12ኛ ክፍልን ከልጃቸው ጋር ተፈትነው ዩኒቨርስቲ የገቡት አርሶ አደሯ የአራት ልጆች እናት

የፎቶው ባለመብት, Daniel Regassa
"የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ከምወደው ትምህርት አቋርጠውኝ ለማላውቀው ሰው አስገድደው ዳሩኝ፤ ቢሆንም ትምህርት በጣም ስለምወድ ልጆቼን ካስተማርኩ በኋላ ወደ ትምህርቴ ተመልሼ ዩኒቨርስቲ የመግባት እድል አግኝቻለሁ" ይላሉ የ47 ዓመቷ ወ/ሮ ይመኙሽ ምትኩ።
ወ/ሮ ይመኙሽ ምትኩ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ በዚህ ዓመት የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ወስደው ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ወለጋ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል።
ከሦስተኛ ልጃቸው ጋር ከአስረኛ ክፍል ጀምሮ አንድ ክፍል የተማሩት ወ/ሮ ይመኙሽ፣ ወደ ቤት ሲመለሱም ሌሊት ከልጃቸው ጋር አብረው ቁጭ ብለው ያጠኑ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ይመኙሽ የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን 3.7 ሲያመጡ፣ ልጃቸው ደቻሳ ደግሞ 3.9 በማምጣት ነበር ወደ መሰናዶ ትምህርት አብረው የገቡት።
ይህ የሆነው በ2011 ዓ.ም ሲሆን፣ የመሰናዶ ትምህርታቸውንም እናትና ልጅ በአንድ ክፍል ጎን ለጎን ተቀምጠው ነው የተከታተሉት።
የወ/ሮ ይመኙሽ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሴቶች ልጆች በወቅቱ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አገባደዋል።
"ትምህርት በጣም እወድዳለሁ፤ ለትምህርት ምን ዓይነት ስሜት እንዳለኝ ሁሉ መግለጽ ይከብደኛል። ድሮ በልጅነቴ ከአንድ እስከ ሰባተኛ ክፍል ስማር ከአምስተኛ በታች ወጥቼ አላውቅም" ይላሉ ወ/ሮ እመኙሽ።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ወጣቶች የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ሥራ ማጋኘት አጥተው ባሉበት ጊዜ ወ/ሮ ይመኙሽ ስለምን ወደ ዩኒቨርስቲ እንዳመሩ አንዳንዶች ቢጠይቁም መልሳቸው የትምህርት ፍቅር እንደሆነ ይናገራሉ።
"ወልጄ ከብጄ፣ ክፉ ደጉን አብሬ ያሳለፍኩትን ማኅበረሰብ ተምሬ ከማገልገል በተጨማሪ፣ ትምህርት ስለምወድ ጭምር ነው የምማረው" ይላሉ።
'ከአስረኛ ክፍል ነው በግድ የተዳርኩት'
በምሥራቅ ወለጋ ሌቃ ዱለቻ ወረዳ ተወልደው ያደጉት ወ/ሮ ይመኙሽ ምትኩ፣ በ1976 ዓ.ም. ነበር አንደኛ ክፍል የገቡት።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም ቦሎ ገርጀጃ በሚባል ትምህርት ቤት ነበር ያጠናቀቁት።
በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት ሲወድቅ የስምንተኛ ክፍል አገራዊ ፈተና አለፋቸው።
ከዚያም ወደ ገጠር ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ጀመሩ።
እንደ ዛሬው መረጃ ማግኘት ቀላል ባልነበረበት ወቅት የፈተና መውሰጃው ቀንን ማወቅ አስቸጋሪ ነበር።
