ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ 'ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ' በሚል ተጠርጥረው እንደተያዙ ጠበቃቸው ገለጹ

ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Region

ከቀናት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ መሰወራቸው የተነገረው ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ተጠርጥረው መያዛቸው እንደተነገራቸው ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለቢቢሲ ገለጹ።

ከአዲስ አበባ በደኅንነት ኃይሎች በሄሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር ከተማ መወሰዳቸው የተገለጸው ጄኔራሉ በዛሬው ዕለት አርብ ግንቦት 12/2014 ዓ.ም. ስምንት ሰዓት ላይ በባሕር ዳር ከተማ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ለቀናት ያህል በባሕር ዳር የከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የቆዩት ጄኔራሉ በዛሬው ዕለት ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠታቸውንና የተጠረጠሩበትም ጉዳይ "ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ" በሚል እንደሆነ ተነግሯቸዋል።

ከእርሳቸው በተጨማሪ ሌሎች የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ቢቢሲ ጠበቃቸውን የጠየቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉት እሳቸው ቢሆንም የሚጠረጠሩ ሰዎች እንዳሉና በሂደት ላይ መሆናቸውን መስማታቸውን አስረድተዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎም ብ/ጄኔራል ተፈራ ግንቦት 08/2014 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር የዋሉበትን ሁኔታ፣ ስለተፈጸመባቸው ድብደባም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት ለህክምና ወደ አዲስ አበባ የመጡት ጄኔራሉ በተያዙበት ዕለት ግንቦት 08/2014 ዓ.ም. ጓደኛቸው ጋር ሲጫወቱ ቆይተው ተሰነባብተው ወደ አስር ሰዓት አካካቢ መኪናቸውን እያሽከረከሩ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መሃል ቀለበት መንገድ ላይ ሲደርሱ ከፊትና ከኋላ ተሽከርካሪዎች እንዳስቋሟቸው ተናግረዋል።

"ሳይገጯቸው ተሽከርካሪ ገጨህብን በሚል እንዳስቆሟቸውና ከዚያ በኋላም አፍነው በኃይል ወደ ሌላ መኪና እንዳስገቧቸውና በወቅቱም ለማስገባት ሲሞክሩ በቦክስ እንደመቷቸው" መናገራቸውን ጠበቃቸው ገልጸዋል።

በተያዙበት ቅፅበት ይዘው ወደተሽከርካሪው ለማስገባት በሚሞክሩበት ጊዜ "ወደየት እንደሚወስዱኝ አላውቅም ነበርና በነበረው መፋፋግ" በቀኝ ወገባቸው በኩል፣ በደረታቸውና አንገታቸው ስር በቦክስ መመታታቸውን እንዲሁም በተጨማሪም አይናቸው አካባቢ እንዲሁ የተመቱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ይህንን ድርጊት የፈጸሙት የታጠቁና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎችና በቁጥርም በርከት ያሉ ነበሩ ብለዋል።

ጠበቃቸውም ዛሬ የአካላቸው ሁኔታ ደህና እንደሆነና እስከ ትናነትና ድረስ ግንባራቸው ላይ እብጠት እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በመጀመሪያ የግለሰቦቹን ማንንት ያልተረዱ ቢሆንም በኋላ ወደ ጨለማ ቦታ ወስደው ከመሬት በታች ባለ ክፍል ውስጥ (አንደርግራውንድ) ሲታሰሩና ይዘዋቸው የነበሩ ስልኮችን፣ የባንክ ደብተርና ተሽከርካሪ ተወስዶባቸው ከቀናት በኋላም በሄሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር ስላመጧቸውና የደኅንነት አካል መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ጨለማ ወደ ሆነው እስር ቤት ሲወሰዱ ተሸፍነውና እንዳያዩ ተደርገው ሲሆን ሁለት ቀናትም በዚያ ማሳለፋቸውን በዛሬው ዕለት ለችሎቱ አስረድተዋል።

ከዚያ በኋለም ወደ ባሕር ዳር በሄሊኮፕተር ያመጧቸው ሲሆን ወደ ባሕር ዳር ለምን መጡ? በአማራ ክልል ጥያቄ ነው? ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ ጠበቃቸው፣ ክልሉ ይፈልጋቸዋል ወይም እፈልጋቸዋለሁ የሚል እንዳልተሰማና ከመርማሪው አንደበት እንደሰሙት ምርመራው የተጀመረውና እየተከናወነ ያለው በፌደራልና በክልል ፖሊሶች ጥምረት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጄኔራሉ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ስጋት ነበራቸው ወይ የሚል ጥያቄ ቢቢሲ ለጠበቃቸው ያቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም ፈጸምኩት ብለው የሚጠረጥሩት ወንጀል ስለሌለ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጸማል የሚል ጥርጣሬ አልነበራቸውም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በዛሬው ችሎት ፖሊስ ምርመራ አለመጀመሩን ጠቅሶ የተጠርጣሪውን ቃል መቀበሉን በመግለጽ የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ብ/ጄኔራል ተፈራም በምላሹ "ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚያስጠረጥር ምክንያት የለም፣ ነገር ግን ከተጠረጠርኩ እንኳን ይቅረቡ የሚባሉ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ጊዜ ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በቅርቡም ለህክምና ወደ ውጪ ለማደርገው ጉዞ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት። እሱም ግምት ውስጥ ይግባልኝ" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው ችሎት ፖሊስ አለ የሚለውን ምርመራ አጠናቆ እንዲቀርብ ለግንቦት 22 ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጄነራል ተፈራ ተፈራ ማሞ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው።

ከሚኖሩበት ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በእግራቸው ውስጥ የሚገኙትን ጥይቶች በተመለከተ የሕክምና ክትትል ለማድረግ እንደነበረም ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ከሰሞኑ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በቅርቡም የትግራይ ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጦርነት ባነሱበት ወቅት የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል።