ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑ ቦታዎች የከባድ መሳሪያ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ታማኝ ምንጮች ለቢቢሲ አረጋገጡ።
ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለው እሁድ ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. ሲሆን በራማ እና ባድመ አካባቢ ባለው የኤርትራ ጦር ላይ ሲሆን፣ ጥቃቱን ተከትሎ በትግራይ ኃይሎችን በኤርትራ ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።
መቀለ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች እንዲሁ ክልሉ ከኤርትራ ጋር በሚዋሰንበት ድንበር አካባቢ ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ ከትግራይ ኃይሎች በኩል መከፈቱን ተከትሎ በስፍራው "ውጊያ ተካሂዷል" ብለዋል።
ነገር ግን የተኩስ ልውውጡ ለአጭር ጊዜ የቆየ መሆኑን እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው እግረኛን ያላካተተ በከባድ መሳሪያ የተደረገ እንደነበር ምንጩ ጨምረው ገልጸዋል።
የከባድ መሳሪያ ጥቃቱን ተከትሎ ለአጭር ጊዜ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ "የትግራይ ኃይሎች ወደ ኋላ አፈግፍገው ውጊያውም ቆሟል'' ሲሉ ተናግረዋል።
ጨምረውም ይህ ጥቃት "የህወሓትን ተንኳሽ ባሕሪይ የሚያሳይ ነው" ሲሉም አክለዋል።
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ አንድ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው እሁድ ከኤርትራ አዲ ኳላ ወደ ራማ ከባድ መሣሪያ መተኮሱን ገልጸው፤ ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች ለዚህ ከኤርትራ በኩል ተተኩሷል ላሉት ከባድ መሣሪያ የመልስ ምት አለመስጠታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በትግራይ ኃይሎችና በኤርትራ ሠራዊት መካከል በራማና ባድመ አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል የተባለው "ከእውነት የራቀ ነው" ሲሉም እኚህ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
ቢቢሲ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ከኤርትራ መንግሥት በኩል ይፋዊ ምላሽ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም እስካሁን አልተሳካለትም።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ለዓለም አቀፍ ተቋማት በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ጦርነት አስቸኳይ መፍትሔ በማፈላለግ እንዲያግዙ እና በትግራይ ላይ ተጥሏል ያሉት ከበባ እንዲያበቃ ካልተደረገ "ሌላ አማራጭ" ለመፈለግ እንደሚገደዱ ገልፀው ነበር።
ነገር ግን ይህ "አማራጭ" ያሉት ምን እንደሆነ በደብዳቤው ላይ አልተብራራም።
ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት የህወሓት ኃይሎች ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃቶችን በኤርትራ ላይ መፈጸማቸው ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልል ተስፋፍቶ ለወራት የቆየ ሲሆን አስካሁን መቋጫ አላገኘም።
ከፌደራልና ከክልል ኃይሎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ የሆኑት የህወሓት ኃይሎች፤ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ያወጀውን ተኩስ አቁም ተከትሎ ጦርነቶች ጋብ ያሉ ቢመስሉም በድንገት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጉዘው የሠራዊቱን ዝግጁነት መጎብኘታቸው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በቅርቡ ህወሓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ለመሳተፍ ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን እያሰረ መሆኑን የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
