"አንድ ቀን ፈተና መቼ እንደሚሰጥ ለመጠየቅ ወደ ትምህርት ቤት ሳመራ፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 28/1983 ዓ.ም. መሰጠቱን ሰማሁ። በጣም አዝኜ እያለቀስኩ ተመለስኩ።"
በድጋሚ ለመፈተን ተመዝግበው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በነበረው ችግር ምክንያት እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ ከትምህርት ገበታ ርቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቆየታቸውን ይናገራሉ።
በ1988 ዓ.ም. የስምንተኛ ክፍል ፈተናቸውን ወስደው ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ነቀምቴ ከተማ አመሩ።
በዚህ ወቅት ነበር ድንገት ያላሰቡት ሕልማቸውን የሚሰናክል ነገር ገጠማቸው።
"ልጃችሁን ለልጃችን ስጡን የሚል ጥያቄ ለቤተሰቦቼ ቀረበ። ቤተሰቦቼም ከምወደው ትምህርቴ አሰናክለው ዳሩኝ። ትምህርቴን በማቋረጤ በጣም አዘንኩ" ይላሉ።
አክለውም "እኔ እና ባለቤቴ አንተዋወቅም። ቤተሰቦቻችን ናቸው የሚተዋወቁት። የደርግ ወታደር ስለነበር እርሱ ከጦር ሜዳ ወደ ቤት ሲመለስ ቤተሰቦቹ ናቸው እንዲያገባ በሚል ቤተሰቦቼን የጠየቁት። ሥራም አልነበረውም" ሲሉ ያስታውሳሉ።
ወ/ሮ ይመኙሽ አግብተው ጅማ አርጆ ውስጥ በእርሻ ሥራ ሲተዳደሩ ኖሩ።
ከትምህርታቸው ከተሰናከሉ በኋላ በወላጆቻቸው ግፊት ያገቧቸው ባለቤታቸውም ቢሆኑ የወ/ሮ ይመኙሻልን መማር ይደግፉት ነበር።
በዚህ መካከል የመጀመሪያ ልጃቸው ተወለደች። ልጅ ወደ ማሳደግ ገቡ።
"ሰው ራሱን እስኪችል ማግባት አያስፈልግም ብዬ አምናለሁ። ትዳር አልወድም ነበር። ካገባሁ በኋላ ሁሉ ወዴት አገር ጠፍቼ መማር እችላለሁ ስል አስብ ነበር" ሲሉ በወቅቱ የነበራቸውን ስሜት ያጋራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Dr Aliimaa Jibriil
ወደ ትምህርት ቤት መመለስ
በ1994 ዓ.ም. ባለቤታቸው የጥበቃ ሥራ አገኙ እና ኑኑ ቁምባ ወደሚባል ቦታ አመሩ።
ብዙም ሳይቆዩ ወ/ሮ ይመኙሽም ወደ ስፍራው አምርተው ልጆቻቸውን ማስተማር ቀጠሉ።
በዚህ መካከል የኮሌጅ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ውትድርና የሄዱት የወ/ሮ ይመኙሽ ባለቤት፣ የሕግ ትምህርት ተምረው ዲፕሎማቸውን ያዙ።
ከዚያም ዲግሪያቸውን ቀጥለው፣ አሁን በኑኑ ቁምባ በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ ተቀጥረው ያገለግላሉ።
ይህ ለወ/ሮ ይመኙሽ የትምህርት ፍላጎት መቀጣጠል ተጨማሪ ማገዶ በመሆን አገለገለ።
'መስከረም ተማሪዎች ሲመዘገቡ እኔ መች እመዘገባለሁ ብዬ እመኝ ነበር'
ወ/ሮ ይመኙሽ አራት ልጆች ወልደው፣ እድሜያቸውም ከገፋ በኋላ ለትምህርት የነበራቸው ፍቅር አልጠፋም።
"የመጀመሪያ ሁለቱ ልጆቼ ዩኒቨርስቲ ከገቡ በኋላ፣ ልጆቼ ከአሁን በኋላ አይቸገሩም ብዬ በ2011 ዓ.ም. ወደ ትምህርት ተመለስኩ። ባለቤቴም እንድማር ያበረታታኝ ነበር፤ ያስመዘገቡኝ ባለቤቴ እና ልጄ ናቸው። ሦስተኛው ልጄ ደቻሳ በትምህርቱ ጠንካራ ነው። ከእርሱ ጋር አስረኛ ክፍል አንድ ክፍል ውስጥ ሆነን መማር ጀመርን።"
ወ/ሮ ይመኙሽ ከልጃቸው ጋር የተማሪ የደንብ ልብስ ለብሰው፣ ቦርሳ አንግተው ቀለም ይቆጥሩ ጀመር። የከበዳቸውን ከመምህራኖቻቸው በተጨማሪ ልጃቸው እያስረዳቸው ቀን ትምህርት ቤት፣ ከዚያ መልስ ማጀት፣ ሌሊት ደግሞ ደብተሮቻቸው መካከል የእውቀት ዘር ፍለጋ ባተሉ።
