በአሜሪካ ቴክሳስ 19 የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሕጻናት ተገደሉ

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት አንድ የ18 ዓመት ወጣት በከፈተው የተኩስ እሩምታ 2 አዋቂዎችን ጨምሮ 19 ሕጻናት ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት አንድ የ18 ዓመት ወጣት በከፈተው የተኩስ እሩምታ 2 አዋቂዎችን ጨምሮ 19 ሕጻናት ተገድለዋል።

በደቡብ ቴክሳስ ግዛት፣ ዩቫልዲ ከተማ ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው ይህ ወጣት ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ ሕጻናቱን የገደለው።

ፖሊስ እንደሚለው ይህ ወጣት የታጠቀው ኤአር-15 ከፊል አውቶማቲክ ጠመንጃ ነበር።

ይህ ወጣት መጀመርያ ሴት አያቱን ከገደለ በኋላ ነው ሕጻናቱን በግፍ የገደላቸው።

አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ወጣቱ በዚያው አካባቢ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እንደሆነ እየዘገቡ ነው።

የቴክሳስ ግዛት ገዥ ግሬግ አቦት ይህ ወጣት ሳልቫዶር ራሞስ እንደሚባልና መኪናውን ደጅ አቁሞ ወደ ትምህርት ቅጥር ግቢው ከገባ በኋላ ይህን አሰቃቂ ድርጊት እንደፈጸመ ተናግረዋል።

ከተገደሉት ሁለት አዋቂዎች አንዷ በዚያው ትምህርት ቤት የምታስተምር መምህርት ነበረች።

በስፋት የስፓኒሽ አሜሪካዊያን በሚበዙበት በዚህ ትምህርት ቤት 500 ሕጻናት ተማሪዎች ይገኙበታል።

ሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ2ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ፤ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 10 ዓመት ያሉ ልጆች የሚማሩበት ነው።

አሶሲየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ከትምህርት ቤቱ በቅርብ የነበረ አንድ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ የተኩስ ድምጽ ሰምቶ ወደ ትምህርት ቤቱ በመግባት ይህን ወጣት ታጣቂ ተኩሶ ባይገድለው ኖሮ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን ይችል ነበር።

ዩቫልዲ ከተማ ከሜክሲኮ ድንበር በ80 ማይል የምትርቅ በቴክሳስ ግዛት የምትገኝ ከተማ ናት።

ይህ ጥቃት ፈጻሚ ደረቱ ላይ የጥይት መከላከያ ያጠለቀ ሲሆን በተመሳሳይ ከሳምንት በፊት በኒው ዮርክ ቡፋሎ አንድ ሱፐርማርኬት ውስጥ ጥቁር ጠል አክራሪ ወጣት በተመሳሳይ ተኩስ ሲከፍት የተጠቀመበትን መሣሪያና አለባበስ ይህም ወጣት አድርጎታል።

በአሁኑ ሰዓት አንዲት የ66 ዓመት ሴት እና የ10 ዓመት አዳጊ በሳን አንቶኒዮ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

የሮብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጥቃት አሜሪካ በጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዙርያ ልትከተል በሚገባው ደንብ ላይ ትኩስ ክርክር እንዲከፈት ምክንያት እንሚሆን ይጠበቃል።

ጆ ባይደን በዚህ ጥቃት ልጆቻቸውን፣ ቤተሰባቸውን ላጡ ሐዘናቸውን ገልጠዋል።