የጋዜጠኞቹ እስርና በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ዘመቻ

የፎቶው ባለመብት, Social Media
በማህበራዊና በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመተቸት የምትታወቀው መስከረም አበራ ቅዳሜ እለት፣ ግንቦት 13 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር መዋሏን ባለቤቷ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በአዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበረችው መስከረም በቁጥጥር ስር የዋለችው በአዲስ አበባ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲሆን ያለችበትንም ስፍራ እንደማያውቁ ባለቤቷ ተናግረዋል።
ይህም በሳምንቱ የታሰሩትን የጋዜጠኞች እና የሚዲያ አካላት ቁጥር ሰባት ያደረሰው ሲሆን ሁኔታውም የተችዎን ድምጽ በማፈኑ ረገድ አዲስ እርምጃ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 11፣ 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ተቀማጭነቱን ያደረገውና የቅርብ ዘገባቸው በፋኖ ላይ ያተኮረው አሻራ ሚዲያ አምስት ጋዜጠኞቹ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
ጋዜጠኞቹ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ፖሊስና የአድማ በታኝ የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት እንደተወሰዱ "ሽንት ቤት ውስጥ ተደብቄ ነበር" ያለ የስራ ባልደረባቸው ለሮይተርስ ተናግሯል።
ግለሰቡ በባህርዳር ከተማ የሚገኘው የአሻራ ጽህፈት ቤት መዘጋቱንም ተናግሯል።
በተጨማሪም በሃገሪቱ የተካሄደውን ጦርነት በመቃወምና የሰላምና ድርድር መንገዶች የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬም መታሰሩ ተዘግቧል።
ቢቢሲ የአዲስ አበባን ሆነ የፌደራል ፖሊስን ለማግኘት ቢሞክርም ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ለማካተት አልተቻለም።
ጋዜጠኞቹ በቁጥር ስር የዋሉት መንግሥት በተለያዩ ክልሎች ህግን የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ባስታወቀ ማግስት ነው።
የፌደራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አርብ ምሽት በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የአገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሔ ነው ብሏል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገ ወጥነትና የሰላም መደፍረስን መንግሥት እንዲቆጣጠር ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር ያለው መግለጫው፣ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን አስታውሷል።
የተቃዋሚው አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዘጠኝ አባላትም እንዲሁ በያዝነው ሳምንት ግንቦት 10፣ 2014 ዓ.ም በሁለት ከተሞች መታሰራቸውን ሮይተርስ በአሜሪካ የሚገኘውን የአማራ ማህበር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በተጨማሪም የአብን ፓርቲ አባላትና አመራሮች እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አምስት የአብን አባላት አርብ ዕለት፣ ግንቦት 12፣ 2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ "መንግሥት እገታና ስወራ" እየፈጸመ ነው ሲሉ ከሰዋል።
"በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አባላትና አመራሮች፣ በፋኖ አባላት፣ በሕጋዊ ታጣቂዎችና ወጣቶች እንዲሁም አገራቸውንና ሕዝባቸውን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ የጦር መኮንኖችንና የጸጥታ አመራሮች ላይ የሚፈጸመው መንግስታዊ እገታና ስወራ በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ሰበብ በማንነታቸው ብቻ የታገቱ አካላትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ እንጠይቃለን፡፡" ብሏል።
ከቀናት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ መሰወራቸው የተነገረው የቀድሞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙና በባህርዳር ጠቅላይ ፍርድ ቤት አርብ እለት መቅረባቸው ይታወቃል።
