በአማራ ክልል ከዛሬ ጀምሮ የጦር መሳሪያ ምዘገባ ሊካሄድ ነው

በአማራ ክልል ከዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 09/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ምዝገባ ሊካሄድ መሆኑን የክልሉ የሰላምና የፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የጦር መሳሪያ ምዝገባው እስከ አርብ ድረስ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ከዚህ በፊት ያልተመዘገበ ማንኛውንም የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች በየአካባቢያቸው ባሉ ማዕከላት በመገኘት እንዲያስመዘግቡ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የጦር መሳሪያ ምዝገባው አስፈላጊነት "የአማራን ሕዝብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ አጋዥ ኃይል ለማጠናከር" መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የክልሉን ሕዝብ ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመ የተደራጀ ሥልጠና ሊሰጥ መሆኑንም የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታውቋል።
አቶ ደሳለኝ ህወሓት "ወደ ዳግም ጦርነት ለመግባት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ በተጨባጭ እያሳየ ነው" በማለት "ይህንን ለማክሸፍ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል በተጨማሪ ማንኛውም የጦር መሳሪያ ያለው ምዝገባ ካካሄደ በኋላ የተደራጀ ሥልጠና እንዲወስድም ይደረጋል" በማለት ተናግረዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ላይ ተወያይቶ ባወጣው መግለጫ ላይ በክልሉ ያለው "የሕግ ማስከበር ሥራ መላላት" እንደታየበት ጠቅሶ፣ እየተስፋፋ መጥቷል ያለው "ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ስጋት ውስጥ እየጣለ ይገኛል" ብሏል።
ጨምሮም ሕገወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት ስር እየሰደደ በመምጣቱ በሕገወጥ ታጣቂዎች ምክንያት በክልሉ ልማት፣ በዜጎች እንቅስቃሴ፣ የኢንቨስትመንት እድሎች፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይና በሌሎችም ላይ እንቅፋት በመፍጠር "የክልሉን ልማት በአደገኛ ሁኔታ እየተፈታተነ እንደሚገኝ" አጽንኦት ሰጥቷል።
ስለዚህም ይህንን ሕገወጥነት በአጭር ጊዜ ማረም አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ "ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲባል መልክ መያዝ" እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
እንዲሁም ምክር ቤቱ ህወሓት "በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እያነሳሳ በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል" ያለ ሲሆን፣ በዚህም ቡድኑ ሊሰነዝር ይችላል ላለው ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ከዚህ አንጻር ከፌደራል የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት "ከህወሓት የሚሰነዘርን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ በመሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ. . . ሕገወጦችንና ሥርዓት አልበኞችን በመቆጣጠር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ግንባር ቀደም የትኩረት አቅጣጫ" እንዲሆን መወሰኑን ገልጾ ነበር።
ለዚህም የፀጥታ ምክር ቤቱ በየደረጃው የፀጥታ ግብረ ኃይል አቋቁሞ "ሕገወጥነትን ለመቆጣጠርና ሕግን ለማስከበር ተገቢ ነው ያላቸውን ሕጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ" ውሳኔ ማሳለፉን የምክር ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።















