታ ወደ ሥራ የተሠማራቸው በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ነበር፡፡
ሞስኮቫ ግዙፍ ሚሳኤል ተሸካሚ የጦር መርከብ በሶሪያ ግጭት ጊዜ የሩሲያ ወታደሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ማገዟ ይነገራል፡፡
እጅግ ውስብስብና ግዙፍ የጦር መሣሪያዎችን መሸከም የምትችለው ሞስኮቫ ከ12ሺህ ቶን በላይ ክብደት አላት፡፡
እንዲህ ዓይነት ግዙፍ የጦር መርከብ ሲሰጥም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሞስኮቫ የመጀመርያዋ ናት፡፡












