"አንቱ በእናቱ"፡ የኢትዮጵያዊው ምርኮኛ እና የኤርትራዊቷ ታጋይ የፍቅር ታሪክ

አቶ ማሞ አፈታ,, ባለቤቱ ሕይወት ተስፋይ እና ልጆቻቸው

የፎቶው ባለመብት, Mamo

ይህ በሁለት ተቃራኒ ወገን ቆመው የታገሉ ጥንዶች የፍቅር ታሪክ ነው።

አቶ ማሞ አፈታ ለኢትዮጵያ፣ ባለቤቱ ሕይወት ተስፋይ ደግሞ ለኤርትራ ወግነው ጦር ሜዳ ውለዋል።

በዚህ መካከል ደግሞ ፍቅር የልባቸውን በር አንኳኩቷል።

አቶ ማሞ በመጀመሪያ በሻዕቢያ ወታደሮች በኋላም በሕይወት ፍቅር ተማረኩ።

አቶ ማሞ ይህንን የፍቅራቸውን ድርሳን በቅርቡ "አንቱ በእናቱ" በሚል ርዕስ በመጽሐፍ አሳትመውታል።

መጽሐፉ ውስጥ ራሳቸውን ጆቴ በሚል የገጸባህሪ ስም ወክለው አቅርበዋል።

የ'አንቱ በእናቱ' ጆቴ የእውኑ ዓለም አቶ ማሞ አፈታ እና ባለቤታቸው ሕይወት ተስፋይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ልጅነት

አቶ ማሞ በአሁኑ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ጊዳ አያና ወረዳ፣ ሲርባ ቡልቶም ተብላ በምትጠራ የገጠር ቀበሌ ነው የተወለደው።

ለእናቱ አንድ የሆነው ማሞ፣ ወላጆቹ በልጅነቱ በመለያየታቸው እናቱ ላይ ወድቆ የነበረው የኑሮ ጫና የልጅነት ጊዜው ሰቀቀንን ያዘለ እንዲሆን እንዳደረገው ያስታውሳል።

ዘጠነኛ ክፍል እንደደረሰ ግን ከዚህ ሰቀቀን ለመገላገል እና እናቱን ለማገዝ የሚወደውን ትምህርት አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ኮበለለ።

አዲስ አበባ ገብቶ እናቱን የሚያግዝበት ሥራ ሲያፈላልግ ደግሞ፣ የጠበቀው የሥራ አማራጭ ውትድርና ብቻ ነበር። አማራጩን ተጠቀመበት፤ ወደ ወታደር ቤት ገባ።

ከዚያም በደብረ ብርሃን መሠረታዊ ውትድርናን ለስድስት ወራት ሰልጥኖ ኤርትራ ተመደበ። አሥመራ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላም ማረፍያው ከረን ሆነ።

በአቶ ማሞ አፈታ የተጻፈው "አንቱ በእናቱ" መጽሐፍ ሽፋን

የፎቶው ባለመብት, Mamo

የአፍአበት ውጊያ እና ምርኮ

በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የሕዝባዊ ግንባር ተዋጊዎች ለሁለተኛ ጊዜ በከባድ መሳርያ የበታገዘ ጥቃት በአፍአበት ላይ በፈጸሙበት ጊዜ ማሞ እንደተማረከ ያስታውሳል።

"እኔ እግሬን ተመታሁ፤ ወታደራዊ ካምፑም ተያዘ. . . ያኔ የሚሞት ሞቶ የቀረው ተማረከ" በማለት ያስታውሳል።

በጦርነቱ ከተማረኩት 165 የኢትዮጵያ ወታደሮች ማሞ አንዱ ነበር።

ወታደራዊ ካምፑ በሻዕቢያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር በወደቀበት ቅጽበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ድብደባ አካሄደ።

