በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ቀናት የተከሰተው ምንድን ነው?

ካርታ

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ሕግ ማስከበር ያሉትን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ቀናት በተከሰቱ ግጭቶች በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።

በምሥራቅ እና በምዕራብ ጎጃም በሰሜን ወሎ አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተረጋጋና ዘላቂ ልማት የሚከናወንበትና ዜጎች ያለምንም የፀጥታ ስጋት ወጥተው የሚገቡበት ክልል እንዲሆን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ለዚህም ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፣ ከዚህ በተጻራሪ በክልሉ የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው ነበር።

ጉዳት ያስከተለ ግጭት

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በታጠቂ ቡድን መሪዎች፣ በቡድኖቹ አባላት እንዲሁም በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ከወሰዷቸው "የሕግ የማስከበር" እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ግጭቶችና ውጥረት መከሰቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተለይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው በሞጣ ከተማ ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ ውጥረት እንደነበር ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ በተከሰተው ግጭት ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች የተለያየ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ገልጸዋል።

"መነሻው ፋኖዎችን ትጥቅ እናስፈታለን በሚሉ የፀጥታ አካላት የተጀመረ ነው። በዚያ ውጥረት ሳቢያ ፋኖዎቹም ትጥቅ አንፈታም በሚል ቦታ ይዘው ነበር" ነበር ያሉት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ እማኝነታቸውን ሰጥተው፣ ነዋሪዎችም ፋኖ ትጥቅ መፍታት የለበትም በሚል ተቃውሞ አሰምተዋል ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ተፈሪ ዳምጤ የተባለን የአካባቢው የፋኖ አባል ጠቅሶ፣ ሐሙስ ዕለት የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂ የፋኖ አባላት ጋር መጋጨታቸውን ገልጿል።

ከዚህ በኋላም ውጥረቱ በርትቶ ነዋሪዎቹ ቀይ መለዮ ካጠለቁ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ግጭት ህፃናትን ጨምሮ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን በከተማው ከሚገኘው የህክምና ተቋም ምንጮች በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ፣ ሁለት በጥይት ተመትተው የሞቱ ሰዎች እንዲሁም 15 የሚሆኑ በተለያየ ደረጃ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መምጣታቸውን ስማቸውን ያልጠቀሱ የጤና ባለሙያ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በከተማው ውስጥ በተከሰተው አለመረጋጋት ሳቢያ በከተማዋ የሚያልፈው ዋና መንገድ በመዘጋቱ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሉን፣ ኢንተርኔት መቋርጡን፣ ትምህርት ቤቶች፣ ባንኮችና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸውን ነዋሪዎች አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም መራዊ ከተማ እንዲሁም በሰሜን ወሎ ወልዲያ አካባቢ ተመሳሳይ ውጥረት እንደነበረ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የሞጣ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, MOTTA CITY COMMUNICATION OFFICE

የምስሉ መግለጫ, የሞጣ ከተማ

'ሕገ ወጥነት መቆጣጠር'

ይህ ውጥረት የተከሰተው የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል ዘልቀው ጥቃት መፈጸማቸው መነገሩን ተከትሎ፣ በበርካታ አካባቢዎች በስፋት በተደራጀው ፋኖ በተባለው መደበኛ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን "ስም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች" ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን ተከትሎ ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ይበልጣል ከፋለ (ዶ/ር)፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ሕግ የማስከበር እርምጃ የሚወስደው በፋኖ ላይ ሳይሆን በቡድኑ ስም የተለያዩ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በሚፈጽሙና የክልሉን ሰላም በሚያደፈርሱት ላይ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች በአራት ቀናት ውስጥ መሳሪያቸውን እንዲያስመዘግቡ እንዲሁም የክልሉ መስተዳደር ስልጠና እንደሚሰጥ አሳውቆ ነበር።

ይህን የክልሉ መንግሥት "ሕግ የማስከበር" ያለውን እርምጃ ተከትሎ በፋኖ አባባላት መካከል ቅሬታ የተፈጠረ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ከህወሓት ጋር በተደረገው ውጊያ ከመንግሥት ኃይሎች ጎን ተሰልፎ የተዋጋው የፋኖ ቡድን ወደ ጎን ተገፍቷል ሲል ተፈራ ለሮይተርስ ተናግሯል።

ምንጮች እንደሚሉት ክልሉ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር በተያያዘ አንዳንድ የአካባቢ የፋኖ መሪዎች እና አባላት በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይነገራል።

ቢቢሲ አለመረጋጋቱ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መስተዳደርም ሆነ ከክልሉ የሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የፌደራል መንግሥት ምን አለ?

የፌደራል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አርብ ምሽት በአማራ ክልልና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የአገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሔ ነው ብሏል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገ ወጥነትና የሰላም መደፍረስን መንግሥት እንዲቆጣጠር ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ነበር ያለው መግለጫው፣ ብሔራዊ የፀጥታ ምክር ቤት አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን አስታውሷል።

ይህ እርምጃም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር አካል ነው ብሏል።

ጨምሮም በአማራ ክልል "በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር፣ በቡድን ተደራጅቶ ግለሰቦች ያፈሩትን ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም ላይ የተሰማሩ፣ በነፍስ ግድያ የሚጠረጠሩ፣ ግጭት በመፍጠር ክልሉ እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ መጠነ ሰፊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል" ብሏል።

በዚህም በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ከጦር መሳሪያዎች፣ ከዘረፉት ንብረትና ከተለያዩ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ገልጾ፣ ጉዳያቸውም እየተጣራ ለፍርድ እንደሚቀርቡ ገልጿል።