የህንዷ ግዛት የሙስሊሞችን ቤቶች እየለየች ለምን ታፈርሳለች?

የፎቶው ባለመብት, Madhya Pradesh police via Twitter
የ72 ዓመቱ ሼክ መሀመድ ራፊቅ ቤታቸውን ሊያፈርሱ የመጡ ግለሰቦች የመጡባትን ጥዋት ያስታውሷታል።
በህንድ ማድህያ ፕራዴሽ ግዛት ለስላሳ መጠጦችን በመሸጥ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩት ሼክ መሀመድ ራፊቅ ሌሊቱንም በደንብ አልተኙም ነበር።
"ወቅቱ ረመዳን ስለሆነ ንግዶቻችን ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ ይጀምራሉ" ይላሉ።
እናም ፖሊሶች ሰኞ በጧት ማልደው ቤታቸው ሲደርሱ ሁሉም ተኝተው ነበር።
"ነገር ግን ከፍተኛ ድምጽ ስንሰማ የበሩ መዝጊያ እየተሰበረ እንደሆነ ተገነዘብን" በማለት ያስረዳሉ።
ከቤት ውጭ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ መኮንኖችና ቡልዶዘሮች ቤታቸውን ከበውታል።
ካርጎን በተሰኘችው ትንሽ ከተማ የምትገኘው ቤታችቸውን ከማፍረስ የሚያድን ኃይል አልነበረም። ቡልዶዘሩም ቤታቸውን አፈራረሰው። መጨረሻ ላይ የቀረው ፍርስራሽ ብቻ ነበር።
"በጣም ፈርተን ስለነበር ምንም ቃል አልተናገርንም። ቤቱን ድርምስምስ ሲያደርጉት በዝምታ ተመለከትን።" ይላሉ።
ሚያዝያ መጀመሪያ ላይ ከነበረው የሂንዱ ራም ናቫሚ ፌስቲቫል የተነሳውን ረብሻ ተከትሎም ነው በርካታ የሙስሊም ቤቶች እና ሱቆችም መፍረስ የጀመሩት።
በማህበራዊ ትስስር ገጽ የተጋሩ ምስሎችና ቪዲዮች የሚያሳዩት ትልልቅ ቢጫ ቡልዶዘሮች ወደ ሰፈሮች ገብተው ሲያፈራርሱና በርካታ ቤተሰቦችም አቅም የለሽ በሆነ ሁኔታ ሲያለቅሱ ነው።
ይህ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ተቺዎች በፕራዴሽ ገዥውና የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ቢጄፒ ፓርቲ 200 ሚሊዮን ሙስሊሞችን ለማግለል የሚያደርጉት ሙከራ ነው ሲሉም ተሰምተዋል።
መንግሥትም ቢሆን ጥፋተኝነቱን በሙስሊሞች ላይ አድርጓል፤ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናሮታም ሚሽራ ለኤንዲቲቪ የዜና ጣቢያ እንደተናገሩት "ሙስሊሞች እንዲህ ዓይነት ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ ፍትህን መጠበቅ የለባቸውም።" ሲሉ ተናግረዋል።
ህጋዊ አይደለም በሚል የተከራከሩ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ደግሞ በሙስሊሞች ላይ የተፈጸመ የጅምላ ቅጣት ሲሉ ጠርተውታል።

"አንድን ማህበረሰብ ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ እየቀጣችሁ ነው። ምንም አይነት ህጋዊ አሰራር ሳይኖር፤ ይህ ህገ-ወጥ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ምሳሌም ነው።" ሲሉ በኢንዶሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ከፍተኛ የህግ ባለሙያ አሻር ዋርሲ ይናገራሉ።
"መልዕክቱ ግልፅ ነው፤ በማንኛውም መንገድ ብትጠይቁን ወይም ብትገዳደሩን እንመጣላችኋለን፥ ቤታችሁን እናፈርሳለን፣ መተዳደሪያችሁን እንወስዳለን፥ ባዶ እናስቀራችኋለን ነው" ይላሉ።
ለዚህ መነሻ የሆነው በርካታ የሂንዱ እምነት ተከታዮች የሙስሊም ሰፈሮችን እና መስጊዶችን አልፈው በመዘዋወር አናሳ ያሉት የሙስሊም ማህበረሰቡ ላይ ጥቃት እንዲደርስ የሚያበረታታ ሙዚቃዎችን ማሰማታቸውን ተከትሎ ነው።