ማሞ የሻዕቢያ ወታደሮች የምርኮኞቹን ሕይወት ለማትረፍ እንደተረባረቡ አልዘነጋም።

የአየር ድብደባው ካበቃ በኋላም በትግርኛ፣ 'እንኳን በሕይወት አተረፋችሁ' የሚል መልካም ምኞት ከታጣቂዎቹ መስማቱን ይገልጻል።

የምርኮ ሕይወት

ምርኮኞቹ ስለ ፖለቲካና እና የኤርትራ ሕዝብ ትግል ትምህርት ይሰጣቸው ጀመር።

በወቅቱም "ደርግ ተራማጅ ነው። አይደለም ፋሺስት ነው የሚል ክርክር ሳይቀር ከታጋዮች ጋር ነጻ ክርክር ይካሄድ ነበር" ይላል።

ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር የነበረው ማሞ የመማር ማስተማሩን ሂደት አጥብቆ ያዘው።

አንድ ችግር ግን ነበር። በአማርኛ የተዘጋጀ መማርያ አልነበረም። ማሞ ይህንን ለመቅረፍ ለመጀመር የሚሆን "አጭር መግለጫ" የሚል 20 ገጽ ያለው ጽሑፍ በማዘጋጀት ታትሞ እንዲሰራጭ ተደረገ።

ምርኮኞቹ በመጀመሪያ ይገድሉናል የሚል ስጋት ስለነበራቸው ለትምህርቱ ግድ አልነበራቸውም።

ማሞ ግን የሻዕቢያ ታጋዮች የሚሰጡትን ትምህርት በአግባቡ በመከታተል በጠቅላላ 15 መጻሕፍት ጽፏል፤ በሂደትም የትግርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ቻለ።

አቶ ማሞ አፈታ እና ባለቤቱ ሕይወት ተስፋይ

የፎቶው ባለመብት, Mamo

የታጋይዋ ትጥቅ የማረከው ልብ

መጽሐፉ ውስጥ በጆቴ እና ገላዬ የተወከሉት ማሞ እና ታጋይ ሕይወት ተስፋይ ትውውቃቸው ከ1982 እስከ 1983 ባሉ ጊዜያት ነበር የጀመረው።

በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ምርኮኞች ምርጫቸውን እንዲወስኑ ሲጠየቁ ማሞ ከሕዝባዊ ግንባር ጎን ተሰልፎ ለመታገል ወሰነ።

ለዚህ ደግሞ ወታደራዊ ሥልጠና መውሰድ ነበረበት።

ሕይወት፣ ማሞ ለስልጠና በተመደበበት 'ሂምቦል' ተብሎ በሚጠራ ማሠልጠኛ አካባቢ በነበረው የ 'ቁጠባ' (ምጣኔ ሃብት) ክፍል ተመድባ ነበር።

ሕይወት በ1978 አካባቢ በብዛት ከገቡትና 'ካምቦድያ' ተብለው ከሚጠሩት ሴት ታጋዮች መካከል አንዷ ነበረች።

ቀዲ አምሓረ አካባቢ ከሚገኝ ጋዴን ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ወደ ትግል እንደተቀላቀለች ትገልጻለች።

ሕይወት ጨዋታና ጭፈራ የምትወድ ነበረች። ሙዚቃ ካለ እሷ አትጠፋም። ይህ ባህሪዋ ደግሞ ከማሞ ጋር እንድትተዋወቅ እና ሕይወትዋን የቀየረው የፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንድትገባ አደረጋት።

"አጠገባችን የነበሩት ምርኮኞች የተለያየ የእርሻ ሥራ ይሰሩ ነበር፤ በተጨማሪም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ ነበር" በማለት የነበረው ሁኔታ ታስታውሳለች።

አንድ ጊዜ በምርኮኞች የተቋቋመችና ጆቴ የሚመራት የባህል ቡድን ትርዒት አዘጋጀች።

ማሞ የመድረክ መሪ ነበረ።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ታዳሚዎች ሆነው መጡ።

