የአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅሩ የህወሓትን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ እንዲሆን አዘዘ

የፎቶው ባለመብት, Bahirdar City Communications
የአማራ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት ከህወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላለፈ።
ምክር ቤቱ በመግለጫው በክልሉ ያለው ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ መገምገሙን አስታውቆ፣ ህወሓት "በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት እያነሳሳ በአማራ ክልል ላይ ዳግም ጦርነት አውጇል" ብሏል።
ጨምሮም የክልሉ ሕዝብ ዳግም ለወረራና ለጥቃት እንዳይዳረግ የፀጥታ መዋቅሩ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲዘጋጅና ደጀኑ ሕዝብም የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለበት በዚሁ መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
ለዚህም ከፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የሚሰነዘርን ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ መቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ ያሉ "ሕገ ወጦችንና ሥርዐት አልበኞችን በመቆጣጠር" የክልሉን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ግንባር ቀደም ትኩረት ይሆናል ብሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል በይዞታ ይገባኛል አወዛጋቢ በሆነው አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በተመሳሳይ ባወጣው መግለጫ፣ ህወሓት በአካባቢው ሕዝብ ላይ ወረራ አውጇል በማለት ይህንን ስጋት ለመመከት በሚያደርገው ጥረት የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።
ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በጥቅምትና ኅዳር ወራት ላይ ከተካሄዱት ተከታታይ ከባድ ጦርነቶች በኋላ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሠራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ እንዳይገባ ካደረገ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ብሎ ነበር።
ባለፉት ወራት ሁለቱም ወገኖች አልፎ አልፎ ከሚያጋጥሙ መጠነኛ ግጭቶች ውጪ ባሉበት ሆነው ለሌላ ዙር ጦርነት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲከስሱ ቆይተዋል።
በዚህም ጦርነቱ መልሶ ሊያገረሽ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከሰሞኑ የሚሰሙት ዜናዎች እየጠቆሙ ነው።
በዚህ ሰሞንም ከፍተኛ የህወሓት መሪዎች ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ ውይይቶች እያካሄዱ መሆናቸውን በክልሉ ያሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በውይይቶቹ ላይ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መመቻቸት ሲባል ተቀባይነት ያገኘውን የተኩስ አቁም፣ ይህንንም ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በሚጠበቀው ሁኔታ አለመግባት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደተቋረጡ መሆንና ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተዋል።
ሊቀመንበሩ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በተገኙበት ስብሰባ ላይም "...በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቀጠል አንችልም። . . . ከጦርነት በፊት እና በጦርነት ጊዜ ዕድል ሰጥተናል። ሁሉም ፖለቲካዊ ችግር በሰላም እና በዲፕሎማሲ ብቻ አያልቅም" ብለዋል።
ጨምረውም "ሕዝባችን እየተራበ ብቻ ሳይሆን እየታመመ እና እየሞተ ነው፤ ጊዜ እያለፈ ነው፤ በዚህ ሁኔታ መቆየት አንችልም። ለሁሉም ነገር ግን ዕድል ሰጥተን መላክ ያለበትን መልዕክት ለሚመለከታቸው አድርሰናል። ስለዚህ እኛ ጨርሰናል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ ባሻገርም በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትግራይን ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች ከኤርትራ ሠራዊት ጋር ለአጭር ጊዜ የቆየ የከባድ መሳሪያ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ከሁለቱም ወገን በኩል የሚወጡት መረጃዎች ሌላ ዙር ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን ከመፍጠሩ ባሻገር፣ አንዳንድ ምንጮች በአንዳንድ ስፍራዎች መጠነኛ ግጭቶች መከሰታቸውን እየዘገቡ ነው።
ቢቢሲ ተከስተዋል ስለተባሉት ግጭቶች መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም እስካሁን ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልቻለም።
