ጥቂት ቦታዎች ላይ አንዳንድ ሙስሊሞች እና የሂንዱ ሰልፈኞች እርስ በርስ በድንጋይ መወራወራቸው ተዘግቧል።
በርካታ ሙስሊሞች በወቅቱ በሂንዱ አክራሪዎች ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ፍቃድ ሰጥተዋል ሲሉ ፖሊሶችን ከሰዋል።
ከፍተኛ ንዴት የሚነበብባቸው ግለሰቦች ሰይፋቸውን ይዘው ወደ መስጊዶች ገብተው ሲያረክሱ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች መታየታቸው ከባለፈው እሁድ ጀምሮ አገሪቱን አስደንግጧታል።
የ28 ዓመቱ ሻህባዝ ካን እንደሚናገረው የሂንዱ አክራሪዎች በሰንድሃዋ ከተማ የሚገኘውን መስጊድ ሰብረው በመግባት ሙስሊሞችን በድንጋይ አሳደዋል ብሏል።
ነገር ግን በነገታው ሌላ አስፈሪ ክስተት መጣ የአካባቢው ባለስልጣናት ያለምንም ምክንያት መጥተው ቤቱን በቡልዶዘር ማፍረስ ጀመሩ።
"ባለቤቴ እና እህቴ እያለቀሱ ፖሊሶቹን እቃዎቻችን እንድናስወጣ ቢያንስ ቁርዓኑን እንድናወጣ ብንጠይቅም ምንም ሊሰሟቸው አልቻሉም" ሲል አሁን ተጠልሎ ከሚገኝበት መስጂድ ተናግሯል።
"ምንም የቀረን ነገር የለም። ነገር ግን ማንም ግድ ያለው አይመስልም። ፖሊስ ጣቢያ ስንሄድም ያባርሩናል" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Madhya Pradesh police via Twitter
የግዛቲቱ አስተዳደር እነዚህን ቤቶች የማፍረስ ስራዎች ድንጋይ በመወርወር እና በማቃጠል ተሳትፈዋል በተባሉት ላይ ያነጣጠረ የቅጣት አይነት ነው ብሏል።
"ድንጋዮቹ የወጡባቸው ቤቶች እራሳቸው ወደ ድንጋይ ክምርነት ይቀየራሉ" በማለት አስተዳዳሪው ሚሽራ ተናግረዋል።
ነገር ግን በህጋዊ መንገድም ምክንያት የተሰጠው ሲሆን ይህም ህገ ወጥ ግንባታን ባከናወኑና የህዝብ መሬት ላይ ቤት የሰሩ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ሲል ፖሊስ ተናግሯል ።
የካርጎኔ ወረዳ ሰብሳቢ አኑግራሃ ፒ "የሁለቱም ድብልቅ ነው" ይላሉ።
"ወንጀለኞችን አንድ በአንድ ማጣራት ጊዜ የሚወስድ ሂደት በመሆኑ ሁከትና ብጥብጥ የተከሰተባቸውን ቦታዎች ሁሉ በመድረስ ህገ-ወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ ለሁከት ፈጣሪዎች ትምህርት ለመስጠት ችለናል" ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሼክ መሀመድ በአካባቢያቸው ምንም አይነት ጥቃት፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዳልነበር ይናገራሉ።
አክለውም "እኔ ሕገ-ወጥ አለመሆኔን የሚያረጋግጡ የንብረት ይዞታ ፈቃዶች አሉኝ፤ ነገር ግን ፖሊሶች ከየትም መጥተው እኔን ሊሰሙኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ቤቴን ነጥቀው ወሰዱብኝ" ብለዋል።
ባለሙያዎችም ቢሆን ይህንን የግዛቲቱ ተግባር ጥያቄ አጭሮባቸዋል። ለሌላ የታሰቡ ህጎችን ተጠቅመው አንድን ሰው ወንጀል ፈጽሟል ብለው መቅጣት ትርጉም የለውም ይላሉ።
"ህጋዊነት እንደ ሽፋን እየተጠቀሙበት ነው። እነዚህ ቤቶች ከሃይማኖታዊ ሰልፎች በፊት ሕገ-ወጥ ነበሩ። መንግሥት በበቀል እርምጃ ነው ቤቶቹን እያፈረሰ ያለው ይህ ደግሞ ሁሉንም የፍትህ ሂደቶች መጣስ ነው" ሲሉ የፖለቲካ ሳይንቲስቷ ራህል ቬርማ ያስረዳሉ።
ዋርሲ በበኩላቸው ግዛቱ ህገወጥ ሕንፃዎችን የማፍረስ ስልጣን አለው ነገርግን ከዚያ በፊት ሊከተሏቸው የሚገቡ የተለያዩ እርምጃዎች አሉ ይላሉ።