ያኔ ማሞ መድረኩን እየመራ በመካከል ግጥሞችና ተጨማሪ አጫጭር መልዕክቶች ሲያቀርብ አንድ ከፊት ለፊቱ ተቀምጣ በተመስጦ የምትከታተው ታጋይ መኖሯን አስተዋለ።

ቆይቶም አንድ የአማርኛ ዘፈን መዝፈን ሲጀመር ገላዬ መጥታ "ዓሽ" አለችው [አድናቆቷን ገለፀችለት]።

ዓይን ለዓይንም ተገጣጠሙ። ፍቅር በዓይናቸው ገብቶ መላ አካላቸው ውስጥ ነፍስ ዘራ።

ሕይወት ያቺን ቅፅበት ስታስታውሳት "ሁለንተናው ማለትም ቁመናው፣ አነጋገሩና አዘፋፈኑ ማረከኝ። ገና እንዳየሁት ወደድኩት። በቃ የዓይን ፍቅር ነው የተሰማኝ" በማለት ትገልፃለች።

ማሞ በበኩሉ "ያኔ በጣም የማረከኝና የወደድኩላት ትጥቋና የታጠቀችበት መንገድ ነበር። የተለየ ነበር. . . በእርሷ ላይ ደሞ እጅግ ያምርባት ነበረ" በማለት ያቺ ቅፅበት ዛሬም ድረስ በውስጡ እንዳለች ይናገራል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ማሞ እየሰረቀ እሷን ማየት ጀመረ። እርሷም የዓይን ፍቅር ይዟት ስለነበር አንድ ቀን ፋስ ለመለመን እሱ ወደነበረባት አሃድ ሄደች። ያኔ ማሞ ተረኛ መጋቢ ነበረ።

"ያኔ ተረኛ መጋቢ ስለነበርኩ ምንም ሳልናገር በመነሳት የጠየቀችውን አቀበልኳት" ይላል በማስታወስ።

ፍቅራቸው እየጠና መጣ። የተለያዩ ምክንያቶችና ሰበቦችን በመፍጠር መተያየት መፈላለግ ሥራቸው ሆነ።

"ስለእርሱ ሳስብ 'የት ላገኘው እችላለሁ? እርሱ ኢትዮጵያዊ ነው። ግንኙነታችን እንዴት ሊሳካ ይችላል?' በማለት እጨነቅና ተስፋ እቆርጥ ነበረ" በማለት ያኔ ስለነበራት የፍቅር ስሜት ታስታውሳለች።

ከዚያም ከሕዝባዊ ሠራዊት ጋር ለመሰለፍ የወሰኑ ምርከኞች 'ሂምቦል' በተባለ ቦታ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ተለያዩ አሃዶች ተመደቡ።

ታድያ ማሞም 'ሕሽክብ' በተባለ የማዕከላዊ ሰውራ (አብዮት) ጥበቃ በመሆን የሥራ ድርሻ ተሰጠው።

ከተወሰነ ቆይታ በኋላም ሕይወት ወደ ተመሳሳይ ክፍል ተመድባ ማሞ ወደነበረበት መጣች። ዳግም ለመገናኘትም በቁ።

ይኹን እንጂ ያ ቀስበቀስ ለሁሉም ግልፅ እየሆነ የመጣው ፍቅራቸው በፈተናዎች የታጀበ ነበር።

"ብዙዎች 'ይህን ኢትዮጵያዊ ለምን ቀረብሽው?' በማለት ያስቸግሩኝ ጀመር። በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ብዙ ሰው አይቀበልም" በማለት ያሳለፈችውን ፈተናዎች ታስታውሳለች።