ሮይተርስን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ከሰሞኑ ባወጡት ዘገባ በተለያዩ ከተማዎች የሚገኙ የፋኖ አባላት መታሰራቸውንና ሌሎቹንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ዘግበዋል።
መግለጫው አክሎም "ህግ ማስከበርን ሰበብ በማድረግ የፌደራል የፀጥታ መዋቅር በሕገ መንግሥቱ ለክልልና ለፌድራል ተለይቶ የተሰጠውን ኃላፊነት እና ሚና በደፈጠጠ መልኩ ክልሉን በሕገ-ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ሙከራ እንዲያቆም" ጠይቋል።
የአማራ ክልል ባለስልጣናት በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ እንዲመዘገብ ያደረጉት ጥሪ ትጥቅ ለማስፈታታት ነው ከሚሉ ወጣቶች ጋር ለግጭት መነሻ ሆኗል።
"መነሻው ፋኖዎችን ትጥቅ እናስፈታለን በሚሉ የፀጥታ አካላት የተጀመረ ነው። በዚያ ውጥረት ሳቢያ ፋኖዎቹም ትጥቅ አንፈታም በሚል ቦታ ይዘው ነበር" ነበር ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ እማኝነታቸውን ሰጥተው፣ ነዋሪዎችም ፋኖ ትጥቅ መፍታት የለበትም በሚል ተቃውሞ አሰምተዋል ብለዋል።
በሞጣ ከተማ በጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው ወጣቶች መካከል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትትሎ የከተማው አስተዳደር በእንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ከመጣል በተጨማሪ የሰዓት እላፊ አዋጅ ጥሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ "የሕግ ማስከበር ሥራውን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ማንኛውም ድርጊቶች ላይ አስፈላጊው የሕግ እርምጃ" እንደሚወሰድ አስታውቋል።
ቢሮው በመግለጫው ካለፉት ቀናት ጀምሮ ተጠርጣሪዎች ያለምንም ግጭት እጃቸውን ለህግ እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሆነና ፈቃደኛ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ጉዳት የመቀነስን ስራ ከህዝቡ ጋር እየተሰራ ነው ብሏል።
ህግ ማስከበር ብሎ የጠራው ተግባር ለህዝቡ ሰላም እና ደህንነት፣ ለክልሉ እና ሃገሪቱ የሰላም ዋስትናን ዓላማ አድርጎ እየተከናወነ ባለበት ወቅት የተለያዩ ግለሰቦች "ዋና ጠላቶች" ብሎ ከጠራቸው ጋር በመተባበር ክልሉንና ሃገሪቱን ለማፍረስ የሚሰሩ አካላት እንቅፋት እየሆኑ ይገኛሉ ብሏል።
"በአሁኑ ወቅት ከዋና ጠላቶታችን ጋር በማበር ክልላችንን እና ሀገራችንን ለማፍረስ የሚሠሩ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች እና ግለሰቦች በአንዳንድ የክልላችን አካባቢዎች ሰልፍ መጥራት እና ለሰላም ማስከብር ሥራው እንቅፋት የኾኑ ቅስቀሳዎችን እያደረጉ ይገኛሉ" ያለው መግለጫው በክልሉ የትኛውም አካባቢ ህጋዊ ጥያቄ ያቀረበም ሆነ ለሰልፍ ፈቃድ ያገኘ እንደሌለም ገልጿል።
የክልሉ መገናኛ ብዙኃን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር)ን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው "ህግ ማስከበሩ ዋና ዓላማው የክልሉ ህዝብ በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመስራት መብት ለማረጋገጥ ነው" ብለዋል።
አክለውም "ክልሉ ከወንጀለኞች የፀዳ ኾኖ እና አንድነቱ የተጠበቀ ሕዝብ ኖሮት ሊመጣ የሚችልን ጠላት ኹሉ በብቃት ለመመከት ነው" ማለታቸውን አስፍሯል።
በክልሉ አፈና፣ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ቀስቃሽነት እና ሌሎችም ወንጀሎች በርከት ብለው እንደተስተዋሉና ይህንንም ለመቅረፍ ወደተቀናጀ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።
ክልሉ የሕግን የበላይነት እንዲረጋገጥና በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን እያደረግኩ ነው ባለው ዘመቻም የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በተቀናጀ አሠራር እየተሳተፉ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንዲካሄድ ባዘዘው መሰረት ከግንቦት 9፣ 2014 እየተካሄደ ይገኛል።
ይህንንም ጥሪ ተከትሎ በርካቶች የጦር መሳሪያ ማስመዝገባቸውን የገለጹት ሰማ ጥሩነህ ምዝገባው በተሰጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቅ ባለመቻሉ እስከ ረቡዕ ግንቦት 17፣ 2014 ዓ.ም በሁሉም አካባቢዎች እንዲቀጥል መወሰኑንም አስረድተዋል።












