ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በድጋሚ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኑ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለማችንን ትልቁን የጤና ተቋም የዓለም የጤና ድርጅትን ለሁለተኛ ዙር እንዲመሩ ዳግም ተመረጡ።

የዶ/ር ቴድሮስ ብቸኛ ዕጩ ሆነው ዳግም መመረጣቸው የተረጋገጠው በጄኔቫ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው 75ኛው የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉብዔ ላይ ነው።

ዶክተር ቴድሮስ ያለተፎካካሪ በብቸኛ ዕጩነት በቀረቡበት መድረክ ላይ ከተለያዩ የድርጅቱ አባል አገራት ለዕጪነት ለተሰጣቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የዋና ዳይሬክተሩ ምርጫን በመደገፍ በቦትሰዋናው ተወካይ በኩል የአፍሪካ አገራት ቡድንን በመወከል ሊቀርብ የነበረውን መግለጫ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተቃውመውታል።

በዚህም 45 የአፍሪካ አገራት ድጋፍ በሚል ቦትሰዋና ለዶ/ር ቴድሮስ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት እና የመልካም የሥራ ጊዜ ምኞት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ያለፉት አምስት ዓመታት የተባበሩት መንግሥት ጤና ድርጅት ሲመሩ ቆይተዋል። በዚህ ወቅት የኮቪድ-19 ስርጭት እና ተቋማቸው ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የገባው ውዝግብ የሥልጣን ዘመናቸውን ፈታኝ ከዳረጉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የዓለም ጤና ዳይሬክተሩ መመረጣቸውን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "በእኔ ላይ ላላችሁ መተማመን እና ለጣላችሁብኝ እምነት አመሰግናለሁ" ብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ተቋሙን በይፋ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣይ አምስት ዓመታት ለሁለተኛ ዙር መምራት ይጀምራሉ።

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመመረጣቸው በፊት እአአ ከ2012 እስከ 2016 ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ሚንስትር ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት በኢትዮጵያ የጤና መሠረታዊ አገልግሎቶች መስፋፋታቸው እና የሕጻናት እና እናቶች ሞት መጠን መቀነሱ ይገለጻል።

ዋና ዳይሬክተሩ በመጀመሪያው ዙር የዓለም ጤና ድርጅት የመሪነት ዘመናቸው ከገጠሟቸው ፈተናዎች መካከል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ጦርነት በገጠመበት ጊዜ ለቡድኑ ድጋፍ ይሰጣሉ በሚል ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ከሰዋቸዋል።