እርሷ ግን "የፈለኩትን ባደርግ ምን አገባችሁ? ፓርቲዬ ከፈደችልኝ እናንተን ምን አስጨነቃችሁ። ከምንም በላይ ደሞ እንደኔ ሰው የሆነውን ነው ያፈቀርኩት። ማንም ይሁን ከየትም ይምጣ አሁን የትግል ጓዴ እንደሆነ ነው የማውቀው። አፈቅረዋለሁ" በማለት ትገልፅላቸው እንደነበረችና ፍቅር የማያሸንፈው ነገር እንደሌለ ትናገራለች።

ማሞ "አንድ ቀን እኔና እሷ ምሽግ ውስጥ ተቀምጠን ስናወጋ፣ አለቃዋ ፈልጎ ስላጣት ወደነበርንበት ቦታ መጣ። በዚያች ቀን ፍቅራችንን ብንገላለፅም ከዚያ በዘለለ ግን ያደረግነው ነገር አልነበረም" በማለት አንድ ልዩ አጋጣሚ ያስታውሳል።

አቶ ማሞ አፈታ እና ባለቤቱ ሕይወት ተስፋይ

የፎቶው ባለመብት, Mamo

በክትትል ስር ስለነበረ፤ ይህንን አጋጣሚ እንደ ሥነ ሥርዓት ጉድለት አስበው በቅጣት ወደ ሌላ ራቅ ወዳለ ቦታ ቀይረው ላኩት።

በ1984 [እ.ኤ.አ] 'ውቃው' የተባለው እዝ በውጊያ በመሸነፉ ማሞ አዲስ ምርኮኞችን ለማስተማር እሷም የጥበቃ አባል ሆና በአንድ አሃድ ውስጥ እንደተገናኙ ሁለቱም ይናገራሉ።

"ሁሉም ሰው አንድ አይደለም፤ የሚደግፍም ይኖራል" የምትውለው ሕይወት፣ ሳባ ዮሃንስ [በቅጽል ስሟ 'ቡፍ'] የተባለች ጓድ 'አይዞሽ ወደ ኋላ መመልከት የለብሽም' እያለች ከጎኗ እንደቆመችና ፍቅራቸውን እንደደገፈች ታስታውሳለች።

በመጨረሻም ውሳኔ ላይ ደረሰች። "የት እንገናኛለን?" የሚል ስጋቷ እየጠፋ አብረው መኖር እንደሚችሉ እየተቀበለችና ውስጧን እያረጋጋች መጣች።

ግንኙነታቸው በ1986 [እ.ኤ.አ] ይፋ ሆነ። የፍቅር ግንኙነት በይፋ ማሳወቅ በትግሉ ባህል መሰረት እንደ መተጫጨት ስለሚታሰብ፣ በግለሰቦች ደረጃ የሚሰሙ ሐሜቶች ባይጠፉም ይፋ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ግን እንደ እጮኛ በነፃነት መጠያየቅና አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ቻሉ።

ማሞ ሳህል በነበሩበት ጊዜ "ገላዬ ገላዬዋ" እያለ ሲዘፍን የሚሰሙ ታጋዮች ለሕይወት 'ገላዬ' ብለው ቅጽል የትግል ስም እንዳወጡላት ያስታውሳል።

ከዚህ በመነሳትም በመጽሐፉ ውስጥ ባለቤቱን ሕይወትን 'ገላዬ' የሚል ስም ሰጣት።

ትዳርና ልጆች

ማሞ ከአምስት ዓመታት የምርኮኝነት ቆይታ በኋላ በ1982 [እ.ኤ.አ] ነፃ ተባለ። ወደ ትግሉ መቀላቀል በመፈለጉም ሙሉ መብት ተሰጠው።

በ1988 [እ.ኤ.አ] በሕዝባዊ ግንባር የትግል ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ 32 ጥንድ ታጋዮች በአንድ ቀን ናቅፋ ላይ ቃልኪዳን በማሰር ለመጋባት በቁ።