ከነዚህም መጀመሪያ ህገወጥ ህንፃዎቹን ገንብተዋል ለተባሉት ማሳሰቢያ ወይም ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ምላሽ እንዲሰጡ ወይም የፍርድ ቤት ማመልከቻ እንዲያቀርቡ እድል መስጠትን ይጨምራል።
ፖሊስ ጥቃት ፈጽመዋል ለተባሉት ሰዎች ማሳሰቢያ መስጠቱን ቢገልጽም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቢያንስ ሦስት ቤተሰቦች ግን ይህንን አስተባብለዋል።
በተጨማሪም፣ በግዛቲቱ ህግ ወይም በማድህያ ፕራዴሽ ማዘጋጃ ቤት ኮርፖሬሽን 1956 ህግ መሰረት፣ ተከሳሹ ቅጣት እንዲከፍል እንደመጠየቅ ያሉ ሌሎች ድንጋጌዎችም የሰፈኑ ሲሆን፣ ይህንንም ባለስልጣናት መጀመሪያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲሉ ዋርሲ ጨምረው ያስረዳሉ።
"ቤት ማፍረስ የመጨረሻው አማራጭ ነው ተብሎ ይታሰባል።"
ነገር ግን የማድህያ ፕራዴሽ ግዛትም ይህንን ዘዴ ፍትህን ለማስፈን ነው በሚል ሲጠቀምበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። መንግስት ከዚህ ቀደም በመድፈር የተከሰሱ፣ ወንበዴዎችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን ቤቶችን አፍርሷል።
"እኛ እያየነው ያለነው በኡታር ፕራዴሽ ውስጥ የተጫወተውን አይነት ፖለቲካ ነው። ዩፒ ሞዴል ተብሎ የሚጠራው በአሁኑ ወቅት በሌሎች ግዛቶች እየተተገበረ ይገኛል" የሚሉት ቬርማ። "ዓላማው የቢጄፒ መሰረት የሆነውን ሂንዱትቫ (ጠንካራ የሂንዱ ብሔርተኝነት) ማስደሰት ነው።"
በኡታር ፕራዴሽ የሂንዱ ብሔርተኛ የሆኑት አስተዳዳሪው ዮጊ አድቲያናት በግዛቲቱ ውስጥ ወንጀልን ለማጥፋት ያለሙና ተልእኮ ያላቸው መነኩሴ አድርገው ነው ራሳቸውን የሚያዩት።
መንግሥታቸው ወንጀለኞች ናቸው ያላቸውን ቤቶች በየጊዜ የሚያፈርስ ሰሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ "ቡልዶዘር ባባ" ወይም የቡልዶዘር መነኩሴ" የሚል መጠሪያም እንዲሰጣቸው ሆኗል።
የማድህያ ፕራዴሽ አስተዳዳሪዎችም ቡልዶዘር ማማ ወይም ቡልዶዘር አጎት የሚል ስያሜም አግኝተዋል።
ሁለቱም ግዛቶች በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ፍቅር የሚቃወሙ ህጎችን እና መንግሥት በተቃዋሚዎች የተበላሹ ንብረቶችን ለማስመለስ ንብረቶችን መውረስ የሚፈቅድ አወዛጋቢ ህግን ጨምሮ ፀረ ሙስሊም የሚል ስያሜ ያላቸውን ፖሊሲዎች በማውጣት ይታወቃሉ።
ህጉ በኡታር ፕራዴሽ አከራካሪ የሆነውን የዜግነት ህግን በሚቃወሙ ሰዎች ጥቅም ላይ ውሏል።
ባለፈው አመት በማድህያ ፕራዴሽ ሲፀድቅ አስተዳደሪው ሚሽራ "በተቃውሞ ፣ በአድማ ወይም በግርግር ወቅት የመንግሥት ወይም የግል ንብረት ባወደመ ማንኛውም ሰው ላይ ተግባራዊ ይሆናል። አስፈላጊ ከሆነም የተከሳሹ ንብረት ይያዛል እና በሐራጅ ይሸጣል" ብለዋል።
ነገር ግን በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመቅጣት ማስጠንቂያ ሳይሰጡ ቤቶችን ማፍረስ በየትኛውም ህግ ምንም አይነት መሰረት እንደሌለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ዋርሲ "በጭራሽ ይህን ማድረግ አይችሉም" ይላሉ።
ባለሥልጣናቱ ህግን እንደፈለጉ እየተጠቀሙና የፍርድ ቤቶቹን ገለልተኝነት በመንጠቅ ሙስሊሞች በመንግሥት ያነጣጠረ ጥቃት እንዲደርስባቸው አድርገዋል ይላሉ።
"ይህን ለማድረግ መንግስት እድል እየጠበቀ እንደነበረ ነው የሚሰማን"ብለዋል ዋርሲ












