በምሥራቅ አፍሪካ በየ48 ሰከንዱ አንድ ሰው በረሃብ የመሞት አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ

የምስራቅ አፍሪካ ድርቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረን ዛሬ ባወጡት ሪፖርት በድርቅ በተጠቁት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በየ48 ሰከንዱ አንድ ሰው በረሃብ የመሞት አደጋ ተጋርጦበታል አሉ።

ሪፖርቱ ዓለም መከላከል የሚቻላቸውን ተደጋጋሚ አደጋዎች መከላከል አለመቻሉን አጉልቶ ያሳያል ተብሏል።

ጃሚኤል ኦብዘርቫቶሪ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በጥምረት የተሠራው ሪፖርት ዓለም ዳግም ከፍተኛ የረሃብ አደጋን ችላ ብሏል ሲል አስጠንቅቋል።

እአአ በ2011 በሶማሊያ ከ260,000 በላይ ሰዎችን (ከግማሽ በላይ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው) ከገደለው ረሃብ ጋር ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት ሪፖርቱ ስጋቱን አስቀምጧል።

ሪፖርቱ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብሏል። በኬንያ ደግሞ 3.5 ሚሊዮን ሰዎች በከፍተኛ ረሃብ እየተሰቃዩ ነው።

በሦስቱ አገራት ለከፍተኛ ረሃብ የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረበት ከ10 ሚሊዮን ወደ 23 ሚሊዮን አድጓል። በተደጋጋሚ ለቀረበው አስቸኳይ ድጋፍ "በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ" የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ተብሏል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ ድርቅ፣ በግጭቶች ምክንያት ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እና የኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ሰዎች ችግሩን እንዳይቋቋሙ አድርጓል። የዩክሬን ጦርነትም እየጨመረ የመጣውን የምግብ ዋጋ በማናር ችግሩን አወሳስቦታል።

"በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ቢሰጡም የዓለም መሪዎች በጣም ከመዘግየታቸው ሌላ የሰጡት ምላሽ አነስተኛ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ ይጋለጣሉ" ሲሉ ያስጠነቀቁት የኦክስፋም ግሬት ብሪቴይን ከፍተኛ ኃላፊ ጆን ፕላስቶው ናቸው ።

"በቅርቡ በኢትዮጵያና በኬንያ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎበኝቻለሁ። በሶማሌ ክልል እንደ ሙስጠፋ ያሉ አርብቶ አደሮችን አግኝቻለሁ። ሙስጠፋ ከአንድ ከብቱ ውጪ ሁሉም ከብቶቹ እና አራቱን ግመሎቹን አጥቷል። የሰዎች ጤና እየተጓደለ ነው፣ ብዙዎች ራሳቸውን ማጥፋት ጀምረዋል፣ የሃብት እጥረት በማኅበረሰቦች እና በቤተሰብ መካከል ግጭት እየፈጠረ ነው። በዚህም በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ህይወታቸው እያለፈ ነው።"

የህፃናት አድን ድርጅት የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቃል አቀባይ ሻኮ ኪጃላ በበኩላቸው፤ "5.7 ሚሊዮን ህጻናት በከፍተኛ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለባቸው እያየን ነው። እርምጃ ካልወሰድን በሶማሊያ ከ350,000 በላይ የሚሆኑት ሊሞቱ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እያንዳንዷ ደቂቃ ስታልፍ ለረሃብ እና ለህፃናት ሞት በጣም እየቀረበን እንመጣለን። ይህ እንደገና እንዲከሰት ከፈቀድን እንዴት ከዚህ ጋር መኖር እንችላለን?" ብለዋል።

ሴቶች የራሳቸውን ምግብ በመቀነስ ሌሎችን ለመመገብ እና አስተማማኝ ያልሆኑ ስራዎችን ስለሚሰሩ ከፍ ሲልም ስለሚሰደዱ በተለይም ጾታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች ይጋለጣሉ ተብሏል።

እአአ በ2012 በድምሩ 20.7 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ብሔራዊ ዕዳ በ2020 ወደ 65.3 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ይህም የአገራቱን ሃብት ከሕዝብ አገልግሎት እና ከማኅበራዊ ጥበቃ በማውጣት ወደ የኪሳራ እየነዳቸው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያ፣ ለኬንያ እና ለሶማሊያ ከተጠየቀው የ4.4 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ውስጥ ማግኘት የቻለው ሁለት በመቶው (93.1 ሚሊዮን ዶላር) ብቻ ነው።

ባለፈው ወር ለጋሾች 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ቢገቡም፣ ከዚህ ውስጥ 378 ሚሊዮን ዶላሩ ብቻ ነው የተሰጠው።

ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረን የጂ7 አባል አገራት መሪዎች ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ፕላስቶው "ሰዎች እየተራቡ ያሉት ዓለም የምግብ ወይም የገንዘብ እጥረት ስላጋጠማት ሳይሆን በፖለቲካዊ ውድቀት ምክንያት ነው። ሃብታም አገራት የዩክሬንን አስከፊ ቀውስ ለመፍታት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ አሰባስበዋል። አገራት የሰውን ልጅ ስቃይ ለመከላከል ሃብት ማሰባሰብ ቢችሉም ይህ የሚሆኑ ከፈለጉ ብቻ ነው" ብለዋል።

"የከፋ ጉዳት ከደረሰባቸው አገራት አንዷ ለሆነችው ሶማሊያ በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ይፋ ያደረገው የ25 ሚሊዮን ፓውንድ እርዳታ የሩሲያ ወረራ በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዩናይትድ ኪንግደም ለዩክሬን ከሰጠችው 400 ሚሊየን ፓውንድ ጋር የሚነጻጸር አይደለም።"

የጃሚኤል ኦብዘርቫቶሪ ኃላፊ የሆኑት ጉዮ ሮባ በበኩላቸው "ቀውሶች ከቁጥጥር ውጪ እስኪሆኑ ጠብቆ ምላሽ ከመስጠት ለጋሾች፣ የልማት ኤጀንሲዎች፣ መንግሥታት እና የግሉ ሴክተር ከተጎዱ ማኅበረሰቦች ጋር ለመተባበር መዘጋጀት አለባቸው" ብለዋል።

ብዙ ጊዜ የደረሰውን ችግር አምነው መቀበል ፈቃደኝነት ስለሌለ የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታትም ለምላሹ መዘግየት የራሳቸው ኃላፊነትም አለባቸው ተብሏል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ መንግሥታቱ በግብርና እና ማኅበራዊ ጥበቃዎች ላይ በማተኮር ዜጎቻቸው ረሃቡን በተሻለ ሁኔታ እንዲቋቋሙ አላደረጉም። መንግሥታትም ከፖለቲካ ይልቅ ለሰው ልጅ ህይወትን ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስቧል።

አገራዊ ድንገተኛ አደጋዎችን በፍጥነት በማወጅ እና ሃብቶችን በማሰባሰብ በጣም ለተቸገሩ ማዞር ይገባቸዋል ብሏል።