"አንድ ማሞ አፈታ የተባለ ኢትዮጵያዊ ምርኮኛ ከአንዲት ሕይወት ተስፋይ - 'ጓል ማኦ' - የምትባል ኤርትራዊ ታጋይ ጋር በመጣመር ቃልኪዳን አሰረ" የሚል ዜና በኤርትራው አብዮት ዘንድ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆነ።

ማሞ ናደው ጦር ከመደምሰሱና የናቅፋ ግንባር ከፈረሰ በኋላ [1988 እ.ኤ.አ] ናቅፋ ውስጥ ቃልኪዳን ያሰሩበት አጋጣሚ ደማቅ የነበረ ሲሆን ለእርሱ ክብር ለመስጠት ሲባል የአማርኛ ዘፈን ቀርቧል።

"አስታውሳለሁ ያኔ አልአሚን መሐመድ ሰዒድ [በቅርቡ በሞት የተለየ የህዝባዊ ግንባር ጽህፈት ቤት ኃላፊ] ነበረ ንግግር ያሰማው" የምትለው ሕይወት በመካከላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ ቃልኪዳን ለማሰር እንደበቃ መናገሩን ትገልፃለች።

የማሞ እና የሕይወት ሠርግን የበለጠ ጣፋጭ ያደረገው፣ የጫጉላ ጊዜያቸውን ማሞ ከ12 ዓመታት በፊት በተማረከባት እና ከናቅፋ 65 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ 'አፍዓበት' በምትባል ከተማ በመዘዋወር እንዲያሳልፉ መፈቀዱ ነበር።

አቶ ማሞ እና ሕይወት አራት ልጆችን ወልደው ለመሳም በቅተዋል።

ሕይወት "ከነፃነት በኋላ እናቴ ወደምትኖርበት ጋዴን ስንሄድ ከልጆቼና ባለቤቴ ጋር ነበርን። አግብቼ ሁለት ልጆች ይዤ ነው የተመለስኩት። ቤት ስደርስ እናቴንና የእህቴ ልጆች አገኘናቸው። ልጆቼን ታቅፌ ስለሄድኩ የነበረውን ስሜት ትንሽ ቀይሮታል። ያኔ አባቴ ደቂ አምሓረ የሚባል ቦታ ነው የነበረው። 'ኢትዮጵያዊ ይዘሽብን መጣሽ!' ብሎ ትንሽ ተቆጥቶ ነበር" ስትል የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች።

"ከነፃነት በኋላ አሥመራ ውስጥ ቤት ተሰጠን። እዚያው በትዳር ፀንተን መኖር ጀመርን" የሚለው ማሞ በልጅነቱ ያቋረጠው ትምህርቱን እንዲቀጥል ዕድል እንዳገኘም ያስታውሳል።

በታዋቂው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ነጥብ አመጣ።

ትዳራቸው እየሞቀና ፍቅራቸው እየፀና በመሄዱ ፊልሞን የሚል ስም ያወጡለት ሦስተኛ ልጃቸውን እዚያው አሥመራ ውስጥ ወለዱ። ከዚያ ግን ኤርትራ ውስጥ አልቀጠሉም። እናቱን እንዲረዳ ተፈቅዶለት በ1995 [እ.ኤ.አ] ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄድ ተፈቀደለት።

በአሁኑ ወቅት የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) ሆና እየሰራች የምትገኘው ሄናን የተባለቸው አራተኛ ልጃቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ተወለደች።

በአሁኑ ጊዜ አዲስ አበባ የሚኖሩት ማሞ እና ሕይወት፤ ያኔ በአፍላ ፍቅር ላይ ሳሉ በሳህል የተወለደው በኩር ልጃቸው አግብቶ የልጅ ልጅ ለመሳም ስላበቃቸው እጅግ ደስተኞች መሆናቸውን ይናገራሉ።

ደራሲ ማሞ አፈታ ስለመጽሐፉም ሲናገር "ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን ልብ ውስጥ የሚኖር ሰነድ ነው" ይላል።