ቦሪስ ጆንሰን ብሪታኒያ የዩክሬን ወታደሮችን ዩኬ ውስጥ እያስለጠነች ነው አሉ

ዩኬ ለዩክሬን ወታደሮች ከምትሰጣቸው ስልጠናዎች መካከል ማስቲፍ የተሰኘው ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች አጠቃቀም ይገኝበታል። [ፋይል ፎቶ]

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ዩኬ ለዩክሬን ወታደሮች ከምትሰጣቸው ስልጠናዎች መካከል ማስቲፍ የተሰኘው ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች አጠቃቀም ይገኝበታል። [ፋይል ፎቶ]

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የዩክሬን ወታደሮች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ እንደሆነ ይፋ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የዩክሬን ወታደሮች እንግሊዝ ውስጥ ብሪታኒያ የምታቀርባቸውን ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ነው እየሰለጡ ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪም የዩኬ ወታደሮች በፖላንድ በመገኘት አየር መቃወሚያ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ለዩክሬን ወታደሮች ስልጠና እየሰጡ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በሕንድ ጉብኘት እያደረጉ ይገኛሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ የዩክሬን ወታደሮች በዩናይትድ ኪንግደም ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ የጀመሩት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ብሪታኒያ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ለገጠመው የዩክሬን ጦር 120 ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችንም ለግሳለች።

ቃል አቀባዩ ጨምረው እንደተናገሩት ብሪታኒያ እና አጋሮቿ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ለዩክሬን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የዓለም ባንክ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያደረሰችው ውድመት 60 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል አለ።

ባንኩ 60 ቢሊዮን ዶላሩ በመሰረት ልማት እና ሕንጻዎች ላይ የደረሰውን ውድመት እንጂ ጦርነቱ ወደፊት በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ አይመለከትም ብሏል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ደቪድ ማለፓስ ትናንት ሐሙስ ሚያዚያ 13/2014 በሰጡት መግለጫ ጦርነቱ በቀጠለ መጠን የሚደርሰው ኪሳራ ይጨምራል ሲሉ ተናግረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቭሎድሚየር ዜሌንሲኪ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እና የምጣሄ ሃብት ድቀቱ እንዲያንሰራራ አገሪቱ በየወሩ 7 ቢሊዮን ዶላር ትፈልጋለች ብለዋል።

ዜሌንስኪ በእግድ የተያዙ የሩሲያ ንብረት ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲያውሉ ምዕራባውያንን ጠይቀዋል።