የመሰናዶ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከልጃቸው ጋር አንድ ክፍል እንደደረሳቸው ጨምረው ገልፀዋል።
ወ/ሮ ይመኙሻልን ከረዥም ዓመት በኋላ ወደ ትምህርት ሲመለሱ አልጠፋብዎትም በማለት ጠየቅናቸው።
"የድሮው ከውስጤ አልወጣም። በልጅነቴ ሒሳብ እወድ ነበር። መጀመሪያ ላይ ትንሽ ከብዶኝ ነበር። አሁን ሁሉንም እወዳለሁ። አላበላልጥም። ልጄ ያስጠናኝ ነበር። ሌሊትም አብረን ቁጭ ብለን እናነባለን። ከትምህርት መቅረትም አልወድም" ይላሉ።
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን እናትና ልጅ የተሻለ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ልጃቸው ደቻሳ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ እናት ወ/ሮ ይመኙሽ ደግሞ ወለጋ ዩኒቨርስቲ ተመደቡ።
"ባለቤቴ ካለፍሽ እዚያው ገብተሽ መማር አለብሽ ስላለኝ፣ አሁን ዶርም ገብቼ ልማር ነው የመጣሁት" በማለት በሙሉ ልባቸው የከፍተኛ ከፍተኛ ትምርታቸውን ለመከታተል መቁረጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የገጠሩ ኅብረተሰብ ውስጥ ኖሬ የእናቶችና ሕጻናት ኑሮ ስላየሁት የጤና ትምህርት ተምሬ ሕዝብ ማገልገል እፈልጋለሁ። እኔ የምማረው ሥራ ላገኝበት ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ዕድል በማግኘቴ እጅግ ደስ ስላለኝም ነው።"
'ከእናታችን ጋር የምንማር ቢሆን. . .'
ወ/ሮ ይመኙሽ ከልጃቸው ጋር የደንብ ልብስ ለብሰው ትምህርት ቤት ሄደው ሲመለሱ በብዙ ሰዎች ዕይታ ውስጥ ይገባሉ።
"በርካታ ተማሪዎች ስለ እኛ ይደሰታሉ። ምናለ እንዳንተ ከእናታችን ጋር የምንማር ቢሆን ሲሉ ይመኛሉ" ይላሉ ደቻሳ።
ወ/ሮ ይመኙሽ እና ልጃቸው ደቻሳ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ተወዳጅ ተማሪዎች ነበሩ።
"መምህራኖቻችን ለእኔ ልጅ የሚሆኑ ስለነበሩ ያበረታቱኝ ነበር" የሚሉት ወ/ሮ ይመኙሽ፣ ልጆች እያሳደጉ፣ የቤት ሥራ እየሰሩ፣ ትምህርትን ማስኬድ እንዳልከበዳቸው ይገልጻሉ።
ከትምህርት ቤት መልስ የቤት ውስጥ ሥራ ከልጆቻቸው ጋር ተረዳድተው ይሰሩ እንደነበርም ይናገራሉ።
ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው በማግባታቸው ይበሳጩ የነበሩት ወ/ሮ ይመኙሽ፣ አሁን ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ በመቃረባቸው ትልቅ ደስታ እንደሚሰማቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ድሮ አግብቶ ተመልሶ መማር አልነበረም፤ አሁን ግን ካገቡ በኋላም መማር ይቻላል" የሚሉት ወ/ሮ ይመኙሽ፣ ሴቶች ለቤት ሥራ ወይንም ለልጆች ብለው ትምህርታቸውን እንዳይተዉ ይመክራሉ።
ትምህርታቸውን ላቋረጡ እናቶችም ቢሆን "ከመጨረሻ ልጃችሁም ጋር ቢሆን አንድ ክፍል ተምራችሁ ካሰባችሁበት መድረስ ትችላላችሁ" ይላሉ ወ/ሮ ይመኙሽ።
በተጨማሪም፣ ለሥራ ወይንም ለደመወዝ ብቻም አንማርም ትምህርትም በእድሜ አይገደብም ሲሉ ትምህርት ያቋረጡ እናቶችን መክረዋል።














