ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ አደገኛ ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ ተገኘ

ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ

የፎቶው ባለመብት, US ATTORNEY'S OFFICE, CALIFORNIA

በመጠኑ ገዘፍ ያለና መብራትን ጨምሮ ሁሉ ነገር የተሟላለት ዋሻ ተገኘ።

531 ሜትር የሚረዝመው ይህ ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ ሐዲድ የተዘረጋለት፣ የአየር መቆጣጠሪያ ስርዓት (ቬንትሌሽን) የተገጠመለት ሁሉን ያሟላ ነው ተብሏል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይህ ዋሻ መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ በድብቅ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አደገኛ ዕፅ ማሾለኪያ እንደሆነ ለመረዳትም የተወሰነ ጊዜ ወስዶባቸዋል።

ይህን ዋሻ ተጠቅመው አደገኛ ዕፅ አስተላላፊዎች ኮኬይን፣ ሜታመፌታሚን እና ሄሮይን ዕፆችን ሊያስተላልፉ የነበሩ ስድስት ሰዎችንም በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ከሰሞኑ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ዕፅ ማስተላለፊያ ዋሻ

የፎቶው ባለመብት, US ATTORNEY'S OFFICE, CALIFORNIA

የሳውዘርን ካሊፎርኒያ አውራጃ የአሜሪካ አቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት ዋሻው ከመሬት 18 ሜትር ጠልቆ የሚገኝ እና አንድ ሜትር መጠነ ዙርያ (ዲያሜትር) አለው ብሏል።

መርማሪዎች ዋሻው መኖሩን ከማወቃቸው በፊት በቲጁዋና አካባቢ ካለፈው ዐርብ ጀምሮ መኪናዎች ብቅ እያሉ አንዳች ነገር አራግፈው ሲመላለሱ ማስተዋል ችለዋል።

ይህን ተከትሎም ወደ ዋሻው የሚጠጉ መኪኖች ላይ ፍተሻ ሲደረግ አደገኛ ዕፅ ተገኝቷል።

ይህን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ በዚያ አካባቢ አንድ መጋዘን የተገኘ ሲሆን መጋዘኑ ውስጥ ደግሞ ድንበሩን ተከትሎ የተቆፈረ ምሥጢራዊ ዋሻ መግቢያን አግኝተዋል።

የአቃቢ ሕግ ጽሕፈት ቤት እንደሚለው 799 ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ 74 ኪሎ ግራም ሜታፌታሚን እና 1.5 ኪሎ ግራም ሄሮይን በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ዕድሜያቸው ከ31 እስከ 55 የሚሆኑት እነዚህ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ዕድሜ ይፍታህ ሊፈረድባቸው ይችላል።

ከዚህ በላይ የ1 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣትም ይጣልባቸዋል።

በካሊፎርኒያ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲህ ያለ ምሥጢራዊ ዋሻ የተገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

ያ ዋሻ 1ሺህ 313 ሜትር ርዝመት የነበረው ሲሆን በርዝመቱም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ነው።

እንደ አውሮጳዊያኑ ከ1993 ጀምሮ 90 የሚሆኑ አደገኛ ዕፅ ማስተላለፊያ የምድር ውስጥ ድብቅ ዋሻዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋለው ዋሻ

የፎቶው ባለመብት, US ATTORNEY'S OFFICE, CALIFORNIA