ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢንያም ግርማይ ጂሮ ዲኢታሊያ ውድድርን በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኤርትራዊው የብስክሌት ተወዳዳሪ ቢንያም ግርማይ ጂሮ ዲኢታሊያ የተሰኘውን ትልቅ ስም ያለው ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ዙር በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሆን ችሏል።
ቢንያም ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ በሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ሆስፒታል መግባቱም ተሰምቷል።
የ22 ዓመቱ ኤርትራዊ ብስክሌተኛ፤ ማቲው ቫን ደር ፖል የተሰኘውን ተወዳዳሪ የመጨረሻው መስመር አካባቢ በመንደርደር ቀድሞ ነው የ10ኛውን ዙር ውድድር አሸናፊ መሆን የቻለው።
ነገር ግን ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ ደስታውን ሲገልጽ በሻምፓኝ መክደኛ ግራ አይኑን መመታቱን ተከትሎ መጨረሻ ላይ የተካሄደውን ጋዜጣዊ መግለጫ መታደም አልቻለም።
የቡድን አጋሮቹ ግን ከሆስፒታል መልስ ደስታቸውን አብረው እንደገለጹ ተናግረዋል። ኢንተርማርቼ- ዋንቲ- ጎበርት ለተሰኘው ቡድን የሚወዳደረው ቢንያም በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲሳተፍ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
ውድድሩን ለማሸነፍ እስከ የመጨረሻዋ መስመር ድረስ ቢንያምን ሲፎካከረው የነበረው ሆላንዳዊው ቫን ደር ፖል መሸነፉን በማመን በእጁ የእንኳን ደስ አለህ መልዕክቱን ገልጾለታል።
''ለማመን የሚከብድ ነው። እያንዳንዱ ቀን አስገራሚ ታሪኮችን ይዞ ይመጣል። ስለዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ'' ብሏል ቢኒያም ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ።
''ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ምድቡን በደንብ ተቆጣጥረነው ነበር። የቡድን አጋሮቼ ያደረጉትን ነገር ሁሉ እንዴት አድርጌ እንደምገልጸው አላውቅም''
ቢንያም ባሳለፍነው ወር በቤልጂየም የተካሄደውን የጌንት-ዌል የብስክሌት የዕለት ውድድር በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ከሆነ በኋላ በጂሮ ዲኢታሊያም ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር።
ቢንያም የጌንት-ዌል የብስክሌት ውድድር የዕለት አሸናፊ በመሆን ታሪክ ከሰራ በኋላ በሰጠው ቃለ ምልልስ "የማይታመንና የሚገርም ነው። ይህን አልጠበቅኩም ነበር" ብሎ ነበር። አክሎም ''የመጣነው ለጥሩ ውጤት ነው። ውድድሩ አስደናቂና የማይታመን ነው" ብሏል ቢንያም።
በትናንቱ የጂሮ ዲኢታሊ ውድድር ቢንያም ለማሸነፍ ስድስት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት በተሳሳተ መንገድ ለመሄድ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ወዲያው በመመለስ ግን ሆላንዳዊው ተወዳዳሪ ላይ መድረስ ችሏል።
''ውድድሩን ስንጀምረው የማሸነፍ ዕድል እንዳለን እናውቅ ነበር። ስለዚህ የስኬታችን ሚስጥሩ የሁሉም የቡድን አባል ጥረት፣ የቤተሰቦቼ እንዲሁም የሁሉም ነው'' ሲል ተደምጧል።
ውድድሩን 2019 ላይ ያሸነፈው ሪቻርድ ካራፔዝ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ወደኋላ ቀርቶ የነበረ ቢሆንም እስከመጨረሻው ድረስ በመታገል የመጀመሪያ አምስት ተወዳዳሪዎች ውስጥ መሆን ችሏል።
''መጨረሻ ላይ የነበረው ትንቅንቅ በጣም አስገራሚ ነበር። ይህ ድል ለቢንያም በጣም ትልቅ ነው። ምክንያቱም ያሸነፈው በዓለማችን አሉ ከሚባሉት ትልልቅ የብስክሌት ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛውን ነው'' ብለዋል የኢንተርማርቼ- ዋንቲ- ጎበርት ስፖርት ዳይሬክተሩ ቫሌሮ ፒቫ።
''ከጥቂት ቀናት በፊት የማሸነፍ ዕድሉ እንዳለን ተገንዝበን ነበር። ስለዚህ በዛሬው ውድድር ብስክሌተኞቹን ለማነቃቃትና ለማደፋፈር ሞክረን ነበር። በቢንያም ዙሪያ የነበረው ቡድን በታጣ አስገራሚ ነው''
አክለውም ''ይህ ትልቅ ትርጉም አለው። በብስክሌት ውድድር አሸናፊዎች ዝርዝር ውስጥ ሌላ አህጉር መጨመሩ በጣም ጠቃሚ ነው'' ብለዋል።
203 ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍነው የውድድሩ 11ኛ ዙር ዛሬ ረቡዕ ቀጥሎ የሚካሄድ ይሆናል።












